27 ህዳር 2020, 15:18 EAT

ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አህመድ በአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ከተላኩት ልዩ ልዑካን ጋር መወያየታቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።
ከሦስት ሳምንታት በላይ በሆነውና በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ያጋጠመውን ወታደራዊ ግጭት በተመለከተ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የተሰየሙት ሦስቱ የቀድሞ የአፍሪካ አገራት መሪዎች አዲስ አበባ መግባታቸው የተነገረው ትናንት ነበረ።
ጠቅላይ ሚንሰትሩ በውይይቱ ቡድኑ ለኢትዮጵያ ጉዳይ ትኩረት መስጠቱን አንስተው ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን “በትግራይ እየተከናወነ ስላለው የሕግ ማስከበር እርምጃ” ማብራሪያ እንደሰጡና ባለፉት ሁለት ዓመታት የህወሓት ኃይል በአገሪቱ የዲሞክራሲ ግንባታ ላይ ሲፈጥር ነበር ያሉትን እንቅፋት በዝርዝር አስረድተዋል ብሏል ጽ/ቤታቸው።
ማዕከላዊው መንግሥት የትግራይ ክልልን ከሚያስተዳድረው ህወሓት ጋር የነበረው አለመግባባት ተካሮ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ወደ ወታደራዊ ግጭት የተገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የትግራይ ኃይሎች በሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ከገለጹ በኋላ ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድን አግኝተው ተወያዩት የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዮአኪም ቺሳኖ፣ የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰንና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩትን ጋሌማ ሞትላንቴ ናቸው።
ልዑኩ ትናንት አዲስ አበባ የገባው በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ሦስት ሳምንት ካስቆጠረ እና የመጨረሻ የተባለው ዘመቻ እንዲካሄድ ጠቅላይ ሚንሰትሩ ካዘዙ በኋላ ነው።
- በትግራይ ክልል ለሰብዓዊ እርዳታ ‘መተላለፊያ ሊመቻች’ መሆኑ ተገለፀ
- የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኞች አዲስ አበባ ገቡ
- ጠ/ሚ ዐብይ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ በውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ አሳሰቡ
- “ሕግ የማስከበር ዘመቻው የተራዘመው ለንፁሃን ዜጎች ቅድሚያ በመስጠታችን ነው” የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ
ግጭቱ ያሳሰባቸው የአፍሪካ ኅብረትና የተለያዩ አካላት ውይይት እንዲደረግ ሲወተውቱ የቆዩ ሲሆን የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሳም መፍትሔ የሚያፈላልጉትን ልዑካን የሰሙት ባለፈው ቅዳሜ ነበር።
ልዑካኑ በቀዳሚነት ግጭቱን ለማስቆም ከሁሉም ወገኖች ጋር በመነጋገር ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣትና “ግጭቱን ባስከተሉት ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለማስገኘት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ” ተብሎ ነበር።
ጠቅላይ ሚንሰትሩ ከልዑካኑ ጋር በተወያዩበት ወቅት የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል እና በመላው አገሪቱ ሕግ የማስከበር ግዴታ እንዳለበት መጥቀሳቸውንና ይህን ማድረግ የሚሳነው ከሆነ ብዙ ኪሳራ ሊያደርስ እንደሚችል ማስረዳታቸውን የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በተጨማሪም መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ እየወሰደ ባለው እርምጃ ለሰላማዊ ዜጎች ጥንቃቄ እንደሚደረግ፣ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ መንግሥት የደርሻውን እንደሚወጣ እና ግጭቱን በመሸሽ ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ ዜጎችን በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለማስፈር እና ወደፊት ወደ ቀያቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን ገልፈዋል።
ቀደም ሲል ልዑኩ ጉዳት እያደረሰ ያለው ግጭት ቆሞ ውይይት የሚጀመርበትን መንገድ ይፈልጋል ተብሎ የተነገረ ቢሆንም ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም።
የትግራይ ክልልና የህወሓት አመራሮች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እንዲሁም አገራት ግጭቱ እንዲቆምና ውይይት እንዲደረግ በተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን፤ መንግሥትም ይህንኑ እንዲቀበል ከተለያዩ ወገኖች ግፊት ሲደረግበት መቆየቱ ይታወሳል።
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሕግን ማስከበበር ስለሆነ ከህወሓት አመራሮች ጋር ምንም አይነት ድርድር ለማድረግ ፍላጎት እንደሌለ ገልጸዋል።
ልዑካኑ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ እንደተገለጸ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመንግሥት ስለጉዳዩ በተሰጠ መግለጫ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የሚልኳቸውን ልዩ መልዕክተኞች በግል ተቀብለው ከማነጋገር ውጪ ድርድር እንደማይኖር አመልክቶ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከልዑካኑ ጋር ባደረጉት ውይይት የትግራይ ክልል ሕዝብ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ሕገ-መንግሥታዊ የሆነ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮችን ለማቋቋም ጥረቶች እየተካሄዱ መሆኑንና በወንጀል የሚፈለጉ የህወሓት ኃይሎችን ለሕግ ለማቅብ አስተዳደራቸው ቁርጠኛ መሆኑን ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በመንግሥት ላይ የሚደረገውን ግፊት በተመለከተ በዚህ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰጡት ምላሽ መንግሥታቸው እየወሰደ ያለው እርምጃ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠብ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
በዚህም መሰረት መንግሥት ተፈጸሙ ላላቸው ወንጀሎች ተጠያቂ የሆኑ የህወሓት አመራሮችን ለፍርድ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ በመሆኑ ለድርድር እንደማይቀመጥ አሳውቋል።
በትግራይ በኩል ያሉ ባለስልጣናት ግን እራስን በራስ የማስተዳደር መብታችንን ተጠቅመን ምርጫ በማካሄዳችንና መብታችንን በማስከበራችን የፌደራል መንግሥቱ ዘመቻ ከፍቶብናል ሲሉ ይከሳሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ክልል አመራር ከአፍሪካ ኅብረትና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አካላት ጋር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚደረገው ግጭት በአስቸኳይ በሚቆምበት ሁኔታ ላይ የሚወያይ ተወካይ መሰየሙን ገለጸ።
በወጣው መግለጫ ላይ ያልተቋረጠ ሰብአዊ እርዳታ የሚቀርብበት መንገድ እንዲመቻችና ተፈጸሙ የተባሉ የትኞችም የጦር ወንጀሎች በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግባቸው ጠይቋል።
በትግራይ ክልል የተከሰተው ቀውስ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የህወሓት ባለስልጣንት የአፍሪካ ሕብረትና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጣልቃ ገብተው እንዲያሸማግሏቸው ሲጠይቁ እንደነበር ይታወሳል።
በትግራይ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት ተጠናክሮ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፤ በመንግሥት በኩል የመጨረሻ የተባለውና ትናንት የተጀመረው ዘመቻ በክልሉ ዋና ከተማ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በትግራይ ክልል ከሦስት ሳምንታት በላይ ተቋርጦ ባለው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ምክንያት በአካባቢው እተካሄደ ስላለው ግጭት አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።