27 ህዳር 2020

በጥቅምት ወር የመጨረሻ ቀን በምዕራብ ትግራይ ማይካድራ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት በትንሹ ስድስት መቶ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከቀናት በፊት ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ሪፖርት አመልክቷል።
በኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው በነዋሪዎች ላይ አሰቃቂ ጥቃት ተፈጽሟል። መርመራውን ያካሄደው ቡድን አባል ለቢቢሲ እንደገለጸችው ማይካድራ ከተማ ሲደርሱ በከተማ የሚረብሽ የአስክሬን ጠረን እንደነበር ተናገራች።
“በዚህ መሰል የምርመራ ሥራ ላይ ተሳትፎ ሲደረግ በተቻለ መጠን ግላዊ ስሜትን ወደ ጎን በማድረግ ሙያዊ ሥራ ላይ ማተኮር ይጠበቃል” የምትለው ሐይማኖት አሸናፊ፤ በማይካድራ በነበራት ቆይታ ግን “የተፈጸሙት ኢ-ሰብዓዊ ደርጊቶች እንደ አንድ ሰው ስሜትን የሚጎዱ ነገሮች አጋጥመውኛል” ብላለች።
- ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የዘመቻው የመጨረሻ ምዕራፍ መጀመሩን አስታወቁ
- የሳተላይት ምስል፡ አክሱም አየር ማረፊያ ከጥቃቱ በፊት እና በኋላ
- በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር የኤርትራ ስም ለምን ይነሳል?
በማይካድራ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የሆነውን ለማጣራት የሄደው የምርመራ ቡድኑ አባል በመሆን ወደ ስፍራው ያቀናችው ሐይማኖት፤ ወደ ከተማዋ የደረሱት ጥቃቱ ከተፈጸመ ከቀናት በኋላ እንደነበረ ታስረዳለች።
ከተማዋ እንደደረሱ በጥቃቱ ወቅት “ንብረት የመዝረፍ እና ማቃጠል በማጋጠሙ አስፓልቱ በሙሉ በቆሻሻ የተሞላ ነበር። የተቃጠሉ እቃዎች በየመንገዱ ተጥለው ይታያሉ። የወዳደቁ ጫማዎች እና አስክሬን የተሰበሰቡባቸው ቃሬዛዎች እዚያም እዚህም ይታያሉ” በማለት ወደ ከተማዋ ለቀናት ተመላልሰው ሪፖርቱን ባጠናቀሩበት ወቅት የተመለከተችውን ታስረዳለች።
የመርማሪ ቡድኑ አባላት ወደ ማይካድራ ሲደርሱ ምንም እንኳ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቀብር የተፈጸመ ቢሆን፤ በከተማዋ ውስጥ ግን “የሚረብሽ የአስክሬን ጠረን ነበር” ትላለች።
ተዘዋውረው እንደተመለከቱትም በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎችን ቀብር ያስፈጸሙ ሰዎች በከተማዋ በሚገኘው የአቡነ አረጋዊ ቤተ-ክርስቲያን በርካታ ሰዎችን የቀበሩባቸውን የጅምላ መቃብር እንዳሳይዋቸው ትናገራለች።
“በቀብሮቹ ላይ የተሳተፉ ሰዎች እንደነገሩን የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ስለነበረ፤ ሟቾችን ለመቅበር ቀናት እንደፈጀባቸው ነግረውናል” ትላለች።
አምነስቲ ትክክለኛነታቸውን አረጋግጫለሁ ያላቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች በቃሬዛ ወደ ቀብር ስፍራ የሚወሰዱ በርካታ አስከሬኖችን የሚያሳዩ ናቸው።
በርካታ ሰዎች በተገደሉባት ከተማ ውስጥ “ከጥቃቱ ያመለጡ ሰዎች እና የዓይን እማኞችን ታሪክን መስማት ከባድ ስሜት ይፈጥራል” የምትለው ሐይማኖት፤ ክስተቱ በነዋሪው ላይ ያስከተለው የሐዘን ድባብ ከባድ ነው በማለት ሁኔታውን ታስረዳለች።
ከሁመራ ከተማ በስተደቡብ በ30 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው የማይካድራ ከተማ የትግራይና የአማራ ተወላጆችን ጨምሮ የሌሎችም ብሔር አባላት የሚኖሩባት ሲሆን የነዋሪዎቿ ቁጥርም እስከ 50 ሺህ የሚገመት ነው።
ከጥቃቱ በኋላ የደረሰውን ጉዳት ለመመርመር ወደ ስፍራው የተጓዙት ባለሙያዎች በከተማዋ የነበረው የሰዎች እንቅስቃሴ በጣም ቀዝቃዛ እንደነበር ሐይማኖት ትናገራለች።
በማይካድራ ከተማ ውስጥ “ብዙ ሰዎች አልነበሩም። አብዛኞቹ ሰዎች ከተማውን ጥለው ወጥተው ነበር። ስንደርስ ከጥቃቱ የተረፉና ከከተማዋ ሸሽተው ቆይተው የተመለሱ ሰዎችን ነበር ያገኘነው” ትላለች።
ማይካድራ ከተማ አቅራቢያ ሰፋፊ የንግድ እርሻዎች መኖራቸውን የምትገልጸው ሐይማኖት፤ የእርሻ ሥራው ብዙ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልግ ብዙ ወጣት የሆኑ ወንዶች ከተለያዩ ስፍራዎች ወደ ከተማዋ ለሥራ እንደሚጓዙ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚስን ሪፖርት ይጠቅሳል።
በተለይ ለወቅታዊው የእርሻ ሥራ ወደ አካባቢው የሚሄዱ ወጣቶች ከአንድ ስፍራ የሚመጡት በአንድ ቦታ የመስፈር ዝንባሌ እንዳላቸውና ነዋሪዎቹም በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ይገኛሉ።
በዚህም “የ’ሳምሪ ሰፈር’ የሚባል ቦታ አለ። ‘ግንብ ሰፈር’ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ደግሞ የአማራ ተወላጆች የሚኖሩበት አካባቢ ነው” እንደሆነ ሐይማኖት ትገልፋለች።
ሳምሪ እነማን ናቸው?
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ወገን ለይተው በማይካድራ ከተማ ጥቃቱን ያደረሱት ‘ሳምሪ’ ተብሎ የሚጠራ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን በከተማዋ ከነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ መዋቅር ጋር በመጣመር ነው ብሏል።
ሐይማኖት የነበረችበት የምርመራ ቡድን ከአከባቢው ባገኘው መረጃ “ሳምሪ የሚባለው ቡድን ኢ-መደበኛ የሆነው የወጣቶች ስብሰብ ሲሆን ከሌላ የትግራይ አካባቢ የመጡ ወጣቶችን ያቀፈ ሳይሆኑ እንደማይቀር ይገመታል” ትላለች።
“‘ሳምሪ’ የተባለው የወጣቶች ቡድን አሰቃቂ ወንጀል ቢፈጽምም፤ በአንጻሩ የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያንና በእርሻ ቦታዎች ሸሽገው በመደበቅ የብዙ ሰዎች ሕይወትን እንዳተረፉ” ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።
በምሳሌነትም አንዲት የትግራይ ተወላጅ 13 ሰዎችን በቤቷና በእርሻ ቦታ ደብቃ እንዳተረፈች፤ እንዲሁም ሌላ ሴት “አጥቂዎቹ በእሳት ሲያቃጥሉት የነበረን የአንድ ተጎጂን ሕይወት ለማትረፍ ስትሞክር በጥቃት አድራሾቹ እጇን በገጀራ ተመትታ ቆስላለች” ሲል ሪፖርቱ እራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ሌሎችን ለማዳን የጣሩ ሰዎችን ጠቅሷል።
ከቀናት በፊት ስለክስተቱ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ አምነስቲ ኢንትርናሽናል በማይካድራ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ የወጡ ምስሎች ሐቀኝነት በማራትና የዓይን እማኞችን በመጥቀስ በከተማዋ ውስጥ ማንነትን መሰረት ያደረገ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙን ባወጣው ሪፖርት ላይ ድርጊቱ ማንነት ለይቶ የተፈጸመ መሆኑን ገልጾ ነበር።
ኮሚሽኑ በዚህ ድርጊት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት በማቅረብ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏልል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሼል ባችሌትም በማይካድራ ከተማ የተፈጸሙት “ግድያዎች መረጋገጥ ከቻሉ እንደ ጦር ወንጀል ይቆጠራል” በማለት ተናግረዋል።
በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና የትግራይ ክልል ኃይሎች ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ከገቡ ከሳምንት በኋላ በምዕራብ ትግራይ የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ ነበር በማይካድራ ከተማ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የሚያመልክቱ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ፎቶግራፎች መታየት የጀመሩት።
ይህ ድርጊት በማይካድራ የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ መዋቅር የፌዴራሉ ሠራዊትን እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቆ ከመውጣቱ በፊት “ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በመተባበር በተለይ “አማሮችና ወልቃይቴዎች” ያሏቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት” መፈጸማቸውን አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ የመንግሥት ባለስልጣናት ጥቃቱን የፈፀሙት የህወሓት ታጣቂዎች ናቸው ማለታቸው ይታወሳል።
የትግራይ ክልል ባለስልጣናት በበኩላቸው በማይካድራው ድርጊት ውስጥ እጃቸው እንደሌለበት የገለጹ ሲሆን፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ውንጀላውን “መሠረት ቢስ” በማለት፤ ጥቃቱ በገለልተኛ ወገን ይጣራ ሲሉ ጠይቀው ነበር።