ሁሌ እናስታውሳቸው ተቀብሮ እንዳይቀርአኩሪ ታሪካቸው!!!!!!!

ቆንጂት ተክሉ/ ትርሲት ማን ናት ???

ማሳሰብያ፡ የመጀምርያው ፎቶ፡ቆንጂት ተክሉ ስትሆን ሁለተኛው ገነት ግርማና ቆንጂት የሁለተኛው የኢሕአፓ ጉባኤ በቋራ፤ሶስተኛው ቆንጂት ከነትጥቋ እና ሌላው ቆንጂት ገበሬውን በማንቃትና በማስተማር ላይ ተሰማርታ ነው።በ አዲስ አበባ ህቡዕ ገብታ በቤት ሰራተኝነት ስትሰራ በአሰሳ መያዟን በተመለከተ ራሷ ከጻፈችው በመጥቀስ እንጀምር ።

” ግብረ ሰይሉ የሚፈጸመው እዚያው ሁሉም እስረኛ በተሰበሰበት ነበር። እስረኛው እስከ ሙታንታው ድረስ እንዲያወልቅ ይደረግና ጉልበቱን ወደ ደረቱ ሰብስቦ፤እጆቹን ወደ ቁርጭምጪቱ ዘርግቶ እንዲቀመጥ ይደረጋል ፡፤ ከዚያም እጆቹና እግሮቹ በፕላሲትክ ገመድ ጠብቀው ይታሰራሉ ። ጠማማ ዘነዘና ብጤ ወይም የሆነ እንጨት በታጠፉት ጉልበቶቹና በተዘረጉ እጆች መካከል ይከተታል። ሁለቱ የዘነዘና ወይም የእንጨት ጫፎች በሁለት ረዳቶች ብድግ ይደረጉና ሁለት ወንበሮች ላይ ይቀመጣሉ ። እንደ ግብረ ሰይል ፈጻሚው ውቃቢ በሮቲሰሪ (ዶሮ መጥበሻ) ሽቦ ላይ ተሸብልላ አስፈላጊውን ማጣፈጫ አቃምመው ያደርጉበት ዘንድ እንደሚያሽከረክሯት ዶሮ እስረኛውም በዚህ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ ይሆንና ለልዩ ልዩ ግብረ ሰይል ዓይነት ይዳረጋል። የሽብሩ ጓዝ ግሳንግስ የሚከተሉትን ያጠቃልላል ። አለንጋዎች፤ ልዩ ልዩ ቅርጽና መጠን ያላቸው ዱላዎች፤ ሁሉ ዓይነት መጠን ያላቸው የፕላስቲክ ገመዶች፤ ከባድ የብረት ዘለበት ያላቸው ቀበቶዎች፤ክከትልቅ መኪና ወይም የትራክተር ጎማ ተቀድደው የወጡ ረጃጅም የጎማ ቁራጮች፤ጎራዴዎችና ካራዎች፤ ክብሪትና የሲጋራ መለኮሻ፤የፕላስቲክ ቀረጢቶችና የቆሸሹ የእግር ሹራቦች/ካልሲዎች/። ግብረ ስየል ፈጻሚዎች በሰው ገላ ላይ የሚመርጧቸው ተወዳጅ ስፍራዎች የውስጥ እግር፤ብብት፤የጀርባ አጥንት፤ጡትና የጡት ውልብልቢት (ጫፍ)፤ጭን ወዘተ ነበሩ ።የግብረ ስይሉ ክንዋኔ፤የአጋልጡ ማታለያ፤ ቀኑን ሙሉ ይካሄዳል ። ዕረፍት የምናገኘው ለምግብና ለሽንት ስንወጣ ብቻ ነበር ። አዳራሹ ውስጥ የነበረው የጽዳት ሁኔታ የሽንት ቤቱን ያህል የከፋ ነበር ።

“ትርሲት በሰፊው ጽሁፍዋ እርገጤ መድበውን፤ሰሙ ንጉስን፤ቀልቤሳና እስረኛን ሠገራ ውስጥ ማጥለቅ የሚወደውን የከፍተኛ 14 ዓለማየሁን፤ሞላ ብርሃኔን በግፍ ስራቸው ጠቅሳቸዋከች ። ልጆችን ሳይቀር ሰብስበው ለግድያ ይወስዱ እንደነበርም፤ሴት እስረኞችንም እየደፈሩ ይገድሉም እንደነበር አጋልጣለች ። ከማድ ቤት የማልወጣ ጭቁን ምስኪን ነኝ በማለት ልትፈታ የቻለችው ትርሲት ሂደቱን በዚህ መልክ ጽፋዋለች።

“እሁድ ዕለት በ12 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ከጠዋቱ ላይ ዘገየ ብቻ ነበርና ያለው ተነስቼ ወደ እሱ ቀረብኩ ።የቀሽአኮ አባልና የከፍተኛ ዘበኞች አለቃ ነበር”። የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የዓመቱ ክብረ በዓል ዛሬ ነው፤ ካድሬ እንግዳን ሐሙስ ዕለት ጠይቄው ትሄጃለሽ የሚል ተስፋ ሰጥቶኝ ነበር፤ግን አልተመለሰምና ቅዳሴው እንዳያመልጠኝ እባክህ ስደደኝ አልኩት ። ሞላም ጠብቂ ሊለኝ ሲጀምር አቋረጥኩና እነዚያ የጠፉ ቀጣሪዎቼን በሚመለከት እዚያው መስራት እቀጥልና የሚካሄደውን እነግርሃለሁ፤እኔን ምንም የማላውቅ ገረድ በነሱ ወንጀል እንድሰቅይ አድረገውኛል በማለት ንዴትን ያንጸባርቃል ብዬ በገመትኩት የድምጽ ቃና አክዬ ተናገርኩ ። ” ግሩም ነው አለ’ ዘገየ ። ይህ ነው የሰራተኛ መንፈስ ። የተቻለውን ያህል መረጃ እየሰበሰብሽ ከኔ በስትቀር ለሌላ እንዳትነግሪ አስታውሺ ብሎ ከዚያ በደም ከተበከለ አዳራሽና አጥር ግቢ አውጥቶ ሸኘኝ ።”

አላዋቂ የቤት ሰራተኛ መስላ ከስቃይና ሞት ያመለጠችው ቆንጂት ለመሆኑ ማን ነበረች ? ቆንጂት አባትዋ በውጭ ጉዳይ ምኒስቴር በውጭ ሀገር ኢምባሲ ተመድበው የሚሰሩ ነበርና ወደ ሁለተና ደረጃ ትምህርት ልትደርስ ስትል ውጭ ሀገር ሄዳ የኖረች ናት ። ከፍተኛ ትምህርቷን በማስተርስ ያጠናቀቀችው በሰሜን አሜሪካ ሲሆን ቆንጂት ተጫዋችና ብልህ እንደነበረችም የሚያውቋት ይናገራሉ ። ባሏ የሆነውን ያይኔእሸት ተፈሪን –በደርግ የተገደሉት የጄኔራል ተፈሪ ባንቲ ልጅ ጋር የተገናኘችውም በዚሁ በስሜን አመሪካ ነው ። መንግስቱ ጂኔራል ተፈሪና ሌሎችን ከረሸነ በኋል ያይኔእሸት ተፈሪንም ይዞት አሰቃይቶ ለሞት ዳርጎታል። ቆንጂት በአሜሪካ የተማሪው ማህበር ንቁ ተሳትፎ የነበራት ሲሆን ጊዜ ሳትወስድም በኢሕአፓ መዋቅር ገብታለች። በውጭ ሀገራት ያሉት የድርጅቱ አባሎች (ኋላ የተሰዉት ክፍሉ ከበደ፤ ሙሉጌታ ዜና ፤ሙሉጌታ ሱልጣን፤ስዩም ከበደ፤ዘራብሩክ አበበ ወዘተ–ሁሉም በደርግ የተገደሉ) ወደ ሀገር ሲመለሱም ትርሲትና ባለቤቷም አዲስ አበባ ተመልሰው ነበር ። በመንግስት የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተቀጥራ ስትሰራና የድርጅቷንም ተልእኮ ስትወጣ ቆይታ የመያዝ አደጋ ሲመጣ ህቡዕ ገብታ በቤት ሰራተኛነት ተቀጥራ ግዳጇን ስትወጣ ቆይታለች ። ከላይ እንደተጠቀሰው በአሰሳ ተይዛ ከብዙ ስየል በኋላም ስትለቀቅ ወዲያውኑ ወደ ህቡዕነት ተመልሳ ወደ አሲምባ አቅንታሠራዊትን ተቀላቅላለች።

ቆንጂት በአሲምባ ተጋዳይም በፖለቲካ አስተማሪነትም ተሰማርታ በታሪካዊው የአሴፋት የሴት ታጋዮች ጉባኤ ከእነ አበራሽ በርታ ጋር ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።

ኢሕአሠ ላይ በወያኔና ሻዕቢያ ጦርነት ሲከፈትና ወደ ጸለምት ማፈግፈግ ግድ ሲሆን በሸምሸሚያና ሌሎች ቦታዎች የጓዶችን ጽናትና ጥንካሬ በመጠበቅ ትግሉን ካስቀጠሉት ጀግኖች አንዷ ነበረች ። ጽኑ የድርጅት አባል ሆናም አንጃዎችንም ታግላለች ። ቆንጂት በጸለምት፤በበለሳ፤ በቋራ አርማጨሆ፤ በወልቃይት ጠገዴ በሰራዊቱ ልዩ ልዩ እርከኖች ሳትታክት የተጋለች ቆራጥ ጓዲት ነበረች ። ከአርሶ አደሮች ጋርም ለመዋሃድ በመቻሏም (እስከ ንግግሩዋ ቃና ድረስ) ቆንጂት በውጭ ሀገር የቆየች ምሁር መሆኗንም መገመትም አይቻልም ነበር ። ቆንጂት ተክሉ የኢሕአፓ አባል ሴቶች ምን ያህል ከሕዝብ ጋር እንደተዋሃዱና በቆራጥነት እንደታገሉ ደማቅ ምስክር ነበረች ። ትሁት፤ ተጫዋች፤ በዚያው ልክ ህዝብ አፍቃሪ፤ ቆራጥ፤ ደፋር፤ የመንደር ልጆች እናትና አሰተማሪ ትሁት ታጋይ ነበረች ። ደከመኝን የማታውቅ። የእነ መድፈሪያሽ ወርቅ (ጀሚላ)፤ የነ ጽጌ መድህን፤የነ ወጣት ጽጌ ታላቅ እህት።

ቆንጂት ተክሉ በ1982 በልብ ሕመም በቋራ ሜዳ አርፋለች ።

በአርአያነቷ ብርቅ የኢሕአፓና የኢትዮጵያ ጀግና ሴቶች ምሳሌ ነበረች።

……….በእንግሊዘኛ የፃፈችው የቆንጂት ተክሉ ማስታወሻ በአማርኛ ተተርጉሞ በቅርብ ጊዜ በገበያ ላይ ይውላል።

የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!!