
ቅጽ 48 ቁ.4 ታህሣሥ፣ 2013 ዓ. ም
የህወሓት ቅጥፈትና እብጠት፣ ለውድቀትና ውርደት
አንድ እርምጃ ብቻ ሳይሆን ብዙ እርምጃዎችን በመራመድ የኢትዮጵያ ልጆች የትእቢት ግንቡን አፍርሰዋል፣ ኢትዮጵያን የምንል ሁሉ ተደስተናል፣ ኢትዮጵያም የዓመታት እንባዋ ይታበስ ዘንድ ቀኑ ደርሷል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታላቅ ገድል ሠርቷል፤ በግንቡ ውስጥ ተሸሽገው የነበሩትን የህወሓትን መሪዎች ለሕግ እስኪያቀርብ ድረስ ግና እረፍት የለውም፡፡
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከተመሠረተበት ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ በፕሮግራሙ ቀርፆ የተነሳው “በኢትዮጵያ ውስጥ የቅራኔዎች ሁሉ እምብርትና አውራው በብሄረሰቦች መካከል ያለው ቅራኔ ነው፣ አማራም የትግራይ ሕዝብና የሌሎች ብሄረሰቦች ጠላት ነው” የሚል ነበር። በዚህ በተሳሳተና በጥላቻ የተሞላ አስተሳሰቡ አገራችንን ለግማሽ ምዕተ–ዓመት ሲያተራምስ ኖሯል።
ድርጅታችን ኢሕአፓ ገና ከጠዋቱ ጀምሮ ይህን የተሳሳተ አስተሳሰብ ከባድ መስዋዕትነትን በመክፈልም ጭምር ሞግቶታል፣ ታግሎታል። ያኔም ሆነ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቅራኔ፣ በአንድ በኩል በመደቦች መካከል ሚዛናዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ የዜጎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና በሕዝብ ሉዓላዊነት ላይ ተመሥርቶ በሚቋቋም ሕዝባዊ መንግሥት የሚያምኑና በሌላ በኩል ደግሞ ሠፊውን ሕዝብ በድህነት አስሮ ማኅበራዊ ፍትኅ የሚነጥቀውን አምባገነናዊ ሥርዓት ማስቀጠል በሚፈልጉ ኃይሎች መካከል የነበረው ተቃርኖ መሆኑን በማስተማር ከፍተኛ ትግል አካሂዷል። ይሁን እንጂ በጥላቻ የተሞላው ህወሓት፣ የኢትዮጵያ ገዥ መደብ አባላት የተለያዩ ብሄረሰቦች ስብጥር መሆኑን ሊገነዘብ የማይፈልግ ቡድን እንደሆነ እስካሁን ዘልቋል፡፡
የዜግነት መብትን ለማስከበር በመላው ሕዝባችን የተካሄደው ትግል፣ የኢሕአፓ ትግል ተጨምሮበት፣ የተዳከመውና እጅግ በሚዘገንን ጭካኔው ምክንያት የሞራል ስብዕና ያልነበረውን ደርግ ሕዝባችን በከፍተኛ መስዋዕትነት አቸነፈው፡፡ ግብዙ ህወሓት ግን ድሉ የርሱ ብቻ እንደሆነ በመቁጠር አዲስ አበባን የተቆጣጠረበትን ግንቦት 20ን የሕዝብ በዓል ሳይሆን የህወሓት በዓል አስመስሎ ሕዝባችን ቋቅ እስኪለው ድረስ ከበሮ ሲደለቅ ተኖረ። አልፎ ተርፎም የህወሓትን የተሳሳተ አመለካከት የሞገቱትን እንደ ኢሕአፓ ዓይነት ኅብረብሄር ድርጅቶችን ወግቶና አግልሎ፣ የብሄረሰብ ድርጅቶችን ባንድ ምሽት ጠፍጥፎ በማደራጀት የይስሙላ የሽግግር መንግሥት መሠረትኩ አለ። ቀጥሎም በሀገራችን ውስጥ ጥላቻን ያነገሠውን ሕገመንግሥት አፀደቀ። ህወሓት፣ ምንም እንኳን ከሥልጣን ቢወገድም፣ ሕገ–መንግሥቱን ከለላ በማድረግ በሀገራችን ውስጥ በቀበረው ፈንጂ እስካሁን ድረስ ሀገሪቱን በቀጣይነት ከማመስ ወደኋላ አላላም። በሥልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታት እንደ ኦነግ ዓይነቶችን ይዞ፣ በአማራው ላይ ያነጣጠረ ከፍተኛ ጥላቻን፣ መፈናቀልንና ጭፍጨፋን አካሂዷል። የአገሪቱን አስተዳደር በእኩይ ዓላማ፣ ብሄረሰብና ቋንቋን መሠረት በማድረግ ከከፋፈለ በኋላ፣ ለይስሙላ ራስ–ገዝ ፌዴራላዊ አስተዳደሮችን መሠረትኩ አለ። ራሱ ህወሓት የሞግዚት አስተዳዳሪ ሆኖ በፌዴራሊዝም ስም አሀዳዊ መንግሥትን ይመራ እንደነበር ደግሞ ሕዝብ የሚያውቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው።
ህወሓት የሞግዚት አስተዳደርን ተግባራዊ ባደረገበት 27 ዓመታት ውስጥ የሀገሪቱን ኤኮኖሚ በመቆጣጠር ከፍተኛ ምዝበራ ሲያካሂድ ኖሯል። እንዲሁም ከደርግ ባልተናነሰና እንዲያውም በከፋ መልኩ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በስፋትና በሚያሰቅቅ ሁኔታ ፈጽሟል፣ እየፈጸመም ይገኛል። ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የተለያዩ ብሄረሰብ አባላት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና አባላት፣ የሲቪክ ማኅበራት…ወ.ዘ.ተ በህወሓት ያልተሰቃየ የኅብረተሰብ ክፍል አልነበረም።
ሕዝባችን ግን የህወሓትን ግፍ በዝምታ አላየውም፣ በተለያዩ መንገዶች አምርሮ ታገለው እንጂ። በትግሉም ብዙዎች በሕይወት፣ በአካል ጉዳተኝነት፣ በእስር፣ በስደት…ወ.ዘ.ተ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል። ምርጫ ብሎ ሲያቀናብራቸው ከነበሩት የምርጫ ቲያትሮች አንዱ በሆነው በምርጫ 97 ሲሸነፍ፣ እንኳን ሥልጣን ለሕዝብ ሊያስረክብ ቀርቶ በሥልጣን ለመቆየት ሲል እራሱ ባመነው መሠረት ከ200 በላይ ዜጎቻችንን በጠራራ ፀሐይ ረሽኗል። በመሆኑም የሕዝቡ የትግል ቁርጠኝነት በየጊዜው እየጎለበተ ሄዶ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው ቅራኔም ተባብሶ ህወሓት በ2010 ዓ.ም. ከሥልጣን ተወገደ።
ከሥልጣን ከተወገደ በኋላም መቀሌ ላይ መሽጎ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሕዝባችንን አሁንም እያመሰና እያተራመሰ ይገኛል። የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በፌዴራል መንግሥት ውስጥ በደህነንት፣ በወታደራዊና በፖሊስ ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛ ማዕረጋቸውን እንደያዙ በሰላም መኖር ተስኗቸው፣ ራሳቸው ያወጡትን ሕገ–መንግሥት ጥሰው፣ ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ ሆኖ “ለምን ከፈላጭ ቆራጭ ሥልጣናችን ተገፋን” በሚል ትዕቢት የወንጀል ሤራቸውን በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘረጉ።
ብጥብጥንና አለመረጋጋትን በመፍጠር ለብዙ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀልና እንግልት ምክንያት ሆኑ። በጎንደር፣ የቅማንት ብሄረሰብ በአማራ ተጨቁኗል በሚል የውሸት ትርክት ባሰማሯቸው የቅማንት ፅንፈኞች በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ተፈናቀለ፣ ሕይወት ጠፋ፣ ቤትና ንብረት ወደመ። በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአማራና በአገው ብሄረሰቦች ላይ እኩይ የዘር ማጥፋት ተግባራቸው እስካሁን እየተካሄደ ይገኛል። በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሐረርና ድሬዳዋ ከኦነግ ሸኔ ጋር ቅንጅት በማደረግ ባመዛኙ በአማራ ብሄረሰብና በአርቶዶክስ አማኞች ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ ተካሂዷል።
መቀሌ ላይ “የፌዴራሊስት ኃይሎች” የሚሏቸውን ፅንፈኞችና የነሱ ተስፈኞችን በየጊዜው እየሰበሰቡ መመሪያ ከመስጠትም በላይ፤ ማሠልጠኛ ጣቢያዎች አደራጅተው የገንዘብና የመሣሪያ ድጋፍ በመስጠት የሽብር ስምሪት ሲያካሂፉ እንደነበር መንግሥት በጊዜው አስታውቋል። ህወሓት፣ ዜጎችን ኢ–ሰብዓዊና አሰቃቂ በሆነ መንገድ ያሰቃየውን፣ የገደለና ያስገደለውን፣ በግፍ ቤተሰባቸው እንዲበትን አድርጎ አያሌ ኢትዮጵያውያንን ጎዳና ላይ የጣለውን የደህነነቱ የቀድሞ መሪ መቀሌ ውስጥ ደብቆ አሳልፌ አልሰጥም አለ። እንዲያውም የፌዴራል መንግሥቱን ለማስፈራራት በሚመስል መልኩ በወታደራዊ ትርዒት የታጀበ የተለያየ የጦር ክፍል ማሳየቱን ተያያዘው።
በተጨማሪም ትግራይ ውስጥ የተደበቁትን የህግ ተፈላጊዎች ለመያዝ ወደ ክልሉ የዘለቀውን የፀጥታ አስከባሪ ኃይል አስሮ፣ ተልዕኮውንም አኮላሽቶ መልሶ ወደ አዲስ አበባ ላከው። የፌዴራል መንግሥቱ ትግራይ ውስጥ ያለውን የሰሜን ዕዝ በከፊል ወደ ሌላ ቦታ ሊያንቀሳቅስ ሲሞክር ሕፃናትንና ሴቶችን ሰብዓዊ ጋሻ አድርገው የመኪናና የታንክ እንቅስቃሴን አገዱ። ህወሓት በመግለጫዎቹ ትግራይ ከፈዴራል መንግሥቱ ጋር ግንኙነት የሌላት ነፃ መንግሥት ለመሆን እያኮበኮበች ያለች አስመሰላት። ይህም ሆኖ ደግሞ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ 3 እንዲሉ፣ ከፌዴራል መንግሥቱ የሚቀርበው ዓመታዊ በጀት አንዲት ሳንቲም ሳትጎድል እንዲላክ ማስጠንቀቂያ መስጠት ተዘወተረ።
በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የ2012 ዓ. ም ብሄራዊ ምርጫ እንዲራዘም ሲወሰን፣ መራዘሙን መቃወም መብታቸው ቢሆንም፣ ራሳቸው የጻፉትን ሕገ–መንግሥት በመጣስና ለፌዴራል መንግሥት ብቻ የሚሰጠውን ምርጫ የማስፈፀም ሥልጣን በመጋፋት በክልላቸው ውስጥ “ምርጫ” አካሄዱ። በዚህም ድርጊት እብጠታቸው ጣራ እንደነካ ይበልጥ ገሃድ ሆነ። ህወሓት በዕብሪት ይህን ሁሉ ሲፈጽም የፌደራል መንግሥቱ ፈጥኖ ወደ ጦርነት አለመግባቱ በአንድ በኩል የሚደነቅ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ለማንኛውም ተከሳች አደጋ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ላይ ነበር ወይ? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች መታየት ከጀመሩ ውሎ አድሯል። ይህ ሁሉ ተጠራቅሞ በኢትዮ–ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ትግራይ ላይ የተመደበውን ብዙ መሣሪያና በርካታ ሜካናይዝድና እግረኛ ክፍለ ጦሮችን የያዘውንና የሰሜን ዕዝን ድንገት በማጥቃት ህወሓት ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላበት አደጋ አደረሰ።
ህወሓትን እዚህ ደረጃ ለመድረስ ያበቃው ለምን ከሥልጣኔ ተገፋሁ? ወደ ቀድሞ ሥልጣኔ መመለስ አለብኝ በሚል ዕብሪት፣ ምናልባትም የፌዴራል መንግሥቱም ሕግን በማስከበርና የንፁሃን ዜጎችን ሕይወት በመታደግ በኩል ባሳየው ዘገምተኝነት ምክንያት ደካማ መንግሥት ነው በማለት ተደፋፍሮም ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን የህዳሴ ግድብን ለመገንባት የወሰደችውን እርምጃ ሊያደናቅፉ ከሚሞክሩ የውጭ ኃይሎች የሚሰነዘረውን ማስፈራሪያና ተጽዕኖ በማየት ከነዚህ ኃይሎች ሊገኝ ይችላል ብሎ በገመተው የዲፕሎማሲ፣ የማቴርያልና ሌላም ዕርዳታ ራሱን አግዝፎና የምመኘውን ማግኘት የምችልበት አጋጣሚው አሁን ነው ብሎ በማስብ ሊሆን ይችላል፡፡
ትክክለኛ እሳቤውን የሚያውቀው ራሱ ህወሓት ቢሆንም በእኛ በኩል ግን ይህ በሠራዊቱ ላይ የፈጸመው ተግባሩ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የሀገርና የሕዝብ ክህደት ነው እንላለን። በመሆኑም ህወሓት ከሀገራችን ሕጋዊ የፖለቲካ መድረክ መታገድ ይኖርበታል፣ መሪዎቹም ለፍርድ መቅረብ ይገባቸዋል እንላለን። ስለዚህም መንግሥት ሕግ ለማስከበር እየወሰደ ያለው ወታደራዊ እርምጃ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን።
ጦርነቱ በንፁሃን ዜጎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለባቸው ከተሞች አካባቢ ጥንቃቄ እንዲደረግ የተሰጠውን መመሪያ ኢሕአፓ ያደንቃል። እስከ አሁን ባለው መረጃ መሠረት 40ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ምክንያት ወደ ሱዳን ተሰድደው መግባታቸው ከሚያሳዝኑት የጦርነት ውጤቶች አንዱ ገፅታ ነው። መንግሥት እብሪተኛውንና አሽባሪውን ህወሓትን በአስቸኳይ ሥርዓት አስይዞ ስደተኞቹ ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል እንላለን። ከዚህ በተጨማሪ በየጊዜው በግፍ ከቀያቸው ተፈናቅለው ለረዥም ዓመታት በሱዳን መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞችም ጉዳይ ከዚህ ጋር አብሮ የሚታይ ይሆናል ብለን እናምናለን።
በጦርነቱ አካባቢ የሚኖሩ ሰላማዊ የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያንም የእለት ተእለት ኑሯቸው በመመሰቃቀሉ፣ ችግራቸው እንዲቀረፍ መንግሥት የሚቻለውን ሁሉ ሊያደርግ ይገባል። የትግራይን ሕዝብም ህወሓት ከ40 ዓመት በላይ ቀጥቅጦ ሲገዛው ስለነበር የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ ማገዝ ያስፈልጋል። እስካሁን ነፃ በወጡት አካባቢዎች ውስጥ ከሕዝብ ፈቃድ ውጭ፣ በጉልበትና በመሣሪያ ኃይል፣ ነዋሪውን በማፈናቀል ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ ይገኛሉ፡፡
የነዚህን አካባቢ ተወላጆች ህወሓት፣ ከ27 ዓመታት 4 በላይ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሊያስከስሰው በሚችል ደረጃ፣ ሲገድላቸው፣ ሲያስራቸው፣ ሲያሳድዳቸውና ሲያፈናቅላቸው ኖሯል። ከላይ የጠቀስናቸውን አካባቢዎች ነፃ በማውጣት ደረጃ ከመከላከያ ጎን በመሰለፍ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሺያም አብሮ እንደተዋጋና መስዋዕትነት እንደከፈለ የሚታወቅ ነው። ህወሓትም ከነዚህ አካባቢዎች ተሸንፎ ሲወጣ በተለይም ማይ ካድራን ሲለቅ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ዓለምአቀፋዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳረጋገጡት፣ ንብረት ከማውደም አልፎ በተለይም በማይካድራ ውስጥ በተለይ በአማራው ላይ ያነጣጠረ ዘር ተኮር ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈጽሟል።
መንግሥት ይህን ግፍ የፈጸሙትን እያጣራ ለፍርድ ማቅረብ የሚጠበቅበት አንዱና ዋነኛው ሃላፊነቱ ነው። በዚህ ሁኔታ እነዚህን አካባቢዎች መልሶ ወደ ትግራይ ክልል ማስገባት ፈፅሞ ሊታሰብና ሊወሰድ የማይገባው እርምጃ ነው እንላለን፡፡ ቋንቋንና ብሄርን መሠረት ያደረገው የፌደራል አከላለል የችግሮቹ ሁሉ መንስዔ በመሆኑ፣ ለዘላቂ መፍትሄ በሰከነ መንገድ ተወያይቶ ሕገ–መንግሥቱን ማሻሻል የግድ ነው።
ለጊዜው ግን የእነዚህ አካባቢዎች ቀድሞ የተፈናቀሉና ለስደትም የተዳረጉ ያካባቢው ነዋሪዎች ሁሉ ተመልሰው እንዲሁም አሁን በቦታው ባሉ ኗሪዎች፣ ያገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻዎችን ባሳተፈ ሁኔታ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት ሃሳብ እናቀርባለን። በክልሎች መካከል ያሉ የወሰን ውዝግቦችም ሆኑ በተለያዩ ክልሎች የሚደርሱ በማንነት ላይ ያተኮሩ ግድያዎችና መፈናቀሎች መሠረታዊ መነሻቸው ክልልን ለተወስነ የማኅበረሰብ ክፍሎች በብቸኛ ባለቤትነት የሰጠው ብሄር ላይ ትኩረት አድርጎ የተዋቀረ ፌደራላዊ አወቃቀርና ይህን አወቃቀር ሕጋዊ ያደረገው ሕገ–መንግሥት ነው። ሕገ–መንግሥቱን የቀረፀው አስተሳሰብ በህወሓት ሲጠነሰስ ጀምሮ ውጤቱ ሀገሪቱን ነውጥ ውስጥ መክተትና ሲበዛም መበታተን እንደሆነ ስናመላክት ብዙ ዓመታት አልፈዋል።
ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት፣ ብሎም ቀጣይ የሆነ የኤኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በየጊዜው የሚነሱትን እሳቶች ለማጥፋት ከመሞከር ይልቅ ለዚህ ሁሉ ጣጣ የዳረገን ሕገ–መንግሥቱን ሰፋ ባለና ፍትሃዊነትንና እኩልነትን መሠረት ያደረገ፣ ፌደራላዊ አስተዳደርን እንዲቀረጽ ሆኖ ሕገ–መንግሥቱን የማሻሻል ሂደት ይዋል ይደር የሚባል ጉዳይ ስላልሆነ በሁሉም ባለድርሻዎች ተሳትፎ እንዲጀመር ማድረግ እጅግ መሠረታዊና አጣዳፊ ጉዳይ ነው እንላለን። የሀገራችን መሠረታዊ ችግርች ለማስወገድ ሕገ–መንግሥታዊና መዋቅራዊ ሳንካዎችን ሳይነኩ የሚደረጉ ማሻሻያዎች ከቀውስ አዙሪት ሊያላቀቁን እንደማይችሉ ጠንቀቆ መረዳት ተገቢ ነው።
በሀገራችን ውስጥ የተካሄደውን ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በትክክል ማወቅ፣ ግፉን የፈጽሙት በአግባቡ እንዲዳኙ፣ ተጎጂዎችም ፍትኅንና ተገቢውን እውቅናም እንዲያገኙ፣ የመብት ጥሰቶችና ግጭቶች ዳግም እንዳይደገሙ፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን በጋራ መሻት እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ ለሀገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ይህን እውን ለማደረግ ደግሞ ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንዳነሳነው እውነተኛ የብሄራዊ እርቅና መግባባት አጀንዳን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
በህወሓት መወገድ ምክንያት ለብሄራዊ መግባባትና እርቅ የሚረዱ አዳዲስ አገራዊ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ስለሆነ መንግሥት እነዚህን ዕድሎች እንድንጠቀምበት ያስፈልጋል። ለዚህም፣ መንግሥት አስፈላጊውን መደላድል እንዲያመቻች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራትም አስፈላጊውን ገንቢ ግፊት እንዲያደርጉ ኢሕአፓ በድጋሚ ያሳስባል። 5 በሌላ በኩል ህወሓት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ውስጥ ባዶ 6 በሚባል የሚስጥር እስር ቤቶች እጅግ በርካታ እስረኞችን ሲያሰቃይበት እንደነበረ ይታወቃል። እነዚሀ የፖለቲካ እስረኞች፣ የኢሕአፓ አባላትን ጨምሮ፣ የተለያዩ ፖለቲካ ድርጅት አባላት እንደሆኑ ይታወቃል። በአሁኑ ሰዓት በትግራይ የሚካሄደው የሕግ ማስከበር ሥራ እነዚህን የመብት ሰላባዎች ማፈላለግና ነፃነታቸውን ማረጋገጥ እንደ አንድ ግብ ይዞ መጓዝ ይገባዋል እንላለን።
በቀጣይም የህወሓት መሪዎች በእነዚሀ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ለጆች ላይ ላደረሱት በደል እንዲጠየቁና መዳረሻቸው ያልታወቁትን ሁሉ የት አንዳደርሷቸው እንዲጠየቁ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። በዚህ ጦርነት ሂደት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማዕከላዊ መንግሥትና ለመከላከያ ሠራዊቱ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ ኢሕአፓ በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ያደንቃል፣ ይደግፋልም።
ጦርነቱ በትግራይ እየተካሄደ እያለ፣ በሌሎቹ የሀገራችን ክፍሎች ውስጥም ከህወሓት ጋር በቅንጅት ወይም በራሳቸው የጥላቻ አጀንዳ አሁንም ብሄር ተኮር ጥቃት የሚያካሂዱ ኃይሎች ስላሉ መንግሥት በነዚህም ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድና ሕዝባችንም የሰላምና የተረጋጋ ሕይወት የመኖር ናፍቆቱ እንዲረጋገጥለት ማደረግ ይገባዋል፡ በተጨማሪም ዛሬ በትግራይ የተረጋገጠውና በሌሎችም የሀገራችን ክፍሎች በተደጋጋሚ እንደዳየነው የክልል ልዩ ኃይል ተብለው የተመሠረቱት ኃይሎች ከፀጥታ አስከባሪነት አልፈው ለሀገር ደህንነት አስጊ ከሆነ ቁመና ላይ ደረስዋል። ሀገራችን በምትገኝበት የተካረረና ያልተረጋጋ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ሲታይ ደግሞ ይህ ምን ያህል አደጋን እንደሚያስከተል ግልጽ ሆኗል።
ከዚህ አኳያ የክልል ልዩ ኃይል ተብለው የተደረጁ ኃይሎች ሁሉ በአንድ ማዕከል ሥር የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ አንድ አካል ሊሆኑ ይገባል እንላለን፡፡ በየክልሉ ለሚደረጉ የፖሊስና ፀጥታ የማስከበር ተግባሮች ደግሞ በየክልሉ የሚገኙ የፖሊስ ኃይል በብዛቱም ሆነ በትጥቁ ዓይነትና መጠን ተልዕኮውን የሚመጠን ኃይል ብቻ እንዲሆን ማደረግ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።
በመጨረሻም ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ ይህን ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ ከመሩ በኋላ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ ሆነው በለውጡ ላይ ብዥታው እየጨመረ የመጣውን ዜጋ አረጋግተው አገራችን ወደ ሰላምና ልማት የምትመለስበትን ዕድልና መንገድ እንዲያመቻቹ ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንዲጠቀሙበት አደራ እንላለን፡፡
ሰላምና የዜጎች በሕይወት የመኖር ዋስትና ዛሬውኑ ይረጋገጥ!
መልካሙ መንገድ ትህትና እንጂ እብጠት መዳረሻው ጥፋት ነው!
ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ !
