በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች በአውሮፕላን ወደ እስራኤል ተጉዘዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተከትለዋቸው ይጓዛሉ ተብሏል። BBC Amharic

እስራኤል ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቤተ እስራኤላውያንን ወደ እየሩሳሌም አመጣለሁ ብላ ቃል ከገባች ሳምንታት በኋላ ነው ይህ የሆነው።
ቤተ እስራኤላውያኑ እስራኤል ውስጥ ለዘመናት ከኖሩ አይሁዶች ጋር ዝምድና ያላቸው ናቸው።
ቀደምት ቤተ እስራኤላውያን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የተጓዙት ሚስጢራዊ በሆነ ጉዞ ነበር።
በቅርቡ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ግጭቱ ወደ ጎንደር እንዳይዘመትና ቤተ እስራኤላውያን ሰለባ እንዳይሆኑ የሚል ስጋት ነበር።
ለዚህም ነው የእስራኤል መንግሥት ኢትዮጵያዊያን አይሁዶችን ወደ ሃገር ቤት ለማምጣት የወሰነው ተብሏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እንዲሁም ተቀናቃኛቸው ቤኒ ጋንትዝ 316ቱ ቤተ እስራኤላውያን ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ተቀብለዋቸዋል።
“ባለቤቴ ሳራህ እና እኔ ዓይናችን እንባ አቅርሮ ነው የተቀበልናችሁ” ሲሉ ኔታኒያሁ መግለጫ ለቀዋል።
“ቤተ እስራኤላውያኑን፤ ኢትዮጵያዊያን አይሁድ እህት ወንድሞቻችን ከአውሮፕላን ሲወርዱ በተመለከትን ጊዜ፤ ወርደው የእስራኤልን ምድር ረግጠው ባየን ጊዜ፤ እንባችን መጣ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አክለውም በመግለጫቸው “ሕልማችሁን ለማሳካት ብዙ ጊዜ ጠብቃችኋል፤ እነሆ ዛሬ ተሳክቷል” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ የተወለዱትና በፈረንጆቹ 1984 ወደ እስራኤል የተጓዙት የስደተኞች ሚኒስትሯ ፒኒና ታማኖ-ሻታ ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው የቤተ እስራኤላውያኑን ጉዞ አስተባብረዋል።
‘ኦፕሬሽን ሮክ ኦፍ እስራኤል’ የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው የቤተ እስራኤላውያኑ ጉዞ ሐሙስ ዕለት ነው የተከናወነው።
‘ፈላሻ ሙራ’ በሚል የተለምዶ ስም የሚታወቁት ቤተ እስራኤላውያን በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ወደ ክርስትና ኃይማኖት የተቀየሩ አይሁዶች ዘር ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ራሳቸውን አይሁድ እያሉ በመጥራት በእምነቱ መሠረት መኖር የጀመሩ ናቸው።
ቤተ እስራኤል እየተባሉ ከሚጠሩት ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በተለየ ግን ፈላሻ ሙራ ወዲያውኑ የእስራኤል ዜግነት ላያገኙ ይችላሉ ተብሏል።
ይህ የሆነው የአይሁድ ሕግ ከየትኛው ዘር እንደመጡ በውል ያልታወቁ ሰዎች ዜግነት ወዲያውኑ አያገኙም ስለሚል ነው።
ይህ ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል።
ነገር ግን የእስራኤል መንግሥት ከአምስት ዓመት በፊት ሁሉኑም በፈረንጆቹ 2020 መጨረሻ ወደ ሃገር ቤት ለማምጣት መወሰኑን አስታውቆ ነበር።
16 ሺህ 600 ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል ለመጓዝ ቢያመለክቱም የእስራኤል ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን እስካሁን መመዘኛውን ያሟሉት 2 ሺህ ብቻ ናቸው ብሏል።
ይህን ተከትሎ የመብት ተሟጋቾች መንግሥት የገባውን ቃል አጥፏል ሲሉ እየተቹ ይገኛሉ።
100 ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች አርብ ዕለት ወደ እስራኤል ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጥር 2021 [በፈረንጆቹ] ደግሞ የተቀሩት 1700 ወደ እስራኤል እንደሚጓዙ መንግሥት አስታውቋል።
በ1980ዎቹ ሱዳን ስደተኛ ካምፖች ውስጥ የነበሩ ቤተ እስራኤላውያን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናኼም ቤጊን ባዘዙት መሠረት በሞሳድ የስለላ ተቋም ድጋፍ በሚስጢር እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል።
ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በርካቶች በዕቃ መጫኛ አውሮፕላን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ተጉዘዋል።
በእስራኤል የኢትዮጵያዊያን አይሁዶች ትብብር የተሰኘው ተቋም ቤተ እስራኤላውያን በብዛት ሥራ አጥና ድሃ ናቸው፤ አልፎም መገለል ይደርስባቸዋል ሲል ይከሳል።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሻሻል እንዳለ ተነግሯል።