
የተባበረ የሕዝብ ትግል ምንጊዜም አቸናፊ ነው
ኅዳር ፲፱ ቀን ፪ ሺህ ፲፫ ዓ. ም
የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር ነው። ጦርነት ደግሞ በማንኛውም መሥፈርት አስከፊ ነው፣ ሕይወትን ይቀጥፋል፣ ንብረት ያወድማል፣ አገርንም ሊያፈርስ ይችላል። የአገር ህልውና ሲደፈርና ሕግ ሲጣስ ግን ዜጎች ከጥፋት ለመታደግና የሀገራቸውን ህልውና ለማስከበር ሕይወታቸውን መስዋዕት ያደርጋሉ፣ አሁን በሀገራችን እየታየ ያለውም ይኽው ነው። ፀረሕዝብና ፀረ-አንድነት የሆነው ህወሓት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የሀገራችንን የግዛት አንድነትና ህልውና፣ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስርና ወንድማማችነት ሲያናጋ እንደቆየ የሚታወቅ ነው።
ህወሓት የሕዝባችንን መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች ደብዛቸውን በማጥፋትና በፍጹም አምባገነንነት በዜጎች ላይ ተወዳዳሪ የሌለው ስቆቃ ለአሥርተዓመታት ሲፈጽም ኖሯል። ይህን እኩይ ተግባሩን ሕዝቤ ነው በሚለው በትግራይ ሕዝብ ላይ ጭምር ፈጽሞታል። በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በጋብቻ ተጋምዶ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ በሃሰት ትርክት እርስ በራሱ እንዲጠራጠር በማድረግ እንደ ጠላት እንዲተያይና በሀገራችን ውስጥ ትርምስና ግድያ እንዲካሄድ አድርጓል።
ሕዝቡ ከዚህ ሁሉ መከራ ለመገላገል ባደረገው ትግል ይህን እኩይ ኃይል አሽቀንጥሮ በመጣል፣ መቀሌ ተጠቅልሎ እንዲመሽግ አድርጎታል። ህወሓት ሥልጣኔን ተነጠቅኩ፣ ሀገሪቱም ከኔ ቁጥጥር ውጭ ሆነች በማለት ወደ ሥልጣን ለመመለስ በሀገሪቱ ውስጥ ብጥብጥና መተላለቅ እንዲስፋፋ እስካሁን እኩይ ተግባሩን በመፈጸም ላይ ነበር።
ህወሓት ወደ ሥልጣን ያደርሰኛል ብሎ ያቀደውን ተግባራዊ ለማድረግ የሰሜን ዕዝ አባላት አገር ሰላም ነው ብለው በተኙበት ኢ-ሰብዓዊ እርምጃ ወሰደባቸው። ይህ እኩይ ተግባር ዝም ተብሎ የሚታለፍ አልሆነም። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከሠራዊቱ የበላይ አመራር ጋር በመምከር ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲወሰድ ወሰኑ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ የህወሓትን ልዩ ኃይል በማጥቃት ትግራይን ለመቆጣጠር ቻለ።
መከላከያ ሠራዊታችን በአሁኑ ሰዓት እያደረገ ያለው ውጊያ ሕግ የማስከበር እርምጃ በመሆኑ እንደግፋለን፣ ያስመዘገበው ድልም ሀገርንና ዜጎችን የሚያኮራ ነው። ህወሓት ከምሥረታው ጀምሮ ለሀገርና ለሕዝብ፣ ብሎም ለሰው ሕይወት ግድ የሌለው ድርጅት በመሆኑ እስካሁን በአገራችን ላይ ያደርሰውን ግፍና በደል ማንነቱን እጅግ ግልጽ ያደርገዋል። መከላከያ ሠራዊታችን ይህንን ጨካኝና ግፈኛ ቡድን ወደ ሕግ ለማቅረብ ያደረገውን መስዋዕትነት ኢሕአፓ ያደንቃል፣ ኮርተንባችኋልም። በጦር ኃይል የተገኘው ድል ጠንካራ መሠረት እንዲኖረውና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ለማድረግ የተደበቀውን ግፈኛ ቡድን እያደኑ ለፍርድ የማቅረብ ሂደቱ መቀጠል ይኖርበታል።
የግፈኛው ቡድን አባላት እጃቸው ከተያዘ በኋላ ቀጣዩ ሥራ እስካሁን ድረስ የበጣጠሷቸውን የኤኮኖሚ አውታሮች መለሶ መገንባትና ሕዝቡን ማረጋጋት ትልቁ ሥራ ይሆናል። ኢሕአፓም በሚችለው ሁሉ የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ ይወዳል።
በመጨረሻም ሳምሪ የተባለው የነብሰገዳዮች ስብስብ በስደተኛ መልክ ሱዳን በሚገኘው የስደተኛ ጣቢያ መጠራቀማቸውን እየሰማን ነው። ይህን ወንጀለኛ ቡድን፣ ከሱዳን መንግሥት ጋር በመተባበር በአስቸኳይ ወደ አገር እንዲመለሱና ሕግ ፊት እንዲቀርቡ እንዲደረግ ኢሕአፓ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድማማችነት፣ በሰላም፣ በፍቅር ለዘለዓለም ይኖራል!
ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ
ስልክ/Phone: +251 944 223 216