December 4, 2020

“እንደሀገር የተጀመረው የህግ የበላይነት መከበር የሚጠናቀቀው ትህነግ በሽብርተኝነት ሲፈረጅ ብቻ ነው” የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አለኸኝ አቶ አብርሃም አለኸኝ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ይህን መልዕክት አስፍረዋል።

“ትህነግን በሽብርተኝነት አምና ያልተቀበለች ሀገር ሽብርተኛንም ሆነ ሽብርተኝነትን የመቃወም የህግም ሆነ የሞራል ብቃት የላትም። ትህነግ አስተሳሰቡም፣ አርማውም፣ መላ መዋቅሩም በመላው አለም ጥቅም ላይ መዋል የለበትም።

በወያኔ ትህነግ ስም የተመዘገበ ማንኛውም ንብረት ምንጩ ዘረፋ ስለሆነ ተወርሶ ለኢትዮጵያ ህዝብ ገቢ መሆን አለበት።

በአለም ታሪክ የወያኔ ትህነግን ያህል በሰብአዊነት ላይ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች አሉ ከተባለ ሁሉም በአሸባሪነት ተፈርጀዋል።

ስለሆነም ትህነግን አሸባሪ ብላ ያልፈረጀች ሀገር ለዜጎች ክብር ፣ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ሁለንተናዊ ደኅንነትና ለሀገር ሉዓላዊነት ደንታ ቢስ ስለሚያደርጋት በራሷ ፈቃድ ታሪካዊ ነፃነቷ እንዲገረሰስና ክብሯ እንዲደፈር ፈቅዳለች ማለት ነው።

ትህነግን ሽብርተኛ ብሎ ያልፈረጀ ሀገርና ህዝብ ለህግ የበላይነት መከበር የተከፈለውን ሁሉንም መስዋዕትነት ፈቅዶ ዝቅ እንዳደረገው (እውቅናና ክብር እንደነፈገው) ይቆጠራል።

እንደሀገር የተጀመረው የህግ የበላይነት መከበር የሚጠናቀቀው ትህነግ በሽብርተኝነት ሲፈረጅ ብቻ ነው። ይህ ባልሆነበት ነባራዊ ሁኔታ በግፍ የተከፈተብን ጦርነትና የዘር ጭፍጨፋ እንዳልተጠናቀቀ ይቆጠራል” ብለዋል።

(አብመድ)