አዲ አረጋ ቂጤሳ
የመንግስት የአስተዳደር ስርዓት ቅርጽን በተመለከተ የተለያዩ እይታዎች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል አሃዳዊ አስተዳደር ስርዓት፣ መልክዓ ምድራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት እና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሃዳዊ የአስተዳደር ስርዓትን የሚያቀነቅኑ ሀይሎች፣ ይህ የአስተዳደር ዘይቤ የሀገር አንድነትን ለማስጠበቅ ሁነኛ መንገድ ነዉ ብለዉ ያምናሉ፡፡ በአንጻሩ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓትን ከፋፋይ፣ ለሀገር አንድነት ጠንቅ ነዉ ብለዉ ይወስዳሉ፡፡ መልክዓ ምድር ፌዴራሊዝምን የሚያቀነቀቅኑ ሀይሎችም ሁኔታዎችን የሚያዩበትና የሚተነትኑበት መነጽር ከአሃዳዊያን ሃይሎች ምንም ልዩነት የለዉም፡፡ አሃዳዊ እና መልክኣ ምድር ፌዴራሊዝም የአስተዳደር ዘይቤዎች በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ የሚያስኬዱ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ሀይሎች በታሪክ ለነበሩት የብሄር ጭቆናዎች ዕዉቅና አይሰጡም፡፡ ብዝሃትን ለማስተናገድም ዝግጁነት የላቸዉም፡፡ ስለሆነም እነዚህን የአስተዳደር ዘይቤዎች ወስዶ ለመተግበር መሞከር ሀገራችንን ወደ አላስፈላጊ የግጭት አዙሪት ዉስጥ መክተት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
እንደ ብልጽግና ፓርቲ ሀቀኛ እና እዉነተኛ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ለሀገራችን የተሻለዉ አማራጭ ነዉ ብለን እናምናለን፡፡ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ግንባታ ሂደታችን ያካበትናቸዉን ጠንካራ ጎኖች በማስቀጠል ያሉ ድክመቶችን አርመን በእኩልነት በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተች ጠንካራ አንድነት ያላት እና በለጸገች ሀገር እዉን ለማድረግ እንታገላለን፡፡ ሀቀኛ ፌዴራሊዝምን ለመገንባት እስካሁን የነበሩ ችግሮች አርመን ወደ ፊት እንራመዳለን ስንል፣ የፓርቲ ሪፎርም በማድረግ በአግላይ የነበረዉን የኢህአዴግ አደረጃጀት አካታች እና ሁሉን አቀፍ በሆነዉ የብልጽግና አደረጃጀት በመተካት በሀገር ጉዳይ ሁሉንም አሳታፊና ዉሳኔ ሰጪ እንዲሆን የጀመርነዉን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን ማለት ነዉ፡፡ እስካሁን የነበሩ ችግሮችን እንፈታለን ስንል በሀገር ደረጃ ብዝሃ ልሳንነት በማረጋገጥ አምስት ቋንቋዎች የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ እንሰራለን ማለት ነዉ፡፡ ከዚህ በፊት የነበረዉን የብሄር ማንነት ጽንፍ ላይ የመንጠልጠል አዝማሚያዎችን በማረም የብሄር ማንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነት ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ፣ በብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መካከል ወንድማማችነት እኩልነት እና የነጻነት እሴቶች እንዲጠናከሩ እንሰራለን ማለት ነዉ፡፡
እስካሁን የነበሩ ችግሮችን እንፈታለን ስንል በጁንታዉ ተዘርግቶ የነበረዉን በክልሎች እስከ የሞግዚት አስተዳደር ደርሶ የነበረዉን ጣልቃ ገብነት አስቀርተን የህዝቦችን ትክክለኛ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እናረጋግጣለን ማለት ነዉ፡፡ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ሲደርሱ የነበሩ ጥሰቶችን አርመን የሰዉ ልጆች መብቶች የተከበሩባት፣ ፍትህ የሰፈነባት፣ ብዝሃነት ጌጥ የሆነባት የበለጸገች ኢትዮጵያን እንገነባለን ማለት ነዉ፡፡ እስካሁን የነበሩ ችግሮችን እንፈታለን የአስተዳደር ወሰን፣ የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ህግን ተከትለዉ ፍትሃዊ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ሀቀኛ ፌዴራሊዝም እንገነባለን ማለት ነዉ፡፡