December 7, 2020

“ጁንታው የትግራይን ህዝብ መውጪያ መግቢያ ከማሳጣት ባለፈ የጠቀመው ነገር እንደሌለ ጠንቅቆ ያውቃል”– ዶክተር አረጋዊ በርሄ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር

*************************

(ኢ ፕ ድ)

ጁንታው የትግራይን ህዝብ እግር በእግር እየተከታተለ መውጪያ መግቢያ ከማሳጣት ባለፈ የጠቀመው ነገር እንደሌለ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አስታወቁ።

ሊቀመንበሩ ዶክተር አረጋዊ በርሄ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት ፣ ጁንታው እስከ አሁን ህዝቡ በድርጅቱ ቁጥጥር ስር አድርጎ እያንዳንዷን እንቅስቃሴውን እየተቆጣጠረ መውጪያ መግቢያ አሳጥቶ ነው የኖረው ። አሁን ግን የተጎናጸፈውን ድል በመጠቀምና ነጻነቱን በአግባቡ በማጣጣም የመንግሥትን እገዛ ተጠቅሞ እራሱን ወደልማት ያስገባል።

የትግራይ ህዝብን በኢኮኖሚ በፖለቲካ ተጠቃሚ አደርጋለሁ ሲባል መጀመሪያ ሊመጣ የሚገባው ነገር ህዝቡን ማስቻል፤ መብቱን መጠበቅ፤ ተደራጅቶ እንዲንቀሳቀስ ማመቻቸት ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ ፣ ይህ ከሆነለት በአጭር ጊዜ ውስጥ በራሱ መንገድ ኑሮውን በማሻሻል መሰረታዊ ለውጥ ማምጣጥ እንደሚችል አስታውቀዋል።

መንግሥት መሰረተ ልማቶችን በማሟላት፤ ለወጣቱ የሥራ እድል በመፍጠር በተለይም ደግሞ የጀመረውን ህግን የማስከበር ሥራ በመላ አገሪቱ በማድረግ የትግራይም ወጣት ሌላ ክልል ሄዶ በነጻነት እንዲሰራ በማመቻቸት በኩል ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ጁንታው ለትግራይ ህዝብ የማያስብ መሆኑን በዚህ ጦርነት እንኳን እራሱን ለማትረፍ ሲል በህዝብና በመንግሥት መሰረተ ልምቶች ላይ ያደረሰውን ውድመትን ማየት ይቻላል ያሉት ዶክተር አረጋዊ፣ የአክሱም የአየር ማረፊያን ጨምሮ ሌሎች በርካታ መሰረተ ልማቶችን አውድሞ መሄዱን አመልክተዋል ።

ጊዜያዊ አስተዳደሩም እነዚህን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ከሚመለከታቸው ጋር በመሆኑ ወደቦታቸው መመለስ ይጠበቅበታል፤ እኛም ማህበራዊ መሰረታችን ትግራይ ክልል የሆንን ፓርቲዎች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በጋራ ለመስራት ባለን አቅም ሁሉ ተዘጋጅተናል ብለዋል ።በክልሉ ሥራውን የጀመረው ጊዜያዊ አስተዳደር የህዝቡን አስከፊ ህይወት ለመለወጥ እንደሚሰራ ተስፋ አለኝ ያሉት ዶክተር አረጋዊ፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ክልሉን እንደገና ለመገንባትና ከዚህ በፊትም አጥቶት የነበረውን መሰረተ ልምት ለማሟላት እንደ ፓርቲ ህዝቡን በማስተባበር ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችንም በማድረግ እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል።

የትግራይ ክልል ከዛሬ 46 ዓመት በፊት ጀምሮ በጦርነት እጅግ የተጎዳ አካባቢ ነው፤ ህዝቡም በእርዳታ ስንዴ የሚኖር የተስተካከለ የመጠጥ ውሃ እንኳን ያላገኘ ነው ያሉት ዳክተሩ፣ ጁንታው በስሙ እየነገደ የሚያጋብሰውን ሃብት ስለተመቸውና እራሱን አንደላቆ እንዲሁም ልጆቻቸውን እጅግ በተቀናጣ ምቾት ውስጥ ማኖር ስለቻሉ ብቻ ስለ ህዝቡ ደንታ ቢስ ሆነው መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

https://www.press.et/Ama/?p=36856