Image may contain: 1 person, text

* ገና የሕወሓት ግብአተ መሬቱ በወጉ ሳይፈጸም፣ … ጠባብ ብሔርተኞች ጩኸታቸውን ማሰማት ጀምረዋል።

***

ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ “የኀጢአተኛ ሞት ምንኛ መራራ ነው” ሲል የዘመረውን ለመረዳት፣ በሞት ጣር ላይ ካለው የሕወሓት ስንክሳር የተሻለ እማኝ የለም ማለት ይቻላል። ድርጅቱ ኢትዮጵያን በተቈጣጠረው በሠላሳ ዓመት ሕይወቱ የዘራውን የግፍ ፍሬ አሁን በማጨድ ላይ ይገኛል። ተረኛው ለመሆን እየዳዳ ካለ፣ ከዚህ ድርጅት የሕይወት ታሪክ ተምሮ ከአሁኑ መቈጠብ ካልቻለ፣ የሱም ዕጣ ፋንታ የተለየ እንደማይሆን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ መሆኑን ቢገነዘብ ይሻለዋል። ጉዞውም የሚቀጨው እንደሕወሓት የዕድሜ ባለፀጋ ሳይሆን ገና በእንጭጩ እንደሚሆን አያጠራጥርም።

ኢትዮጵያ ከሕወሓት በኋላ፣ የጐሣ ዕፀ ፋርስ ያሳበዳቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች መፈናጫና መቦረቂያ እንዳትሆን ተግቶ መጠበቅ የያንዳድንዱ አገርወዳድ ዐላፊነት እንደሆነ አያጠራጥርም። ከመነሻው በዚህ ሁሉ ጣጣ የከተተው የአገሪቷ መከላከያ ሠራዊት እንደሆነም መረሳት የለበትም። ኢትዮጵያን የጠባብ ጐሠኝነት አስተናገር ራሳቸውን ካዞራቸው ሕሙማን እጅ በቀላሉ ለመታደግ የሚቻለውም የዚህ ኀይል ጉልበት ቢታከልበት ነው ብል ስሕተት አይመስለኝም። ገና የሕወሓት ግብአተ መሬቱ በወጉ ሳይፈጸም፣ እነዚህ ጠባብ ብሔርተኞች ጩኸታቸውን ማሰማት ጀምረዋል። ዓላማቸውም ሕወሓትን ቀብረው ድርጅቱ በቀደደው ጐዳና ጉዟቸውን መቀጠል ይመስላል።

ሕወሓት ይዞ የመጣው ኮተት ለነዚህ የሥልጣን ጥመኞች ብርቃቸው እንደሆነ አይካድም። ስለዚህም ሕወሓት ከቀበራቸው ከጐሣ ጉድጓድ ወጥተው አውላውን የኢትዮጵያን ሜዳ ማየት ተስኗቸዋል።

ሕወሓት ብቅ ያለው ከሦስት ኮተት ጋር ነው። ክልል፣ ሕገመንግሥትና ባለኮከብ ሰንደቅ ዓላማ።

ሦስቱንም ተገን በማድረግ በሕወሓትና፣ ለእኩይ ዓላማው አስፈጻሚነት ሲል በፈጠረው ኢሕአዴግ፣ ለመስማት የሚቀፍ፣ ለማሰብ የሚሰቀጥጥ፣ ለማየት የሚያስበረግግ፣ ለመጻፍ የሚያስደነግጥ በሰው ኅሊና የማይታሰብ ግፍ ተሠርቷል። ሦስቱም እንድናስብ የሚያስገድዱን ይኸንን የማይካድ አሰቃቂና ዘግናኝ እውነታ ነው።

የኢሕአዴግ ሰንደቅ ዓላማ ከናዚዎቹ እስዋስቲካ ተለይቶ የሚታይበት ምክንያት አይታየኝም። የሕዝብ አንድነትና የአገር ልዕልና ማሳያ ሳይሆን፣ የክፋት ዐዘቅት ምልክት፣ የኢሰብኣዊ ጭካኔ ማስታወሻ ነው።

ሕዝቡ ለኻያ ሰባት ዓመት የተጋረጠው የግፍና የሰቈቃ፣ የእስራትና የግድያ ምልክት አርማ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክና ሰንደቅ ዓላማ በሕወሓት ተዋረደ እንጂ አልተጀመረም። ሕዝቡ ከአያቶቹ የወረሰውን፣ ከራሱና ከትውልድ አገሩ አልፎ በመሻገር የዓለም ግርማና ሞገስ የሆነውን ታሪካዊውና ድል አድራጊው ሰንደቅ ዓላማ በቅጽበት እንዲመለስለት መጠየቅ ይኖርበታል። አንድ ኢትዮጵያዊ ባለኮከቡን ሰንደቅዓላማ በእጁ እንዲይዝ መጠበቅ፣ አንድ አይሁድን የናዚን እስዋስቲካ እያውለበለብህ ሂድ ማለት ከሚያደርሰው ውርደትና ዝቅጠት አይተናነስም።

ፍትሕና ርትዕ፣ አንድነትና እኩልነት፣ ሰላምና ፍቅር የሚመኝ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ የአገሩ ነፃነትና መለዮ፣ የሕዝቡ አንድነትና ኩራት ምልክት ነው ብሎ በማመን ይኸንን ሰንደቅዓላማ በእጁ ከቶዉኑ ሊይዘው አይገባውም። ማንም ኅሊና ያለውና ግፍ የሚጠላ ባለሥልጣንም፣ ሳይውል ሳያድር፣ ለሕዝቡ ፍቅር፣ ለአገሩ ክብር ሲል ይኸንን ሰንደቅ ዓላማ አላንዳች ማመንታት እስከነአካቴው ሊያጠፋው ይገደዳል።

ከዚያ ባሻገር፣ የኢሕአዴግ ክልልም ሆነ፣ ሕገመንግሥት ሳይውሉ ሳያድሩ መወገድ ያለባቸው የሕወሓት ነውረኛ ቅርሶች ናቸው። ሦስቱም፣ ማለትም ባለኮከቡ ሰንደቅ ዓላማ፣ ክልልና ሕገመንግሥት፣ ሕወሓት ለዘር ማጽጃና ለዘረፋ ዓላማው ማስፈጸሚያ እንዲረዱት የሸረባቸው የወንጀል መሣርያዎቹ መሆናቸው አይካድም። ልክ የናዚ ተቋማትና ሥርዐት የድርጅቱን መገርደስ ተከትለው ከነአካቴአቸው እንደተደመሰሱ ሁሉ፣ የነዚህም መውደም አስፈላጊ የማይሆኑበት ምክንያት የለም። እውነት ነው ናዚ የሥርዐቱና የተግባሩ አድናቂዎች እንደነበሩለት ሁሉ፣ ሕወሓትም ኢሕአዴግም የራሳቸው እንደሚኖሩላቸው አይካድም።

እንደነዚህ ዐይነቶቹ ሰዎች፣ የፋርሱ ባለቅኔ ሳኢዲ እንዳለው፣ ለሌላው ሰው ሥቃይ ደንታ የሌላቸው፣ ሰው የሚል መጠርያ ከቶም የማይገባቸው ግለሰቦች ናቸው። ለነሱ ሲባል የሕወሓትን መዝገብ በማያፋልም ሁናቴ ላለመዝጋት መሞከር በድርጅቱ ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ ፋይዳው ምን እንደሆነ ለመጠየቅ ያስገድዳል።