ሁሌ እናስታውሳቸው

ተቀብሮ እንዳይቀር

አኩሪ ታሪካቸው!!!!!

ጀግናይቱ እናት ወ/ሮ በላይነሽ ለማ ማን ነበሩ???

ማሳሰብያ፤……የመጀመርያው ፎቶ ወ/ሮ በላይነሽ ለማ ልጆቻቸውን ገና በ ፋሺስት ደርግና በዘረኛው ወያኔ ሳይነጠቁ በፊት ሲሆን ሁለተኛው ፎቶ ግን በትግሉ ሂደት ወቅት ልጆቻቸውን እያጡና እየተጎሳቆሉ በነበረበት ወቅት ነው፤.…

የቅርብ የቤተሰብ አባል ወ/ሮ በላይነሽ ለማን እንዲህ ሲል ይገልፃቸዋል ”እትዬ ልጆችዋን ያለአጋር ብቻዋን እንደ አራስ ነብር በጥርሶቿ ነክሳ ከክፉ ነገር ተከላክላ፤ የሚያስፈልጋቸውን አሟልታ፤ አራቱንም ልጆቿን ለወግ ለማእረግ ያበቃች ጠንካራ ሰው ናት።”……ከዚያም ታሪኩን እንዲህ በማለት ይቀጥላል፤……

“ወ/ሮ በላይነሽ ለማ ከአባታቸው ከግራዝማች ለማ ገ/ህይወት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ገነት ኅ/ማርያም በትግራይ ክ/ ሀገር በአዲግራት አውራጃ በሰንቃጣ ወረዳ በ 1930 ዎቹ ተወለዱ።

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ መቀሌ አያታቸው ዘንድ በመቀመጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ እንደቆዩ ከትዳር አጋራቸው እና ውዱ ባለቤታቸው ሻምበል ግርማ ጥላሁን ጋር ተዋውቀው ከዚያም ተጋብተው አራት ውድና ብርቅዬ ልጆቻቸውን አፍርተዋል። እነሱም ናሁሰናይ፤ አዜብ፤ሶለሞንና አንተነህ ግርማ ጥላሁን ናቸው።

ውድ ባለቤታቸው ሻምበል ግርማ ጥላሁን የእግዚአብሄር ፍቃድ አልሆነምና ልጆቻቸው ገና ወጣቶች እያሉ በአጭር ጊዜ ህመም ከዚህ አለም በሞት ቢለዩም፤ሀዘናቸው ከባድና መራራ ቢሁንም፤ ልጆቻቸውን በመልካም ስነ ምግባርና ባህል አሳድገው፤ ለወግ ለመአረግ ለማብቃት ቆርጠው በመነሳት፤ እቅዳቸውን ከግብ ለማድረስ ጊዜና ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ ደክመዋል።

ወ/ሮ በላይነሽ ለምዝብሩና ለድሃው ሕዝብ በመቆርቆርና ለውጥ ለማምጣት ባላቸው ፅኑ ፍላጎት የተነሳ፤ ለድሀው ህዝብ ድምፅ ለመሆን፤ ለውጥ ሳይመጣ በፊት ፓርላማ ውስጥ ወንበር ይዘው የድሀውን ድምፅ ለማስተጋባት ብሎም ለውጥ ለማምጣት ለፓርላማ አባልነት አዲግራትን ወክለው ተወዳድረዋል፤ ሆኖም በ 1966 ዓ.ም አብዮቱ በመፈንዳቱ እቅዳቸው ግቡን ሳይመታ ቀረ።

በዚህም ጊዜ ነበር የበኩር ልጃቸው ናሁሰናይ ግርማ ጥላሁን የትምህርት እድል አግኝታ ወደ ሰሜን አሜሪካ ያቀናችው።የተቀሩት ልጆቻቸው፤ የራሷ ታላቅ ገድልና ታሪክ ያላት፤በዚሁ አምድ ከዚህ በፊት የተፃፈ እና በከተማ በትግሉ በፋሺስቱ ደርግ የተሰዋችው አዜብ ግርማ ጥላሁን፤ለምዝብር ህዝቦች አርነት በከተማም በገጠርም ትግል ውስጥ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለውና ኢሕአሠ ከወያኔ ጋር ባደረገው ውግያ የተሰዋው ሰለሞን ግርማ ጥላሁን እና ከወንድሞቹ ጋር በመሆን በኢሕአፓ ስር ተደራጅቶ በከተማም በገጠርም ትጥቅ ትግል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ፤በ ኢሕአሠ ውስጥም በታላላቅና አብይ የትጥቅ ትግል ተልዕኮዎች ታላላቅ ድልን ያስመዘገበና የጋንታ ምክትል መሪ የነበረ አንተነህ ግርማ ጥላሁን እዛው አዲስ አበባ ቀርተው፤ በኢሕአፓ ስር ተደራጅተው ህዝባዊ ትግሉን ተቀላቅለዋል።

ጀግናው አንተነህ ግርማ ከሌሎቹ የኢሕአፓ ጓዶቹ ጋር በመሆን፤ የደርግን ፋሺስታዊ ተልዕኮ አስፈፃሚ የሆነና ብዙ ወጣቾን ያስጨፈጨፈ አንድን ‘ግለሰብ” ለማጥቃት በተልዕኮ ላይ እንዳሉ፤ በአንጃዎች ጠቋሚነት ደርግ ደርሶበት፤ አንተነህና ጓዶቹ “ግለሰቡን” ይጠብቁበት የነበረው ቦታ ወታደሮች ደርሰው ጂፖች ላይ በተጠመዱ መትረየሶች ተኩስ ከፍተውባቸው፤ አንተነህ የያዛት መኪና በመትረየሱ ተኩስ ወንፊት እስከምትሆን ድረስ ብትደበደብም እስከተቻለውና እስከመጨረሻው ነድቷት ኋላም ሮጦ ማምለጥ ችሏል። ወታደሮቹ መኪናዋን ሲፈትሹ የአንተነህና የሶሎሞን ግርማን መንጃ ፍቃድ አግኝተው በቀጥታ ወደ ወንድማማቾቹ መኖርያ ቤት በመሄድና በሩን አጥሩን “በማክ” የወታደር መኪና ደርምሰው ገብተው ቤተሰቡን በጣም ካጎሳቆሉ በኋላ እናታቸውን ወ/ሮ በላይነሽን ይዘው ይኽውልሽ ሁለቱን ልጆችሽን ገለናቸዋል በማለት ያረዷቸዋል።እናታቸው ወ/ሮ በላይነሽም “ ፋሺስቶች! ፋሺስቶች! ልጆቼን ገደላችሁብኝ” እያሉ ሲጮኹና ሲራገሙ ሳለ ቆራጡ አንተነህ ግርማ ልብሱን ቀይሮና፤ ራሱን ቀይሮ፤ መንገዱንና ቤቱን ከበው ትዕይቱን ከሚመለከቱት ሰዎች መካከል በመደባለቅ ቀስ ብሎ ለእናቱ የተነገራት ዜና ውሸት እንደሆነና እሱም እዛው ከተመልካቾቹ መካከል ተመልካች መስሎ መቆሙን በሰው መልእክት ይልክባቸዋል።

ልጆቻቸው መኖራቸውን ካረጋገጡም በኋላ ወታደሮቹ ቤቱን ሲፈትሹና ሲመዘብሩ እስከሚሄዱ ድረስ ወ/ሮ በላይነሽ ላለማስነቃት ጩኽታቸውን አላቆሙም ነበር።ወታደሮቹ ለቀው እንደሄዱም ወድያውኑ ወ/ሮ በላይነሽ ልጆቻቸውን የሚደብቁበት የዘመድ ቤት አዘጋጅተው ለሳምንት ደብቀው አቆይተዋቸዋል።ከሳምንት በኋላም ሰሎሞንና አንተነህን የመጓጓዣ እቅድ በማዘጋጀት፤ ሁለቱን በተለያዩ አውቶቡሶች በማሳፈር እሳቸውም አብረው መቀሌ ድረስ ተጉዘዋል።

ከዚያም የትውልድ መንደራቸው ድረስ በመውሰድ ወላጆቻቸው ቤት አስቀምጠዋቸው፤ወድያውኑ አዲስ አበባ ተመልሰው፤ በከፍተኛ ደረጃ ይፈለግ የነበረውንና በተልዕኮውም ላይ ተሳታፊ የነበረውን የአጎታቸውን ልጅ ስለሺ ዘውዴ እና የሰሎሞን ጓደኛና በደርግ ስትፈለግ የነበረችውን ጓዲት ይዘው ወደ ሰንቃጣ ገብተዋል።

የኢሕአሠ ቤዝ የነበረው አሲምባም እዛው ወ/ሮ በላይነሽ የተወለዱበት መንደር ነበርና፤ ለጀግኖቹ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ግዜና ችግር አልነበረባቸውም፤ ተቀላቀሉ።ታድያ ወ/ሮ በላይነሽ ስለ ልጆቻቸው ደህንነት በየግዜው አሲምባ በመሄድ ይጠይቁ እንደነበርና፤ በሠራዊቱ አባላትም በተጠቀሰው ስም የሚያውቁት ግለሰብ እንደሌለ ይነገራቸው ነበር። የ ወ/ሮ በላይነሽ ቤተስብም ይሁኑ የአካባቢው ነዋሪ፤ ለሠራዊቱ ታላቅ ክብርና እንክብካቤ ያደርግ ነበር።ይኽውም ምግብና መጠት መጠለያን ጨምሮ በመለገስ ከ ኢሕአፓ ታጎዮች ጋር ይተባበሩ ነበር።ወ/ሮ በላይነሽ ለማም ለሠራዊቱ የተቻላቸውን ያህል አበርክተዋል።

በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ነበር ከባድና መራራ ዜና ስለጀግናዋ ሴት ልጃው አዜብ ግርማ በአንጃዎች ጥቆማ መያዝ ዜና የደረሳቸው። ታድያ አይበገሬና ጠንካራዋ እናት ወ/ሮ በላይነሽ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የልጃቸው የአዜብ ግርማን መያዝና በ 3ኛ ፖሊስ ጣብያ መታሰርና መሰቃየት ደርሰውበት የምትፈታበት ሁኔታ ቢያመቻቹም ሊሳካ ባለመቻሉ ከባድና መራራ መከራ ውስጥ ወድቀው ነበር።

ቀደም ሲል “ ሁሌ እናስታውሳቸው!” በሚለው በዚሁ አምድ በወጣው የአዜብ ግርማ ጥላሁንን የተመለከተው ፅሁፍ እንደተገለፀው፤ የደርግ ባለስልጣንና የቤተሰብ ቅርብ ወዳጅ የነበረ አንድ ኮለኔል አማካኝነት፤ አዜብ የደርግን ርዕዮተ አለም ከተቀበለችና ኢሕአፓን ካወገዘች፤ አባላቱን ካጋለጠች፤መሳርያና ንብረት የተደበቀበትን ቦታ ከመራች እንደምትፈታ ቢነገራትም “ ሞት ለፋሺስቶች! ሞት ለባንዳዎች! ኢሕአፓ ያቸንፋል! ሕዝባዊ መንግስት ይመሰረታል!” በማለት ከአላማዋ ፍንክች ሳትል በፋሺስቶች በግፍ ተገድላለች።

ወ/ሮ በላይነሽም ውዷና ምትክ የለሽ ብርቅዬ የጀግናይቱ ልጃቸውን በግፍ መገደል ከሰሙ በኋላ መራራ ሀዘን ውስጥ ወደቁ፤ አይበሉም አይጠጡም፤ከሰው አይቀላቀሉ፤ ሁሌ ማንባት፤ ማንባት፤ ፋሺስቶችን ማውገዝ ነበር የረጂም ጊዜ ድርጊታቸው።በዚህ መሀል አሲምባ የነበረው የኢሕአሠ ሠራዊት በካሀዲው የ ወያኔ ጦር ተጠቃ።የመረረ ጦርነትም ለ 3ት ቀናት ተካሂዶ ጀግኖቹ ሰሎሞን ግርማ ጥላሁንና ስለሺ ዘውዴ ጥላሁን ተሰዉ።ይሄም ሠራዊት በማፈግፈግ ጉዞ በ ኤርትራ አርነት ግዥ ምድር በማድረግ ወደ በጌምድር አቀና፤ እዛ ካለው ሠራዊት ጋር ተቀላቀለ።

ይህን ጊዜ ወ/ ሮ በላይነሽ ከአዲስ አበባ ወደ አሲምባ ጉዞ ጀመሩ።ሲደርሱም ሠራዊቱ ከሲምባ ቤዙን ለቆ ወደ በጌምድር መጓዙን ሰሙ።እሳቸውም የልጆቻቸውን ዜና ለማግኘት በጌምድር በመጓዝ ሰራዊት ያለበት ካምፕ በመሄድ፤ የሠራዊቱን አባላት የልጆቻቸውን ፎቶ በማሳዬት ደህንነታቸውን ይጠይቁ ነበር። ሆኖም የድርጅት ስነ ስርአት ጉዳይ ነውና አጥጋቢ መልስ ባያገኙም ተስፋ ባለመቁረጥ ጥረታቸውን በረሃ ለበረሃ በመንከራተት ቀጥለዋል።

ኋላም ሠራዊቱ ሲበተን አንተነህም ከጓዶቹ ጋር በመሆን ሱዳን ከገባ በኋላ ደህነቱን ገልጾ፤ ስለ ሰሎሞንና ስለሺ ግን እንደተሰዉ ዜናው ለ ወ/ሮ በላይነሽ ይደርሳቸዋል።

የሀዘን ሁሉ ሀዘን ደረሰባቸው፤ልጃቸውና ስለሺንም የማግኘት ተስፋቸው መነመነ፤ ከሰው መገናኘት ቀረ፤ እንዳነቡ እግዚአብሔርን እንደተማጸኑ ታመሙ።ከዛሬ ሁለት አመት በፊት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ መሬት ላይ ነበር የሚተኙት።

ወ/ሮ በላይነሽ ለማ መሳርያ ታጥቀው ውግያ ሜዳ መውጣት ነው የቀራቸው እንጂ፤ ለፓርቲውም ሆነ ለሠራዊቱ ያበረከቱት ብዙ አስተዋጽኦ ያለ ቢሆንም በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ማጠቃለል አልተቻለም።

ብዙ እናቶች በትግሉ ውስጥ በመሳተፍ፤ በፓርቲውም በመታቀፍ፤ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።ከነዚህም አንዷና ዋነኛዋ የነበሩት ወ/ሮ በላይነሽ ለማ ናቸው።

ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን! ጀግና ቢሞትም ታሪኩ ህያው ነው።

”ማሳሰብያ፤……የ ወ/ሮ በላይነሽ ለማ ታሪክ ሆነ የጀግኖች ልጆቿ የትግል ታሪክ፤ በህይወት ከተረፈው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ አንተነህ ግርማ ጥላሁን ሰፋ ባለ ሁኔታ ለአንባቢያን እንደሚደርስ ከፍተኛ ተስፋ አለን።

ክብር ከፋሺስቶች ጋር ሲታገል ግንባሩን ለጥይት እየሰጠ በጀግንነት ለተሰዋ አይበገሬ ትውልድ።