9 ታህሳስ 2020ተሻሽሏል ከ 1 ሰአት በፊት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ የሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ ገብተዋል።
ይህ ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ሠራዊት በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን ይፋ ካደረጉ በኋላ የሚደረግ የመጀመሪያው የውጪ አገር ጉብኝታቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀዳሚነት ያቀኑት ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ሳይሆን ሁለቱን አገራት ወደምታዋስነው የድንበር ከተማ ሞያሌ ነበር። እዚያም የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በዚህ ጉብኝት ሁለቱ መሪዎች አገሮቻቸውን ያስተሳስራሉ ከተባሉት ታላላቅ ፕሮጀክቶች መካከል የተጠናቀቁትን የሚመርቁ ሲሆን በግንባታ ላይ ያሉትን ደግሞ ይጎበኛሉ።
ይህም በድንበራቸው ሞያሌ ላይ ያለውን የድንበር መተላለፊያ እና አዲሱን የላሙን ወደብ ይጨምራል። በተለይ ‘ላፕሴት’ በመባል በእንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል የሚጠራው በውስጡ በርካታ ዕቅዶችን ያቀፈው የላሙ ወደብ ፕሮጀክት በጉብኝቱ ሰፊውን ቦታ ይይዛል።
ይህ የላሙ ወደብ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ኬንያን ብቻ የሚያስተሳስር ሳይሆን ደቡብ ሱዳንንም ያካተተ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ ይነገራል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያ ወቅታዊውን ሁኔታ ለማስረዳት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት በተጓዙበት ወቅት ወደ ናይሮቢ በመምጣት ከፕሬዝዳንቱ ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ አገራት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን መሪዎቹም በተደጋጋሚ ሲገናኙ ቆይተዋል፤ የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ከዚሁ ጋር የሚገናኝ ሲሆን ከወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ወሳኝ ጊዜ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለቱን አገራት በሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎች በሚኖሩ ማኅበረሰቦች መካከል በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች የሚያጋጥሙ እንደሆነ ይታወቃል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት በድንበር አካባቢ ካሉ ታጣቂዎች ጋር ውጊያ አካሂዶ እንደነበር ይታወሳል። በዚህም ሠራዊቱ ወደ ኬንያ ድንበር ዘልቆ በመግባት ቢያንስ 10 ኬንያዉያንን ይዘው መውሰዳቸው ተነግሯል።
ሁለቱ መሪዎች በሚያደርጉት ውይይት በድንበር አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙ ግጭቶችን በተመለከተ ከሚመካከሩባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ይሆናል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከዛሬ ጀምሮ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ለመድረግ ወደ ኬንያ እንደሚገቡ የተገለጸ ሲሆን፤ በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ እና ኬንያን የሚወሰኑበትን የሞያሌና የላሙ ወደብን ይጎበኛሉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በጉበኝታቸው ከኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በመሆን የሞያሌን የድንበር መተላለፊያን በር የሚከፍቱ መሆኑ ተነገረ ሲሆን፤ በተጨማሪም የሁለቱ አገራት መሪዎች በላሙ ግዛት ግዙፉን ‘ላፕሴት’ ፕሮጄክትን ይጎበኛሉ።
‘ላፕሴት’ ፕሮጀክት ምንድነው?
ላፕሴት (LAPSSET) የተባለው ፕሮጀክት የሚለው ምህጻረ ቃል የላሙ ወደብ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ የትራንስፖርት መተላለፊን ሚወክል ነው።
የላፕሴት ፕሮጀክት ይፋዊ ድረ-ገጽ እንደሚያመለክተው ግዙፉ ፕሮጀክት የኬንያ፣ የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ፕሮጀክት ነው። ፕሮጅክቱ ሦስቱን አገራት እርስ በእርስ የሚያስተሳስር ሲሆን ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጋርም የሚያገናኛቸው ነው።
ግዙፉ ላፕሴት ፕሮጀክት በውስጡ 7 ፕሮጀክቶችን አቅፏል። እነዚህም የወደብ ግንባታ፣ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ ሁለት የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ዝርጋታ ፕሮጀክቶች፣ የአየር ማረፊያ ግንባታ እና የሪዞርት ከተሞች ግንባታን ያቀፈ ነው።
1. የአውራ ጎዳናዎች ግንባታ
ይህ ፕሮጀክት የኬንያ የወደብ ከተማ ላሙን ከወደብ አልባዎቹ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ኢትዮጵያን እና ደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኝ ነው።
በፕሮጀክቱ የሚገነባው መንገድ ከኬንያዋ ላሙ ወደብ ተነስቶ-ኢሲኦሎ የሚደርስ ሲሆን፤ ኢሲኦሎ (ኬንያ) – አዲስ አበባ እንዲሁም ከኢሲኡሎ – ጁባ (ደቡብ ሱዳን) የሚያገናኝ ፕሮጀክት ነው።
በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ የሚገነቡት መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፤
- ላሙ ወደብ – ዊቱ ጋሪሰን (ኬንያ) 113 ኪ.ሜትር የሚረዝም
- ላሙ ወደብ- ጋሪሳ- ኢሲኦሎ (ኬንያ) 530 ኪ.ሜትር የሚረዝም
- ኢሲኦሎ – ሞያሌ – ሐዋሳ (ከኬንያ-ኢትዮጵያ) 505 ኪ.ሜትር የሚረዝም
- ኢሲኦሎ – ሎኪቻር – ናዳፓለ – ቶሪት – ጁባ (ከኬንያ-ደቡብ ሱዳን) 700 ኪ.ሜትር የሚረዝም
ላሙ ወደብ – ዊቱ ጋሪሰን መንገድ ግንባታ 60 በመቶ ተጠናቋል። ኢሲኦሎ – ሞያሌ – ሐዋሳ መንገድ ግንባታ ተጠናቋል።
ከላሙ ወደብ – ጋሪሳ – ኢሲኦሎ የሚወስደው መንገድ ዲዛይን በአፍሪካ ልማት ባንክ ወጪ የተጠናቀቀ ሲሆን ኢሲኦሎ – ሎኪቻር – ናዳፓለ – ቶሪት – ጁባ መንገድ ደግሞ የኬንያ እና ደቡብ ሱዳን መንግሥታት ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን በቅርቡ የአዋጭነት ጥናት አካሂደዋል።
ሎኪቻር – ናዳፓለ ያለውን መንገድ ለመገንባታ የዓለም ባንክ 500 ሚሊዮን ዶላር ፈቅዷል።
![የባቡር መስመር [ፎቶ ፋይል]](https://i0.wp.com/ichef.bbci.co.uk/news/800/cpsprodpb/357C/production/_115929631_mediaitem115929630.jpg?w=800&ssl=1)
2. የባቡር መስመር ዝርጋታ
ይህ የባቡር መስመር ዝርጋት የሦስቱን አገራት መዲናዎችን የሚያገናኝ ነው።
የባቡር መስመሩ ከላሙ ወደብ ኢሲኦሎ፣ ከኢሲኦሎ አዲስ አበባ፣ ከኢሲኦሎ ጁባ እንዲሁም ከኢሲኦሎ ናይሮቢ ይዘረጋል።
የባቡር ዝርጋታው ወጪም ከ7 ቢሊየን ዶላር በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል የሚዘረጋው የባቡር መስመር ቅዳሚ ዲዛይን ተጠናቋል። የሁለቱ አገራት መንግሥታትም በላፕሴት ፕሮጀክት ውስጥ የተካተተውን ይህን ፕሮጀክት በጋራ ለማልማት ከሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ከ700 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝመውን አዲስ አበባ – ጅቡቲ የባቡር መስመር የዘረጋው የቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሸን (ሲሲሲሲ) በላፕሴት ፕሮጅከት ውስጥ በኬንያ በኩል ያለውን የባቡር ዝርጋ የአዋጭነት ጥናት እና ዝርዝር የዲዛይን ሥራ እንደሚያከናውን ተጠቅሷል።
3. የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ዝርጋታ
ሁለት አይነት የነዳጅ ማስተላለፉያ ቱቦዎች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል። እነዚህም የድፍድፍ ነዳጅ እና የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ናቸው።
ድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ያልተጣራውን ነዳጅ ወደ ማጣሪያ የሚወስድ ሲሆን የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ደግሞ ምርት ወደ ገበያ የሚያስተላልፍ ነው።
የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ከሎኪቻር – ወደ ላሙ ወደብ (ኬንያ) የሚዘረጋ ነው።
በሌላ በኩል የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ በላፕሴት ከታቀፉ 7 ፕሮጀክቶች ውስጥ ከታተካተቱት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ነው።
ይህ ፕሮጀክት ከላሙ ወደብ – ኢሲኦሎ – ሞያሌ – ሐዋሳ – አዲስ አበባ የሚዘልቅ ነው። 790 ኪሎ ሜትር ያህልም ይረዝማል።
ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በደቡብ ኢትዮጵያ ያለውን የነዳጅ ምርት ፍላጎት ለማሟላት የሚሰራ ይሆናል።
ከላሙ ወደብ – ኢሲኦሎ-ሞያሌ – ሐዋሳ – አዲስ አበባ የሚዘረጋው የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ፕሮጀክት ዝርጋታ የጸደቀው በኬንያ መንግሥት እአአ 2016 ላይ ነበር።
ከዚያም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ድርድሮች ከተካሄዱ በኋላ በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈርሟል።

4. ላሙ ወደብ
ይህ ወደብ የሚገነባው በኬንያዋ ላሙ ግዛት ውስጥ ሲሆን 32 መርከቦች በተመሳሳይ ሰዓት መልህቃቸውን እንዲጥሉ የሚያስችል ነው።
የዚህ ወደብ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት መርከብ ማረፊያዎች ግንባታ ወጪ በኬንያ መንግሥት የሚሸፍን ይሆናል ተብሏል።
የመጀመሪያው መርከብ ማቆሚያ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛው እና ሦስተኛዎቹ የመርከብ ማቆሚያዎች ግንባታ ደግሞ በቀጣይ ወራት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይገመታል።
ይህንንም ተከትሎ የላሙ ወደብን ወደ ሥራ ለማስገባ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
5. የአየር ማረፊያዎች ግንባታ
በላፕሴት ፕሮጄክት ውስጥ ከተያዙት ፕሮጄክቶች መካከል የሦስት አየር ማረፊያዎች ግንባታ ይገኝበታል።
ሦስቱም አየር ማረፊያዎች በኬንያ ላሙ እና ቱርካና ግዛት እንዲሁም በኢሲኦሎ ከተማ የሚገነቡ ናቸው።
የእነዚህ አየር ማረፊያዎች ግንባታም እያንዳንዳቸው ከ143 እስከ 188 ሚሊዮን ዶላር የሚያስወጡ ይሆናሉ።
6. ሪዞርት ከተሞች ግንባታ
የላፕሴት ፕሮጄክት ሌላው አካል የሦስት መዝናኛ ከተሞች ግንባታ ነው።
የሪዞርት ከተሞቹ በኬንያዎቹ ላሙ፣ ኢሲኦሎ እና ቱርካና ሐይቅ ላይ የሚገነቡ ናቸው። ወጪያቸውም እንደ የቅድመ ተከተላቸው 970፣ 200 እና 42 ሚሊዮን ዶላር ወጪን ይጠይቃል ተብሏል።
የኬንያ መንግሥት ከተሞቹ በሚገነቡባቸው ስፍራዎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ካጠናቀቀ በኋላ፤ የከተሞቹ ግንባታ የሚከናወነው በግል ኢንቨስተሮች ይሆናል።
በአሁኑ ሰዓት የላሙ ሪዞርት ከተማ ማስተር ፕላን ዝግጅት እየተካሄደ ይገኛል።