12 ታህሳስ 2020

ስደተኞች

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም በትግራይ ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ በኋላ በክልሉ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ሁኔታ እንዳሳሰበው ገለጸ።

ድርጅቱ እነዳለው ኤርትራውያን ስደተኞች መገደላቸውን እንዲሁም በግድ ታፍነው ወደ ኤርትራ እየተወሰዱ እንደሆ የሚያሳዩ ሪፖርቶች እጅግ እንዳሳሰበው አስታውቋል።

የተመድ የስደተኞች ክንፍ ኃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ እንዳሉት፤ ስደተኞቹን እንዳጋጠሙ የተጠቀሱት ድርጊዎች ተፈጽመው ከሆነ ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ትግራይ ውስጥ ወደሚገኙ አራት የስደተኞች መጠለያዎች መግባት መቻል እንዳለበት አመልክተው፤ ስደተኞቹ ያለፍላጎታቸው በግድ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ መደረጉ ተቀባይነት የለውም ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት መከላከያ ሠራዊቱ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው አብቅተወል ቢልም፤ የህወሓት ኃይሎች ውጊያው በተለያዩ ግንባሮች መቀጠሉን ተናግረዋል።

አርብ ዕለት ኤርትራውያን ስደተኞችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳለው የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ምንም አይነት ስጋትን የሚደቅን እንዳልሆነ አመልክቶ፤ ነገር ግን በተሳሳተ መረጃ ሳቢያ ከካምፖቻቸው ወጥተው ወደ አዲስ አበባ የሄዱ ስደተኞች እንዳሉ ገልጿል።

ጨምሮም በትግራይ ክልል ከሚገኑ የስደተኞች መጠለያዎች ወደ አዲስ አበባ የሄዱ ስደተኞችን እየመለሰ እንደሆነም አስታውቋል።

ትግራይ በሚገኙ የስደተኛ ማቆያዎች ካምፖች ውስጥ በአገራቸው ፖለቲካዊ እስርና አስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን የሸሹ ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ይነገራል።

መንግሥት ባወጣው መግለጫ፤ “በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸውና ትክክለኛ መረጃ ያላገኙ ስደተኞች በሕገ ወጥ መንገድ ከማቆያ ካምፖቹ እየወጡ ነው። መንግሥት እነዚህን ስደተኞች ወደ የካምፖቻቸው እየመለሰ ነው” ብሏል።

መንግሥት ለስደተኞቹ የሚሆን ምግብ አቅርቦት ወደ ካምፖቹ እየላከ መሆኑንም አመልክቷል።

ይህንንም ተከትሎ ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ አዲስ አበባ ካሉ ኤርትራውያን ስደተኞች “በፍርሀት የተሞላ” የስልክ ጥሪ ደርሶኛል ብሏል።

ለስደተኞቹ ስጋት ዋነኛው ምክንያት በአውቶብስ ወደ ትግራይ እንደሚወሰዱ ቢነገራቸውም ካለፍላጎታቸው ወደ ኤርትራ እንወሰዳለን ብለው እንደሚፈሩ ተናግረዋል።

አንዲት ኤርትራዊት እንዳለችው፤ “ኤርትራ የኢትዮጵያን መከላከያ እንዲያግዙ ወታደሯቿን በመላኳ፤ የትግራይ ተወላጆች ኤርትራውያኑ ስደተኞች ላይ ተቆጥተዋል።”

ስደተኛዋ ለሮይተርስ እንደተናገረችው፤ “አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ባለቤቴን ደብድበውታል። አገራችሁ መጥታ እየወጋችን ነው ይሉናል። እኛም እንገድላችኋለን ሲሉን ፈራን” ማለቷን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

አሜሪካ፤ የኤርትራ ኃይሎች ትግራይ ገብተዋል የሚል መረጃ ብታወጣም፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለውታል።

ፊሊፖ ግራንዲ እንዳሉት፤ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) እና አጋሮቹ አራቱ በትግራይ የሚገኙ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ መግባት አልቻሉም። “ይሄ የስደተኞቹን ደኅንነት እና ህልውና ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይከታል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም “ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ኤርትራውያን ስደተኞች እየተገደሉ፣ በግድ ታፍነው ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ እየተደረጉም እንደሆነ የሚያሳዩ አሳሳቢ ሪፖርቶች ደርሰውናል። እነዚህ ሪፖርቶች ከተረጋገጡ ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኞችን የመጠበቅና ዓለም አቀፍ ሕግን የማክበር ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።

ከሁለት ዓመታት በላይ በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የዘለቀው ፍጥጫ በትግራይ ክልል ምርጫ መደረጉን ተከትሎ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ. ም የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸው ይታወሳል።

ከሦስት ሳምንት ግጭት በኋላ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በመንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ስር እንደገባችና ወታደራዊ ዘመቻው እንዳበቃ መገለጹ አይዘነጋም።

የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ተቋማት መንግሥት ለስደተኛ ካምፖችና የመሠረታዊ እርዳታ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ለማድረስ ነጻ የእንቅስቃሴ ፈቃድ ሲተይቁ የቆዩ ሲሆን፤ ለዚህም ተባበሩት መንግሥታት ከመንግሥት ጋር ከስምምነት መድረሱ ይታወቃል።