የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፓሊስ ከህጋዊ የስልጣን ወሰኑ ውጪ ያለምንም የፍርድ ቤት ትእዛዝ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ በር ላይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትን ለማሰር መሞከሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የሚያሰናክል እና አሳሳቢም ከመሆኑም በላይ የህገመንግስታዊውን የቦርዱን ተቋማዊ ሃላፊነት እና ስልጣን ንቀትን ማሳየት ጭምር ነው።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጪው ምርጫ የሚካሄድበትን አውድ ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት የሚመለከታቸው አካላት ሊያግዙት ይገባል!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመጪው ምርጫ ዝግጅት በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚነሱ አቤቱታዎችን በማሰባሰብ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት ሲደርግ እንደነበር ይታወቃል። ከነዚህም ጥረቶች መካከል የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትን ለአቤቱታዎቹ ምላሽ እንዲሰጡ ማድረግ፣ ምላሽ ላልተሰጠባቸው አቤቱታዎች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት ጥረቶችን አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ በፓርቲዎች እና ከመንግስት ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በማጠናቀር ያቀረበ ሲሆን ይህንን መሰረት አድርጎ ፓርቲዎች፣ ገዥው ፓርቲ እና ቦርዱ በጋራ በመገኘት ችግሮችን የሚፈቱበት የሶስትዮሽ ችግሮችን እና አቤቱታዎችን የሚፈታ አሰራር እንዲቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት የመጀመሪያው የሶስትዮሽ ውይይት ትላንትና ታህሳስ 02 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቢሮ የተከናወነ ሲሆን የቤኒሻንጉል ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ እንዲሁም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገኝተዋል። በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የመንቀሳቀስ የአባላት እስር እና ሌሎች ችግሮች የተነሱ ሲሆን፣ በገዥው ፓርቲ በኩል የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ሆነው በወንጀል እና በትጥቅ ትግል መሳተፍ ችግሮች አሉ የሚል አቤቱታ ቀርቧል፡፡ በውይይቱ ማጠቃለያም በክልሉ ውስጥ ያለውን የፓርቲዎች ችግር ለመፍታት ቦርዱን ጨምሮ ሁሉም አካላት የሚሳተፉበት ቡድን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል በመሄድ ለማጣራት ስምምነት ተደርጎ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
ነገር ግን ውይይቱ ተጠናቆ በቤንሻንጉል ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት የምርጫ ቦርድ ዋና መስሪያ ቤት ጊቢን ለቅቀው ለመውጣት ሲሞክሩ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፓሊስ አባላት የእስር ሙከራ አድርገውባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህ ገንቢ እና ችግሮችን ለመፍታት ተስፋ ሰጪ አቅጣጫ ከነበረው በተቃራኒ በተከናወነው እርምጃ ከፍተኛ ቅሬታ ተሰምቶታል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፓሊስ ከህጋዊ የስልጣን ወሰኑ ውጪ ያለምንም የፍርድ ቤት ትእዛዝ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ በር ላይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትን ለማሰር መሞከሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የሚያሰናክል እና አሳሳቢም ከመሆኑም በላይ የህገመንግስታዊውን የቦርዱን ተቋማዊ ሃላፊነት እና ስልጣን ንቀትን ማሳየት ጭምር ነው፡፡
ቦርዱ ችግሩን ለመፍታት ከሰአታት ጥረት በማድረግ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን እና ከፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን በተገኘ እገዛ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፓሊስ ሃይል ከምርጫ ቦርዱ ዋና መስሪያ ቤት በር ላይ ከ3 ሰአት ቆይታ በኋላ አንዲነሳ ለማድረግ ቢቻልም የተከናወነው የህግ ጥሰት እና ተቋማዊ ስልጣንን አለማክበር እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቀጣዩ ምርጫን ተከትሎ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግስት በመዋቅሮቹ የስነስርአት ደንብ አክብረው እንደሚንቀሳቀሱ በይፋ ያረጋገጡትን የሚቃረን በመሆኑ መስተካከል የሚገባው መሆኑን ያምናል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው አቤቱታዎች ላይ የሚደረገው የሶስትዮሽ ችግሮችን መፍታት ሂደት የሚቀጥል ሲሆን መጪው አገራዊ ምርጫ አለም አቀፍ ተቀባይነት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በዚህ ሂደት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ቦርዱ በአጽንኦት ያስገነዝባል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ