
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ
13 December 2020
የሕሙማኑ ቁጥር በመጨመሩ የጤና ተቋማት ከመቀበል አቅማቸው በላይ ሆኗል
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጽኑ ሕሙማን ክፍል ከገቡት ውስጥ 59 በመቶ ሞተዋል
በኢትዮጵያ በኮረና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ተይዘው ወደ ሕክምና ማዕከል ከሚገቡት ሕሙማን፣ የጽኑ ሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሯ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አሥጊ ደረጃ ላይ መድረሱን አስመልክተው ሐሙስ ታኅሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የጽኑ ሕሙማን ሕክምና የሚፈልጉ ታማሚዎች በከፍተኛ መጠን እየጨመሩ በመምጣታቸው፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከጤና ተቋማት የመቀበል አቅም በላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
በቫይረሱ ተይዘው በየዕለቱ ወደ ሕክምና ማዕከል ከሚገቡ ታማሚዎች ውስጥ በአማካይ 305 ያህሉ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ መሆናቸውን፣ ከገቡት ከ40 እስከ 45 ያህል ሕሙማን ሰው ሠራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ የሚፈልጉ እንደሆነም አክለዋል፡፡
የኅብረተሰቡ መዘናጋት በዚሁ ከቀጠለ በኢትዮጵያ ካለው ውስን የጽኑ ሕሙማን ማቆያ አንፃር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአቅም በላይ ሊሆን እንደሚችል ዶ/ር ሊያ አስገንዝበዋል፡፡ ቫይረሱ ኢትዮጵያ ከገባ ካለፉት ዘጠኝ ወራት ወዲህም በጽኑ ሕሙማን ክፍል ከነበሩ ታማሚዎች 59 በመቶ መሞታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ቁጥሩ ለማደጉ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው መዘናጋት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሊያ፣ ኅብረተሰቡና የሚመለከተው አካል ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው እንደ ምክንያት አስረድተዋል፡፡
በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግዴለሽነት በዚሁ ከቀጠለ የማከሙ ሁኔታ ከአቅም በላይ እንደሚሆን ያላቸውን ሥጋት ገልጸው፣ በአዲስ አበባ ወደ ጽኑ ሕሙማን የሚገቡ ሕሙማን ቁጥር ከአቅም በላይ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ ላይ የሚታየው መዘናጋትና ቸልተኝነት ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ መሠራጨት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ያወሱት ዶ/ር ሊያ፣ የማስክ አጠቃቀምን አስመልክቶ በየጊዜው በተሠሩ ዳሰሳዎች በአዲስ አበባ ቀድሞ የነበረው 78 በመቶ ወደ 62 በመቶ፣ አሁን ደግሞ ወደ 52 በመቶ ወርዷል ብለዋል፡፡ የመከላከል ሥራው እየቀነሰና እየተዘነጋ የጽኑ ሕሙማን ቁጥር ደግሞ እየጨመረ መምጣቱም ተገልጿል፡፡
ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ሊያቃልል ይችላል የተባለው የኮቪድ-19 ክትባት ባደጉት አገሮች በተወሰነ ደረጃ ቢጀመርም፣ በስፋት ተመርቶ ለዓለም ሕዝብ ለማዳረስ ጊዜ እንደሚወስድም አስረድተዋል፡፡
ክትባቱ ሲመረት በቅድሚያ ከዓለም ሕዝብ 20 በመቶ ለሚሆነው ለማዳረስ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆን ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. ከ2021 አጋማሽ በፊት ይደርሳል ተብሎ አይጠበቅም ብለዋል፡፡ ክትባት ቢገኝ ቅድሚያ ተጋላጭ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ክትባቱን ለማግኘት የተጀመረውን ጥረት አስመልክተው እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ክትባቱን ለማግኘት ኮቫክስ ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጀት ጋር እየሠራች ትገኛለች፡፡ ለዚህም በጤና ሚኒስቴር የሚመራ ግብረ ኃይል የተቋቋመ መሆኑን፣ ግብረ ኃይሉም ክትባቱን ለማግኘት ያዘጋጀውን ዝርዝር ዕቅድ ለድርጅቱ መላኩ ተጠቁሟል፡፡
ከሠለጠነው ዓለም ሲነፃፀር በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ዘግይቶ የገባው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደሠለጠነው ዓለም ሰዎች ኢትዮጵያውያንን ባይቀጥፍም፣ ውስጥ ለውስጥ እየተስፋፋ የመጣው ሥርጭት ለኢትዮጵያ ሥጋት መሆኑን የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚታየው መዘናጋትና ቸልተኝነት ዋጋ ያስከፍለናል የሚሉት የጤና ባለሙያዎች በተለይ መንግሥት ለወረርሽኙ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ካነሳ ጀምሮ ኅብረተሰቡ መዘናጋቱን ይገልጻሉ፡፡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛም ሆነ የግል ንፅህናን በመጠበቅ በኩል የተስተዋለው ቸልተኝነት፣ ኢትዮጵያን የማትቋቋመው የጤና ቀውስ ሊከታት ይችላል ይላሉ፡፡
የፀጥታ አካላት ከዚህ ቀደም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ ሰዎችን የሚቀጡበት አሠራር የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን መዘንጋቱ አግባብ እንዳልሆነና የፀጥታ አካላትና የሚመለከታቸው ሁሉ ተናበው በመሥራት ኢትዮጵያ የጤና ቀውስ ውስጥ ሳትገባ እንዲታደጓት ጥሪ ያቀርባሉ፡፡