በመተከል ያለውን ዕልቂት የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ አልገዛም፤ ምናልባትም ለዚህ ምክንያቱ የሚገደለው የአማራና አገው ሕዝብ መሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በእርግጠኝነት የምናገረው በፍጥነት የዚህ ቀጠና ዘላቂ መፍትሔ ካልተበጀለት የእርስ በርስ ጦርነት (Civil war) የሚጀመር እዚህ ቦታ ነው፡፡
በመተከል በሰው ልጅ ላይ ያልተሞከረ ጭካኔ የለም፡፡ ከ1985 ዓም ጀምሮ አካባቢውን ለሚያውቅ ሰው ቀጠናው በተመሳሳይ ሁናቴ ለሦስት ዐሥርት ዓመተት በዚሁ መዝለቁን ይገነዘባል፡፡ ኢትዮጵያውያን በመተከል የሚደረገውን አሰቃቂ ሁኔታ እያዩ አለማውገዛቸው የሞራል ሚዛናችን የተዛባ እንደሆነ ያሳየ ለዘመናት ያልቆመ ነውር ነው፡፡ የሚገደለው አማራ ባይሆን ኖሮ እስካሁን አገር በአንድ እግሯ ቆማ ነበር፡፡ የበሳው ከመምጣቱ በፊት፤
1) የአማራ ብልጽግና አመራሮች ከአክቲቪዝም በመላቀቅ ለዘላቂ ሰላም የሚሆን መሬት የነካ ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋችኋል፡፡ ከፌደራል መከላከያ ጋር በመጣመር ከአሶሳ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋውን መረብ በመበጣጠስ በሴራ የሚያልቁ ንፁኃን አማሮችና አገዎች ሕይወት ሳይውል ሳያድር በቃ ሊባል ይገባል፡፡
2) የቤኒሻንጉል ጉምዝ ከልል አመራሮችን ተጠያቂ በማድረግ በክልሉ የሽግግር ወይም የጥምር መንግሥት ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡
3) የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አጣሪ ባለሙያዎችን በመላክ ይህን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ማሳወቅ አለበት፡፡4) የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች ይህን ግፍ በጋራ በማውገዝ ሰብአዊነታችሁን ማሳየት አለባችሁ፡፡
አልሰማንም አላየንም ብለን የምናልፈው ሞት የሁላችንም ሰላም መንጠቁ አይቀርም፡፡