14 ታህሳስ 2020, 13:00 EAT

አል-ቃይዳ በታንዛኒያ እና ኬንያ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ጥቃት በሰነዘረበት ወቅት የቡድኑ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን መቀመጫው ሱዳን ነበር።
የምስሉ መግለጫ, አል-ቃይዳ በታንዛኒያ እና ኬንያ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ጥቃት በሰነዘረበት ወቅት የቡድኑ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን መቀመጫው ሱዳን ነበር።

አሜሪካ በይፋ ሱዳንን ለሽብር ድጋፍ ከሚያደርጉ አገራት ዝርዝር ውስጥ አስወጣቻት።

ሱዳን ለሸብርተኞች እና ለሽብር ቡድኖች ድጋፍ ታደርጋለች በሚል በአሜሪካው ጥቁር መዝገብ ላይ ስሟ ሰፍሮ ለዓመታት ቆይታለች።

ሱዳን ከዚህ መዝገብ ለመውጣት 335 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል መስማማቷን ተከትሎ ፕሬዝደንት ትራምፕ ሱዳንን ከዝርዝሩ እንደሚያስወጡ አስታውቀው ነበር።

ሱዳን ለመክፈል የተስማማችው ገንዘብ አል-ቃይዳ በታንዛኒያ እና ኬንያ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ ባደረሰው የሽብር ጥቃት ለሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች የሚከፈል ካሳን ይጨምራል። በኤምባሲዎቹ ላይ ጥቃቶቹ ሲሰነዘሩ የአል-ቃኢዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን በሱዳን ይኖር ነበር።

አሜሪካ እአአ 1993 ላይ አል-ቃኢዳ መቀመጫውን ሱዳን አድርጓል በሚል ሱዳንን በዚህ ዝርዝር ውስጥ አካታ ቆይታለች። ይህንንም ተከትሎ ማዕቀብ ተጥሎባት የቆየ ሲሆን በቀጠጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ጫና በማሳደሩ የሱዳን ምጣኔ ሃብትን ሲጎዳው ቆይቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳን በአሜሪካ አሸማጋይነት በቅርቡ ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን ለማሻሻል መስማማቷ ይታወሳል። ከሱዳን በፊት የትራምፕ አስተዳደር ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ባህሬን እና በቅርቡ ደግሞ ሞሮኮ ለእስራኤል እውቅና እንዲሰጡ ማደራደሩ ይታወሳል።

የሱዳኑ የቀድሞ መሪ ፕሬዝደንት ኦማር አል-በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የአሜሪካ እና ሱዳን ግንኙነት መሻሻል አሳይቷል።

አል-በሸር ሕዝባዊ ተቃውሞ ከበረታባቸው በኋላ በአገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሞባቸው ነው ከሥልጣን ወርደው ለእስር ተዳርገው የሚገኙት።

እንደ አውሮፓዊያኑ በ1989 አልበሽር መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ነበር ካርቱምን የጽንፈኞች መናኽሪያ ያደረጓት ይላሉ የአካባቢው ተንታኞች። በዚህም ጂሐዲስቶች ነጻ አገር አገኙ።

በአሜካና በምዕራቡ ላይ ለመዝመት እንቅስቃሴያቸውን ከዚያ ማድረግ እንደጀመሩ ይነገራል።

በአሜሪካ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በግብጽ፣ በኢትዮጵያ፣ በዩጋንዳና በኬንያና በታንዛኒያ እንዲሁም በየመን ለተፈጸሙ ጥቃቶች ግንኙነት ሲካሄድ የነበረው ከሱዳን እንደነበር የደኅንነት መረጃዎች ያመለክታሉ።