15 ታህሳስ 2020, 14:26 EAT

የዘንድሮው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን በርካታ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ተቋም ሲፒጄ ዛሬ ባወጣው ሪፖርቱ አስታወቀ።
ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፣ ስለ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሲዘግቡ የነበሩ ጋዜጠኞች መታሰራቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።
“በወረርሽኙ ወቅትም የጋዜጠኞቹ የፍርድ ሂደት ተጓቷል፤ እስር ቤትም በበቂ ሁኔታ እንዳይጠይቁ ሆኗል፤ እስር ቤት እያሉም ጤንነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችሉ ሁኔታዎችን እያዩ ችላ ተብለዋል” በማለት በዚህም ምክንያት ቢያንስ ሁለት ጋዜጠኞች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መሞታቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል። እስከ ኅዳር 2013 ዓ.ም ድረስ ቢያንስ 274 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል ብሏል።
ኢትዮጵያና ቤላሩስ የጋዜጠኞች እስር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ የመጣባቸው አገራት መሆናቸውን ሲፒጄ በሪፖርቱ ገልጿል።
ለዚህም በኢትዮጵያ ከነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጀምሮ ወደ ወታደራዊ ግጭት ያመራውን ክስተት ተከትሎ በርካታ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን አመልክቷል። በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ታስሮ የነበረው ጋዜጠኛ አንድ ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ቢያንስ ሰባት ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንዳሉ ሲፒጄ ገልጿል።
በምስራቅ አፍሪካ አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በኤርትራ፣ ካሜሩን ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ማሊ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በአጠቃላይ 45 ጋዜጠኞች ታስረዋል። በምስራቅ አፍሪካ በዘንድሮው ዓመት የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ጭማሬ አሳይቷል።
በቤላሩስም የጋዜጠኞች እስር ለመጨመሩ ለረዥም ጊዜ በሥልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚደንት በድጋሜ መመረጥን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ ምክንያት ነው ብሏል። በአገሪቷ እስከ ኅዳር 22 ድረስ ቢያንስ 10 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል።
በርካታ ጋዜጠኞች የታሰሩባቸው አገራት
ቻይና፦ቻይና ኮቪድ -19 ወረርሽኝን በተመለከተ የሚዘግቡ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ለታከታታይ ሁለት ዓመት በርካታ ጋዜጠኞችን ያሰረች አገር ሆና ተመዝግባለች። በቻይና 47 ጋዜጠኞች የታሰሩ ሲሆን አብዛኞቹ ለረዥም ጊዜ በእስር የቆዩና ለምን እንደታሰሩ እንኳን ሳይገለፅ ለእስር የተዳረጉ ናቸው።
ቱርክ፦በዋስ የተፈቱ ጋዜጠኞችን ፍርድ ቤት በማቅረብ እንዲሁም አዳዲስ ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛ ሆናለች። ቱርክ በዚህ ዓመት 37 ጋዜጠኞችን አስራለች። ይህ ቁጥር ከ2008 ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ያነሰ ቢሆንም ባለሥልጣናት አሁንም ጋዜጠኞችን ማስሩን ቀጥሏል ብሏል ሲፒጄ።
ግብፅ፦ ግብፅ ደግሞ በምንም ዓይነት ወንጀል ሳይከሰሱ ጋዜጠኖችን የምታስር አገር ተብላለች። በአገሪቷ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር 27 የደረሰ ሲሆን በ2008 ዓ.ም የተመዘገበውን ከፍተኛ ቁጥር ጋር የሚስተካከል ነው።በአገሪቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎም በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀመው እንደቀጠለ ሲፒጄ በሪፖርቱ ጠቅሷል።
ሳዑዲ አረቢያም ጋዜጠኞች በማሰር ግብፅን ተከትላ ተቀምጣለች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በእስር ላይ ከሚገኙ ጋዜጠኞች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የተከሰሱት በሽብር እና በሕግ በታገዱ ቡድኖች አባልነት ምክንያት መሆኑንም ሲፒጄ በሪፖርቱ አትቷል።
ሲፒጄ በሪፖርቱ የተገለፀው የጋዜጠኞች ቁጥር እስከ ኅዳር 2013 ዓ.ም ድረስ በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች ቁጥር መሆኑን በመጥቀስ ዓመቱን ሙሉ ሲታሰሩና ሲፈቱ የነበሩ የጋዜጠኞችን ዝርዝር አለማካተቱን አክሏል።