21 ታህሳስ 2020, 10:06 EAT

ኮቪድ-19 ክትባት ተገኘለት እፎይ መባል በጀመረ ገና በሳምንቱ ከወደ ብሪታኒያ መጥፎ ዜና ተሰምቷል፡፡ የኮቪድ ተህዋሲ አዲስ ዝርያ ያለባቸው ሰዎች መገኘት ነው ዜናው፡፡
በፈረንጆች ገና ይህ ያልተጠበቀ ዜና መሰማቱ ለጊዜው አውሮጳን እያመሳት ነው፡፡
ከብሪታኒያ የሚመጡ አውሮፕላኖች ላይ እግድ እያወጡ ያሉት የአውሮጳ አገራት ድንበራቸውን ጠርቅመው እየዘጉት ነው፡፡
ለመሆኑ ይህ አዲስ የኮቪድ ዝርያ ምንድነው?
1ኛ፡- በብሪታኒያ በተለይም በሎንደንና አካባቢው እስከዛሬ ታይቶ የማይታወቅ የተህዋሲው ናሙና ተገኝቷል፡፡ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን በታመሙ ሰዎች ላይ በብዛት የሚታየው የቫይረስ ዓይነትም ይኸው ዝርያ መሆኑ ድንጋጤን ፈጥሯል፡፡
2ኛ፡- ይህ የቫይረስ ዝርያ ሌሎች የተህዋሲ ዝርያዎችን በፍጥነት እየተካ ቦታውን እየያዘ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
3ኛ፡- ራሱን የሚያባዛበት መንገድ ለየቅል መሆኑ ምናልባት ለቁጥጥር ያስቸግር ይሆን የሚል ስጋትን ጨምሯል፡፡ ከመተንፈሻ አካል ውጭ ያሉ ሴሎችንም ራሱን እየለወጠ የማጥቃት አቅም ሊኖረው ይችል ይhoን የሚል ስጋትም አለ፡፡
4ኛ፡- ለመጀመርያ ጊዜ ይህ የተህዋሲ ዝርያ የተገኘው በመስከረም ወር ነበር፡፡ በጥቅምት ወር ሎንዶን አካባቢ በኮቪድ ከተያዙት ሲሶዎቹ የዚህ ተህዋሲ መልክ ተገኘባቸው፡፡ በታኅሣሥ ወር ደግሞ 75 ከመቶዎቹ ታማሚዎችን የለከፈው ይህ ልዩ ተህዋሲ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡
- በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምክንያት የአውሮፓ አገራት ብሪታኒያን እያገለሏት ነው
- የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው አለ
- አሜሪካ ተጨማሪ የኮቪድ-19 ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቀደች
5ኛ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ ይህ ተህዋሲ እስከዛሬ ከነበረው ቫይረስ ጋር ሲወዳደር የመዛመት ዕደሉ በ70 ከመቶ የፈጠነ ነው ብለዋል፡፡
6ኛ፡- አዲሱ የተህዋሲ ዝርያ በጊዜ ሂደት ራሱን ቀይሮ ይሁን ወይም ከሌላ ቦታ መጥቶ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።
7ኛ፡- አዲሱ የተህዋሲ ዝርያ በመላው ብሪታኒያ የተሰራጨ ቢሆንም አሁን ክምችቱ በብዛት የሚኘው በለንደንና አካባቢው ነው፡፡ ከለንደን በተጨማሪ በደቡብ ምሥራቅና በምሥራቅ ኢንግላንድም እንዲሁ በስፋት ተመዝግቧል፡፡
8ኛ፡- ኔክስትስትሬይን የተሀዋሲ ዝርያዎችን የዘረ መል ኮድ የሚመዘግብ ድርጅት ሲሆን፣ ይህ ልዩ የተህዋሲ ዝርያ ከብሪታኒያ ወደ ዴንማርክና አውስትራሊያ መዛመቱን ተናግሯል፡፡ ኔዘርላንድና ጣሊያንም ይህ አዲሱ የተህዋሲው ዝርያ አገራቸው መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡
9ኛ፡- ይህ ልዩ የተህዋሲ ዝርያ ቅንጣት በደቡብ አፍሪካም ተገኝቷል የተባለ ሲሆን በኋላ ላይ የወጡ መረጃዎች ግን ከዚህ ብሪታኒያ ተገኘ ከተባለው ተህዋሲ ጋር የዝርያ ተመሳሳይነት የላቸውም ብለዋል፡፡
10ኛ፡- ተህዋሲው ራሱን ቆርጦ እየቀጠለና እያባዛ ሊያመልጥ ቢችልም አሁን ወደ ገበያ እየገቡ ያሉ ክትባቶች ግን ማንነቱን ያጠፉታል፣ ፈውስም ይሆናል ተብሎ በስፋት ታምኗል፡፡
ከዚሁ አዲስ የተህዋሲ ዝርያ ጋር ተያይዘው የሚነሷ አንኳር ጥያቄዎች
የኮቪድ ተህዋሲ እስከዛሬ ሌሎች ዝርያዎች ኖረውት ያውቃሉ?
አዎ!
ዛሬ በተለያየ ዓለም የምናገኘው የቫይረስ ዝርያ ቅንጣት ቻይና ዉሃን ከተማ ከተገኘው ዝርያ ጋር አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ አሁን በብዙ የአውሮጳ አገሮች የሚገኘው D614G የሚባል የተህዋሲ ዝርያ ዓይነት ነው።
ይህ የተህዋሲ ዝርያ ቅንጣት ከየት ተወለደ?
ተህዋሲው ራሱን እየቀየረ ሊመጣ ይችላል፡፡
ምናልባት መነሻው ሊሆን የሚችለው ደካማ የመከላከል አቅም ካለው በሽተኛ ራሱን ቀይሮ የተነሳ ተህዋሲ ነው የሚሆነው፡፡ አንድ ታማሚ ተህዋሲውን ማሸነፍ ሲሳነው ሰውነቱ የተህዋሲው መራቢያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡
ይህ የተህዋሲ ዝርያ ከሌሎች ዝርያዎች የበለጠ ገዳይ ነው?
እስከአሁን በዚህ ረገድ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ገና በደንብ መጠናት ይኖርበታል፡፡ ለጊዜው የሚታወቀው በከፍተኛ ፍጥነት ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ብቻ ነው፡፡
ያም ሆኖ ብዙ ሰዎችን ማዳረስ ከቻለ ብዙ ሰዎች አልጋ ይይዛሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ ሞትን ሊጨምር ይችላል፡፡
ተገኙ የተባሉት ክትባቶች ይህን የተህዋሲ ዝርያ ያስቆሙታል?
መቶ በመቶ ባይሆንም አሁን የሚገመተው ክትባቶቹ ለዚህ ተህዋሲም ፈውስ እንደሆኑ ነው፡፡
ይህም የሚሆነው አሁን ተሳኩ የተባሉት ክትባቶች የተህዋሲውን መላ አካሉንና ባህሪውን ሁሉ እንዲያጠቁ የተዘጋጁ ስለሆኑ ተህዋሲው ራሱን እያባዛ ራሱን ሊቀያይር ቢሞክርም እንኳ ከክትባቶቹ ያመልጣል ማለት ዘበት ነው ይላሉ ተመራማሪዎች፡፡