የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመተከል ተደጋጋሚ የንፁኃን ግድያ እና በአሸነባሪነት ሊፈረጁ ይገባቸዋል ባሏቸው ድርጅቶች ላይ በዝግ መምከራቸውን አሐዱ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡
አባላቱ ስለምን መንግሥት ጥቃቱን ማስቆም ተሳነው? በሚለው እና እኛ ምን እናግዝ? በሚሉ ሃሳቦች ላይ በዝግ መክረዋል ነው የተባለው፡፡ በዚህም ለስብሰባው የተጠሩ መገናኛ ብዙኃን ከ1 ሰዓት በላይ ከአዳራሽ ውጭ እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ ከዚህ ቀደምም በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ተጠይቆ ምላሽ ባልተሰጠባቸው የሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ ጉዳይ ላይ ለምንድነው በሽብርተኝነት ተፈርጀው እርምጃ የማይወሰደው? የሚል ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉን ከእንደራሴዎቹ መስማቱን ነው ጣቢያው የጠቀሰው።
በተጨማሪም መቀመጫውን ሱዳን አድርጎ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የቤኒሻንጉል ነፃ አውጭ ንቅናቄም በአሸባሪነት እንዲፈረጅ የሚል ሃሳብ ላይ መክረዋል፡፡
በውይይቱ በቀጣይ ማክሰኞ ወይም ሐሙስ በሚጠበቀው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ የአገሪቱ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማትን የሚመሩ ባለሥልጣናት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ እንደራሴዎቹ ተስማምተዋል፡፡
ለዚህም የውሳኔ ሃሳቦችን የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲሁም የውጭ ግንኙነትና ደኅንነት ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲያቀርቡ በመስማማታቸው የዝግ ስብሰባው ተቋጭቶ፤ ሌሎች ለመገናኛ ብዙኃን ክፍት የተደረጉ አጀንደዳዎች ተመክሮባቸዋል ሲል አሐዱ ቴሌቪዥን ዘገባ ያሳያል።
