(ኢ ፕ ድ) – ላለፉት 30 አመታት አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው የኖሩትና የደርግ ባለስልጣናት የነበሩት ኮለኔል ብርሃኑ ባየህና ሌተናል ጄነራል አዲስ ተድላ እንዲለቀቁ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መወሰኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምንጮች አረጋገጡ።ፍርድቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት የሁለቱን ግለሰቦች ጉዳይ ተመልክቶ በአመክሮ እንዲፈቱ ወስኗል።

ቀደም ብሎ በእነ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የክስ መዝገብ ስር ተፈርዶባቸው የነበረው ቅጣት ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮ እንደነበር በመግለጽ፤ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የአመክሮ አስተያየትን ከይቅርታ ሰነዶች ጋር ለፍርቤት ማቅረቡን አስታውቋል።የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የእድሜ ልክ ፍረደኛ በአመክሮ መታሰር ያለበት ለ20 አመት በመሆኑ ግለሰቦቹ በአመክሮ ቢፈቱ ተቃውሞ የለንም የሚል አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ፍርድቤቱም ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የህግ መንግስት ድንጋጌዎችና ሌሎች ህጎች መርምሮ ግለሰቦቹ ከኢንባሲው እንዲለቀቁ ወስኖ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትዛዝ ሰጥቷል።ትዛዙ በቀጥታ ለጣሊያን ኤምባሲ ሳይሆን በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለጣሊያን ኤምባሲ እንዲሁም ለቀድሞ ፍርደኞች ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ እንዲደርስ ይደረግ ዘንድ አዟል።
ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ የቀድሞ ፍርደኞች አሁን ግን በአመክሮ በፍርድ ቤት የተለቀቁ መሆኑን አውቀው መብታቸውን ለማስከበር ጥበቃም ሆነ ክትትል እንዲያደርጉ ለሚመለከተው አካል እንዲጻፍ ፍርድ ቤቱ አዟል።
