የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በመተከል ዞን ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ መካሄዱን እንዳረጋገጠ ገለጸ

(ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ መካሄዱን የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ባካሄደው የጥናትና ቁጥጥር ስራ እንዳረጋገጠ ገለጸ።ተቋሙ ለኢዜአ በላከው መግላጫ እንዳስታወቀው፤ በመተከል ዞን እየደረሰ ባለው የዜጎች ጭፍጨፋ፣ የንብረት ውድመትና ከቤት መፈናቀል የክልሉ መንግስትና የጸጥታ መዋቅር ድርጊቱን መከላከልና ማስቆም ለምን እንዳልቻሉ ለመመርመርና ለማጥናት ሞክሯል።–ጉዳዩን የሚመረምር የጥናትና ቁጥጥር ቡድን ወደ አካባቢው በመላክ ባደረገው ጥናትም በዞኑ ማንዱራ፣ ዳንጉር፣ ጉባ፣ ደባጤ፣ ቡለንና ወንበራ ወረዳዎች ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ የተካሄደ መሆኑን እንዳረጋገጠ አመልክቷል።“እስከ ታህሳስ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከ163 በላይ ዜጎች ህይወት ያለፈ መሆኑን እንዲሁም ከ31 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ለመረዳት ተችሏል” ብሏል በመግለጫው።–በተፈጸመው የወንጀል ድርጊት የክልሉ መንግስት አስተዳደር አካላት፣ የፓርቲ አመራሮችና የጸጥታ መዋቅር አካላት እንደተሳተፉም ጠቁሟል።ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት አካላት የነበራቸው ድጋፍና ክትትል ዝቅተኛ እንደነበር ገልጾ፤ “”ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል የነበረው የኮማንድ ፖስት ከችግሩ ክብደትና ስፋት አንጻር የሰራው የጸጥታ ማስከበር ስራና በአጥፊዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ደካማ እንደነበር የተቋሙ የጥናትና የቁጥጥር ቡድኑ ለይቷል” ብሏል።–ተቋሙ የክልሉ የአስተዳደር አካላትና የጸጥታ መዋቅር በወንጀል ድርጊቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸው እንዳለበት እንደሚያምን ገልጿል።በመሆኑም በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለ የመንግስት መዋቅር የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ቀዳሚ ተግባርና ሃላፊነቱን ተገንዝቦ የዜጎችን ንብረትና ደህንነት በአግባቡ እንዲጠብቅና ዳግም ተመሳሳይ ጉዳት እንዳይደርስ አሳስቧል።ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመተከል ዞን ከህብረተሰቡ ተወካዮችና ከአመራሮች ጋር ተወያይተው ያስቀመጧቸው አቅጣጫዎች በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆኑ ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።በተጨማሪም በወንጀል ድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የነበሩ አካላት በህግ እንዲጠየቁ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድና ለህዝቡም ይፋ እንዲሆን ጠይቋል። የፌዴራል የጸጥታ መዋቅር አካላት ህጉ በሚፈቅደው መንገድ ከሁሉም ክልሎች የተቀናጀ የጸጥታ ሃይል በማዋቀር በክልሉ ተሰማርቶ የዜጎችን ህይወትና ንብረት ሊታደግ በሚችልበት ቁመና ላይ እንዲገኝ መንግስት ከውሳኔ ላይ እንዲደርስ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
