ዶክተር ፍፁም ኃይለማሪያም

በአሜሪካው የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ፋይዘር እና በጀርመኑ የሕክምና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ባዮንቴክ በጋራ የተሰራው የኮቪድ -19 ክትባት በአሜሪካ መሰጠት ከጀመረ ሁለት ሳምንታት አልፎታል።

ክትባቱም ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ እንደ የጤና ባለሙያዎችና በዕድሜ የገፉ ሰዎች በቅድሚያ እየተሰጠ ነው።

በዚያው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የጤና ባለሙያዎችም ክትባቱን እየወሰዱ ነው።

መስመር

ዶክተር ፍፁም ኃይለማሪያም በአሜሪካ ፊላደልፊያ ቶማስ ጃፈርሰን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ የውስጥ ደዌና የኩላሊት ሕክምና ስፔሻሊስት ነው።

በቅርቡ ፋይዘር /ባዮንቴክ ያበለፀጉት የኮቪድ-19 ክትባትን ከተከተቡ ባለሙያዎች አንዱ ነው።

ዶክተር ፍፁም በበሽታው የታመሙትንም፣ የሞቱትንም፣ ወረርሽኙ ያስከትለውንም ዘርፈ ብዙ ችግር በቅርበት ስለተመለከተው ክትባቱ እስከሚመጣ እየተጠባበቀ ነበር።

በዚህም ምክንያት ክትባቱን ለመከተብ ለመወሰን አልተቸገረም።

“ክትባቱ ያለፈበትን የምርምር ሂደት በቅርብ ለመከታታል ችያለሁ። በምን ደረጃ እንዳለፈ፣ ውጤታማና ደህንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ መረጃው ስላለኝ ለመከተብ አላመነታሁም” ይላል።

ሌላኛው ክትባቱን የወሰዱት የሕክምና ባለሙያ ደራራ ዳዲ ይባላሉ። በካሊፎርኒያ ሳን ሆዜ ከተማ ፓልምትሪ የእንክብካቤ ማዕከል ነርስ ናቸው።

እርሳቸውም ከዶ/ር ፍፁም የተለየ ሃሳብ የላቸውም።

“በእውነቱ ይሄ ክትባት በመገኘቱ ሁላችንም ደስተኞች ነን። በተለይ ደግሞ ከህሙማን ጋር ንክኪ ያለን ሰዎች ከዛሬ ነገ ይይዘኛል የሚል ስጋት ነበረብን። . . . አሁን ማንኛውም የጤና ባለሙያ በክትባቱ ደስተኛ ነው” በማለት በክትባቱ መገኘት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

በኮሮናቫይረስ ተይዘው ያገገሙ ክትባቱን ይወስዳሉ?

አንዳንድ በበሽታው ተይዘው ያገገሙ ሰዎች በራሳቸው የበሽታ መከላከል አቅም እንዳጎለበቱና ዳግም እንደማይዛቸው በማሰብ ሲዘናጉ ይስተዋላል። ክትባቱንም መከተብ እንደማያስፈልጋቸው የሚያስቡም አሉ።

ዶክተር ፍፁም ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ ሦስት ጊዜ ያህል የኮሮናቫይረስ ምርምራ አድርጓል። ሦስቱንም ጊዜ ግን ነጻ ነበር።

“ምን አልባት ባልተመረመርኩባቸው ጊዜያት ይዞኝ ሊሆን ይችላል” ይላል።

ዶ/ር ፍፁም እንደሚለው ምን አልባት በቅርብ ጊዜ የታመሙ ሰዎችና በሕክምና ላይ ያሉ ሰዎች ክትባቱን ላይወስዱ ቢችሉም፤ በበሽታው ተይዘው የዳኑ ሰዎች ግን ክትባቱን ወስደዋል፤ መውሰድም ይገባቸዋል ሲል ያስረዳል።

“አንዳንድ ጥናቶች በበሽታው ተይዘው የዳኑ ሰዎች በሽታ የመከላከል አቅማቸው ከተወሰነ ወራት በኋላ ሲቀንስ አሳይተዋል። በእርግጠኝነት በአንድ ጊዜ መታመም በሽታውን ይከላከላል ወይ? የሚለውን ማወቅ አይቻልም። በሽታው ከያዛቸው በኋላ በበሽታው ድጋሜ የተያዙ ሰዎች አሉ፤ በመሆኑም ክትባቱን መውሰዱ ጥሩ ነው” ሲልም ይመክራል።

ክትባቱ የሚሰበት ሂደምን ይመስላል?

በሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን እንዲወስዱ የተደረገው እንደ ተጋላጭነታቸው ሁኔታ ነው። በተለይ ደግሞ ፅኑ ሕሙማንና ድንገተኛ አደጋ ክፍል የሚሰሩ ባለሙያዎች ቅድሚያ እንደተሰጣቸው ዶ/ር ፍፁም ይናገራል።

ዶ/ር ፍፁም እንደሚለው ማንኛውም ሰው ክትባቱን ከመውሰዱ በፊት ወደ 10 የሚደርሱ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል።

ለምሳሌ አለርጅ [የሰውነት መቆጣት] ያለባቸው ፣ ነፍሰጡር ሴቶች፣ የማንኛውም ህመም ምልክት ያለባቸው እንዲሁም በማንኛውም በሽታ ለህመም ተዳርገው ሆስፒታል ያሉ ሰዎች ክትባቱን አይወስዱም።

እነዚህንና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟሉ ግን ክትባቱን ይወስዳሉ።

ክትባቱ ከተወሰደ በኋላም ለ15 ደቂቃ እዚያው እንዲቆዩ ይደረጋል። ይህ የሚደረገው ምን አልባት የተለየ የሰውነት ግብረ መልስ ካለ በሚል ነው።

ዶ/ር ፍፁም ክትባቱን ከወሰደ በኋላ ምንም ዓይነት ችግር ስላልገጠመው በቀጥታ ወደ ሥራው እንዳመራ ይናገራል።

የኮቪድ-19 ክትባት ከሌሎቹ ክትባት የሚለየው ነገር የለም የሚለው ዶ/ር ፍፁም፤ “በክንድ ላይ በመርፌ የሚሰጠው ክትባቱ የሚወሰደው ሁለት ጊዜ ነው። የመጀመሪያው ክትባት በተወሰደ በሁለተኛ ሳምንቱ ሁለተኛው ክትባት ይሰጣል። ውጤታማ የሚሆነውም ከዚያ በኋላ ነው” ይላል።

እርሱ እንደሚለው ክትባቱ በተወጋበት ቦታ ላይ መርፌ ሲወጋ የሚሰማ ስሜት፣ መጓጎል ዓይነት ምልክቶች ካልሆነ በስተቀር ሌላ የተለየ ስሜት አልተሰማውም።

ነርስ ደራራም በበኩላቸው ክትባቱ ምንም የተለየ ስሜት እንዳልፈጠረባቸው ተናግረዋል። “ከተከተብኩ ከ30 ደቂቃ በኋላ ነው ወደ ሥራ የሄድኩት። የተወጋሁበት ቦታ ትንሽ ህመም ነበረው፤ ከዚያ ውጭ ምንም ነገር የለኝም” ብለዋል።

አንዳንድ ሰዎች ክትባቱን ከወሰዱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደማያስፈልግ ሲናገሩ ይሰማል። ዶ/ር ፍፁም ግን ከተከተብኩ በኋላ ኃላፊነት ተሰምቶኝ ነው የወጣሁት ይላል።

” ክትባቱ ለበሽታው የመጋለጥና የመታመም ዕድሌን 95 በመቶ ይቀንሰዋል እንጂ፤ ኢንፌክሽን ሊኖርና በሽታውን ለሌላ ሰው ላስተላልፍ እችላለሁ። ስለዚህ እስከ 60/70 በመቶው የማሕበረሰብ ክፍል እስኪከተብ ድረስ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግና ሌሎች ጥንቃቄዎችን አልተውም፤ ግዴታም ነው” በማለትም የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች መቀጠል እንዳለባቸው ይመክራል።

በክትባቱ ላይ ያላቸው አመኔታ

ስለ ክትባቱ በርካታ የተሳሳቱ መረጃዎች ይሰማሉ። በተለይ ደግሞ ዓመታትን ይወስዳል የተባለው ክትባት በአጭር ጊዜ መገኘቱ አንዳንድ ሰዎች በክትባቱ ላይ እምነት እንዳያሳድሩ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ ነው።

ይህንን እና ሌሎች የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለመለወጥ የአገር መሪዎች በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ሲከተቡ ታይተዋል።

ከእነዚህ መካከል ተመራጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደንና ምክትል ፕሬዚደንት ማይክ ፔንስ ይጠቀሳሉ።

ጆ ባይደን

“እዚህ እኛ በምንኖርበት አሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ወረርሽኙ ብዙ የተሳሳቱ ነገሮችን ይናገሩ ስለነበር፤ ዓለም ላይም የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ፈጥሯል” የሚለው ዶ/ር ፍፁም፤ እርሱ ግን የሕክምና ባለሙያ በመሆኑ በጥናቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተሳተፉ፣ ምን ያህል ክትባት እንዳገኙ፣ ከዚያ ውስጥ ምን ያህሉ ደህና ሆነው እንደቆዩ እና ክትባቱን ያልወሰዱ በበሽታው እንደተያዙ መረጃው ስላለው ጥርጣሬ አልፈጠረበት።

ክትባቱ እንዴት በቶሎ ደረሰ? ለሚለውም ወረርሽኙ መላው ዓለምን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደከተተው በመጥቀስ፤ በዚህም የተነሳ የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም አገሮች ክትባቱን ስለደገፉት እንዲሁም ሳይንሱም ስላደገ ቶሎ ሊደርስ መቻሉን ይናገራል።

ምንም እንኳን አብዛኞቹ ክትባቱን እየወሰዱ ቢሆንም፤ አንዳንድ በእድሜ ገፋ ያሉና ሌሎች ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ‘የክትባት አለርጂ አለብኝ’ በማለት ክትባቱን ሲሸሹም ነርስ ደራራ ታዝበዋል።

ዶ/ር ፍፁም እንደሚለው በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ስለክትባቱ የሚጻፉ መረጃዎች በርካቶችን እያሳሳተ ነው። እርሱም ከቤተሰቦቹ ተቃውሞ አይግጠመው እንጂ ጥርጣሬ እንዳላቸው ሲገልፁለት እንደነበር ይናገራል።

ይህም ጥርጣሬያቸው የመነጨው ከማኅበራዊ ሚዲያ ከሚያገኙት የተሳሳተ መረጃ የተነሳ ነው ይላል።

“ሐኪሞች ከሚሰጡት መረጃ ይልቅ፤ የተሳሳቱ መረጃ የሚሰጡ ማህበራዊ ሚዲያዎች ብዙ ናቸው። ብዙ ሰውም ይመለከታቸዋል። ይህ ደግሞ ብዙውን ሰው ያሳስታል። በመሆኑም እዚህ ላይ ከፍተኛ ሥራ መሰራት አለበት። የተሳሳተ መረጃ ከእውነተኛ መረጃው ፈጥኖ እየተሰራጨ በመሆኑ ‘አልከተብም’ የሚለው ሰው እንዳይበዛ እፈራለሁ” ሲል ስጋቱን ገልጿል።

ክትባቱ ‘ማይክሮቺፕ’ አለው፤ እኛን ለመከታተልና ለመሰለል የተደረገ ነው፣ የአፍሪካን ሕዝብ በ500 ሚሊየን ለመቀነስ የተደረገ ሴራ ነው” የሚሉ የተሳሳቱ መረጃዎችን እንደተመለከተም አስታውሷል።

በመሆኑም የሚዲያ ባለሙያዎችና የጤና ባለሙያዎች በዚህ ላይ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስቧል።

ክትባቱ የሰጠው ተስፋ

ነርስ ደራራ በተለይ የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን መውሰዳቸው ለጤና ዘርፉ ትልቅ ድጋፍ ያደርጋል ይላሉ።

ከዚህ ቀደም በእድሜያቸው ገፋ ያሉ ነርሶች በሽታውን ፈርተው ጡረታ የወጡና ቤታቸው የተቀመጡ እንዳሉ ያስታወሱት ነርስ ደራራ፤ በዚህ ምክንያት የጤና ባለሙያዎች እጥረት በማጋጠሙ በሌሎች ሰራተኞች ላይ ጫና እንደነበር ይናገራሉ። ክትባቱን ከተከተቡ እነዚህ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ይመለሳሉ የሚል ተስፋን ፈንጥቋል።

“ይህ መሆኑም ሥራውን ያቀላጥፋል፣ በራስ መተማመንን ይጨምራል፤ የጤና ሰራተኞች የመታመም ዕድልን ይቀንሳል” ብለዋል።

ዶ/ር ፍፁም በበኩሉ ክትባቱ በግለሰብም፣ በተቋማትም ሆነ በአገር ደረጃ የሰጠው ተስፋ ቢኖርም፤ በዚህ ተስፋ መዘናጋት እንዳይኖር ጥንቃቄዎች ላይ ትኩረት መደረግ ይኖርበታል ይላል።

“ክትባቱም ቢመጣም አብዛኛው ሰው እስኪከተብ ድረስ አሁን የምናደርጋቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች የሚቋረጡ አይደሉም። ሰው በሙሉ ከመከተቡ የተነሳ ሌላውን ከማስያዝ የምንከላከልበት ደረጃ [ኸርድ ኢሚዩኒቲ] ስናዳብር ወደ ቀደመው ሕይወት ልንመለስ እንችላለን። አሁን ግን ሁሉም ሰው ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ክትባቱ ተስፋ ነው፤ ተጀምሯል፤ ነገር ግን አሁኑኑ ወደ ቀድሞው ሕይወት እንመለሳለን ማለት አይደለም” ሲል መዘናጋት እንዳይኖር መክሯል።

በዓለማችን እስካሁን ከ78 ሚሊየን 837 ሺህ ሰዎች በላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን፤ ከ1 ሚሊየን 733 ሺህ ሰዎች በላይ ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

ከዚህ ውስጥ ከ18 ሚሊየን 466 ሺህ ሰዎች በላይ በቫይረሱ የተያዙ፤ ከ326 ሺህ ሰዎች በላይ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች የተመዘገቡት በአሜሪካ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ በፋይዘርና በባዮንቴክ የበለፀገውን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለዜጎቻቸው እየሰጡ ነው።

95 በመቶ ኮሮናቫይረስን ይከላከላል የተባለለት ይህንን ክትባት ለዜጎች በመስጠት ዩናይትድ ኪንግደም ቀዳሚዋ አገር ናት።

ሩሲያና ሕንድን ጨምሮ ሌሎች አገራትም ክትባቱን መስጠት መጀመራቸው ተዘግቧል።

ኢትዮጵያን ጨምሮም ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ክትባቱን ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዩናይትድ ኪንግደም ተገኘ የተባለው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ሌላ ስጋት ፈጥሯል። አንዳንድ አገራትም ወደ ዩኬ የሚያደርጉትን በረራ አቋርጠዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንም በዚሁ ሳምንት በጉዳዩ ላይ መክሯል። አገራትም በዩኬ ላይ የጣሉትን የበረራ እገዳ እንዲያነሱ አሳስበዋል።

አዲሱ የኮሮናቫይረስ የመዛመት እድሉ ከነባሩ 70 በመቶ የበለጠ ቢሆንም ገዳይነቱ ግን እንደ ቀድሞው አይደለም እየተባለም ነው።