December 10, 2018 

ዛሬ እፊታችሁ የቆምኩት ከአዛውንት ተራ የተሰለፍኩ ሴት ትናንትን ሳስብ የምትታየኝ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይና ጉራንጉሮች ውስጥ የሕዝብን ጥያቄ አንግባ ላይ ታች የምትል ለጋ ወጣት ነች።

ከእርሷም ጋር እነዚያ ልክ እንደእርሷው የነበሩ ወጣቶች በዚያው በወጣትነት ቁመናቸው ይታዩኛል። ታዲያ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ከተማና ገጠር ለሐገርና ለሕዝብ ብለው ይማስኑ የነበሩ ወጣቶች ድቅን ይሉብኛል፤ ድምጻቸውም ይሰማኛል።

ከወንዶቸ እኩል መሆኔን እንዳምን ጉልበት የሰጥኝን ያንን የትግል ዘመን የማስታውስው ስቃዩና እንግልቱ እንዲሁም እልቂቱ ያስከተለውን ሓዘን በሚሸፍን ደስታ ቢሆንም በእስር ቤቶች ውስጥ በሴትነታችን የደረሱብንን መከራዎች ማስታውስ ግን ያማል፡፡ ኢሕአፓ ውስጥ የተሳተፍነው በታጋይነት ሳይሆን ለርካሽ ተግባር መጠቀሚያነት መሆኑን እንድናምን ከመገረፍ ጀምሮ መደፈርንና በሴት ልጅ ላይ ሊፈፀሙ ይችላሉ ተብለው የማይታስቡ ጭካኔዎችን መቀበል ነበረብን፡፡

ብዙዎች እነዚያን ሁሉ ጭካኔዎች ተቋቁመው ለአላማችው መስዋእትነት ከፍልዋል፡፡ እነዚያ ዓላማቸው ዓላማዬ፣ ጩኸታቸው ጩኸቴ፣ ስቃያቸው ስቃዬ የነበረ ሞታቸው ግን ሞቴ ሳይሆን ያለፈኝ ሴቶችና ወንዶች ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ምንጊዜም የሚዘነጉኝ አይደሉም። ሰንደቃቸውን አንስተን ትግሉን እንደምንቀጥል አምነው መፈክራችንን እየፈከሩ ድል ለሕዝብ እንደሚሆን እርግጠኞች ሆነው የተሰዉ ሁሉ የዚህች አገር ሰማዕታት መሆናቸውን ለአፍታም እንኳ መጠራጠር አይቻልም።

ዛሬ ዛሬ ግን ትናንትን በዛሬ ዓይን በማዬት፣ በዛሬ ጭንቅላትና አመለካከት ለመገምገም በመሞከር ለመስዋዕትነታቸው ክብር ላለመስጠት የሚደረግ ሙከራ በርካታ እየሆነ ነው። እነዚያን ሕይወታቸውን፣ ኑሮአቸውንና ቤተሰባቸውን ለሃገር እድገት፣ ለሕዝብ ዲሞክራሲን፣ ፍትህና እኩልነት አሳልፈው ይሰጡ የዓላማ ሰዎች ታሪክ የማጠልሸቱ ሁኔታ እንደቀጠለ ነው።

ሆኖም ትናንት ትናንት ዛሬም ዛሬ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልምና ወቅቱ በፈቀደው ፖለቲካዊ አመለካከት ባመኑበት መሰመር በጽናት በመታገል ለተሰዉት ወገኖች ያለኝ አክብሮት ህያው ነው። በወቅቱ የተከተልኩት የፖለቲካ መስመር ትክክል ለመሆኑ ለአፍታ እንኳ ተጠራጥሬ አላውቅም፤ በኢ ሕ አ ፓ ጥላ ስር መሳተፌም በሕይወት ዘመኔ ከምኮራባቸው ተግባሮቼ የመጀመሪያው ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። ያን ጊዜ ዓለም ተቀብሎ ያቀነቀነውን የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መንገድ መከተል የወቅቱ መፈክር ነበር። በግራው የፖለቲካ መስመር ውስጥ ርእዮተ ዓለማዊ ግብግቡ፣ በተለያዩ ምክንያቶች መለያየትና መገዳደሉም ቢኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ አይመስለኝም፡፡

ዛሬ ስናስበው ይዘግንነን እንጂ በዚያን ጊዚው የፖልቲካ እምነት ላመኑበት መስመር መሞትም ሆነ መግደል የጥንካሬ መለኪያ ነበር፡፡ በትግሉ ሂደትም “ነፃነት የሚገኘው ከጠመንጃው አፈሙዝ ከሚወጣው ፍላፃ ነው” የሚለው አባባል በትግሉ ውስጥ የተሳተፉትን ሁሉ አሳምኖ አብዛኞቹ መሳሪያ መታጠቅንና ቃታ መሳብን እንዲመኙ አድርጎ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ያንን ሃሳብ የሚያስተናግድ አእምሮ ጤነኛ አይደለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ዓለምን ለሁለት ከከፈለው ቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ የአለም ፖለቲካዊ አመለካከት ወደሰላማዊ ትግል ተቀይሮ የሕዝብ ስልጣን የሚመነጨው ከድምጽ ኮሮጆ ውስጥ መሆኑ ሁሉንም የሚያግባባ ሆኗል፡፡

ታዲያ ይህ አባባል እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራተ ከወሬ የዘለለ ሳይሆን እነሆ በርካታ አስርተ አመታት አልፈዋል፡፡ የጮህንለት፣ የታሰርንለት፣ የተገረፍንለት፣ የተገደልንበትና የገደልንለት፣ የተሰደድንለት ሕዝባዊ መንግስት እውን ሳይሆን፤ ነጻነት፣ ፍትሕ ሳይሰፍን፣ ድህነት ጎጆውን እንደሰራብን፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ዘረኝነትና መለያየት በጠባብ አጥር ውስጥ አስሮን፣ ሌብነትና ራስ ወዳድነት የነበሩንን በጎ እሴቶች ሁሉ አጨልሞብን፣ ግራ እንደገባን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡

አንዳንዶች ግን በእነዚህ ሁሉ አመታት በአንድም በሌላ መልኩ ትግላቸውን ሳያቋርጡ ኖረዋል፤ ብዙዎቻችን ደግሞ ውሰጣችን እየተብላላ በዝምታ ኖረናል፡፡ በእውነቱ በምንም ደረጃ ይሁን ትግላቸውን ሳያቋርጡ ለኖሩት ሰዎች ከፍተኛ አድናቆት አለኝ፡፡ በውጭ ሃገራት በስደት እየኖሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተደረጉ ትግሎች ኢ ሕ አ ፓ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ላደረጉ፣ ወደሃገር ውስጥ ለገቡትና ላልገቡት መሪዎችና በውጭም በሃገር ውስጥም ሲንቀሳቀሱ ለኖሩ አባላት አክብሮት አለኝ፡፡

በእርግጥ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ያልተከፋፈለ ኢሕ አ ፓ ወደሃገሩ ቢገባ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ንው፤ በጥይት በተደበደብንባት አገር፣ የሰውነት ከብር ተነፍገን በየጎዳናውና በየስርቻው በተጣልንባት አገር፤ ከሞትና ከስደት የተረፍነው አንገታችንን እንድንደፋ በተደረግንባት አገር… በአዳራሽ ውስጥ ተሰብስበን አንደበታችንን ከፍተን የ ኢ ህ አ ፓ አባል የነበርን መሆናችንን መናገር የቻልንበት ቀን!

ከመሳሪያና ከአመጽ በመለስም ላልተመለሱ የሐዝብ ጥያቂዎች መቆምና መስዋእትነት የከፈሉ ጓዶቻችን የሰጡንን አደራ መወጣት የሚያስችለን የታሪክ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ ይህ ሁኔታ እውን ይሆን ዘንድ ዝግጅትና ድፍረት ሰንቀው ከራሱ ከኢሐአዲግ ውስጥ የወጡትን መሪዎች ማመስገን ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ታዲያ ይህንን ሁኔታ በመጠቀም ጓዶቻችን በታሪክ ውስጥ ሊኖራችው የሚገባውን ቦታ እንዲያገኙ ማድረግና ለዲሞክራሲ፣ ለፍትህና ለነጻነት ለሚደረገው ሰላማዊ ትግል የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የሁላችን ሃላፊነት ነው ብየ አምናለሁ፡፡

ያም ሆኖ ዛሬ ኢትዮጵያ ከምን ጊዚውም በበለጠ ችግር ውስጥ ትገኛለች፤ በሃገርና በሕዝብ ላይ ኢሰባዊ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ ገና በሕግ የበላይነት ቁጥጥር ስር አልዋሉም፤ የሕዝብ መፈናቀል፣ ስደትና ሞት አልተገቱም፣ የተዘራባትን የዘረኝነትና የጠባብነት አራሙቻ ለመንቀልና ለማጥፋት በሚታትሩና እንዳይነቀልና እንዳይጠፋ በሚፈልጉ መሃል ግብግቡ ተጧጡፏል።

ሌብነትና ዝርፊያ ስሩን ሰዶ በመንሰራፋቱ በግለሰቦችና በቡድኖች የተዘረፈውን የሀገርና የሕዝብ ሃብትና ንብረት ማዳንም ከባድ ሆኗል። በጥቅሉ ይህች ሃገር ለሦስት አስርተ ዓመታት አካባቢ ባላሰለሰ ጥረት የተሰጣትን የቤት ሥራ ለማጠናቀቅና ጠንካራና ዲሞክራሲያዊት ሃገር ለመሆን ገና ረጅም ጉዞ ይጠብቃታል፤ ለዚህም የሁሉም ሕዝብ ተሳትፎ ያስፈልጋታል። ታዲያ የነበርንበት የፖልቲካ መስመርና ድርጅት ዘረኝነትን፣ ሌብንነትንና ኢፍትሃዊነትን እንድንጸየፍ የሚያስችለንን ስብእና የገነቡልን የኢሕአፓ ለጆች (ጭልጥ ብለው ራሳቸውንና እምነታቸውን ከለወጡት በስተቀር) በዚህ ጭንቅ ውስጥ ላለች ሃገራችንና ሐዝባችን አለን ለማለት ምን ይከለክለናል? እንደኔ እምነት አብዛኞቹ በኢሕአፓ የትግል መስመር ውስጥ የነበሩ ሰዎች በመርህ ላይ ልዩነት የላቸውም ብል የምሳሳት አይመስለኝም።

ዛሬ ከኢትዮጵያና ከሕዝብ ጎን ለመቆም የግዴታ በአንድ ድርጅት ውስጥ መሆን የለብንም፤ ከድርጅት አገርና ሕዝብ ይበልጣሉና ለእነርሱ የሚበጅ ከሆነ የድርጅትን ጉዳይ ወደጎን አድርገን በየፊናችንም ሆነን ኢትዮጵያን በማዳኑ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ለነገ የማይባል ተግባር ይመስለኛል፡፡ በእዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍም የግዴታ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆንን አይጠይቅም። አንድ የማይታበል ሃቅ ግን በውስጣችን አለ፤ እኛ የመርህ አንድነት አለን፤ የትም ፈጭተን ዱቄቱን ስናመጣው ለኢትዮጵያ የሚያድናት መድኃኒት እንጂ የሚጎዳት መርዝ እንደማይሆንባት እርግጠኛ መሆን ይኖርብናል።

ከመርህ በመለስ ያሉ ልዩነቶቻችን ከእኛ አልፈው አገርንና ሕዝብን እንዳይጎዱና እንዳያሳዝኑ የየበኩላችንን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። ዛሬ የግል የሃሳብ ነጻነትን ማክበር፣ ከመራራቅ ይልቅ ተቀራርቦ መወያየትና ለመግባባት ፈቃደኛ መሆን፣ መግባባት የማያስችሉ ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳን ትልቁን ስእል በመመልከት ልዩነቶቻችንን ማስተናገድ ግድ ይለናል።

አንዳንዶች ሲናገሩ እንደሚደመጡት፤ እድሜያችንን ታሳቢ አድርገን ከሁሉ ነገር ተገልለን በርቀት መመልከት ይገባናል ብየ አላስብም። ዕድሜ አካላዊ እርግውናን ሲያስክትል አእምሮአዊ ብልጽግናንም አብሮ ማምጣቱን ማሰብ ይጠይቃል፤ እኛ ለአገር የሚጠቅም ተዝቆ የማያልቅ የእውቀትና የልምድ ሃብት ያለን ዜጎች በመሆናችን ለሀገራችንና ለሕዝባችን እናስፈልጋለን። ይህንን ሃብታችንን ግን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይኖርብናል።

አመሰግናለሁ!

ክብር ለሰማእታት!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

ሕዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም

የቀድሞ የኢሕአፓ አባላት ስብሰባ ላይ ያቀረብኩት