የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር ኦስማን አቡከር ዱቤ

የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር ኦስማን አቡከር ዱቤ

የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮቹ በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ተሳትፈዋል ሲሉ የወጡ ዘገባዎች ትክክል አይደሉም ሲል አስተባበለ።

መንግሥት ይህንን ምላሽ የሰጠው የአገሪቱ የቀድሞ ከፍተኛ የደኅንነት ባለስልጣን ከጥቂት ወራት በፊት ኤርትራ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሶማሊያ ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ተገድለዋል ካሉ በኋላ ነው።

አብዲሰላም ጉሌድ የተባሉት የሶማሊያ ብሔራዊ የደኅንነትና መረጃ ተቋም የቀድሞ ምክትል ኃላፊ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ሳያቀርቡ ለአንድ የግል ሬዲዮ “400 የሚደርሱ የሶማሊያ ወታደሮችበኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በቅርቡ በተካሄደው ውጊያ ተገድለዋል ሲሉ ተናግረው ነበር።

የቀድሞው ባለስልጣን ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ጋር ተሰልፈው ሲዋጉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተገድለዋል ያሏቸው የሶማሊያ ወታደሮች በ20 እና በ30 ዓመት ዕድሜ ውስጥ የነበሩ ናቸው።

ይህ የግለሰቡ ንግግርም በተለያዩ የሶማሊያ ክፍሎች ውስጥ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፤ ልጆቻቸው ለወታደራዊ ስልጠና ወደ ውጪ አገራት የሄዱ ቤተሰቦች ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ የአገሪቱ መንግሥት ልጆቻቸው የት እንዳሉና በሕይወት ይኑሩ ወይም ይሙቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ነገር ግን የሶማሊያው የማስታወቂያ ሚኒስትር ኦስማን አቡከር ዱቤ የተባለውን ውድቅ በማድረግ የሶማሊያ ኃይሎች በቅርቡ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ውጊያ ላይ አልተሳተፉም ብለዋል።

ሚኒስትሩ ከቢቢሲ የሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንዳሉት ከዚህ ቀደምም የሶማሊያ ወታደሮች በሊቢያና በአዘርባጃን ውስጥ በተካሄዱ ውጊያዎች ውስጥ ተሳትፈዋል ተብሎ ቢወራም ኋላ ላይ ወሬው ሐሰተኛ መሆኑ ተረጋግጧልብለዋል።

ጨምረውም የሶማሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያው ግጭት ውስጥ ተሳትፈዋል የተባለው ወሬ ሐሰተኛ ነው ብለዋል።

ይህንን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ አስካሁን ያሉት ነገር የለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በህወሓት ኃይሎች ላይ በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማከሄድ ከጀመረ በኋላ ከ50 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ግጭቱን በመሸሽ ወደሱዳን የገቡ መሆኑ ይነገራል።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥታት ቢያስተባብሉም የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል በተካሄደው ግጭት ውስጥ መሳተፋቸውን የሚገልጹ ወገኖች አሉ።

በትግራይ ክልል የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ በአሁኑ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች የሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል በማለት እያስጠነቀቁ ነው።

ቢቢሲ