22 ጥር 2021

ኬንያ ኃይለስላሴ ጎዳና

አፍሪካ ክትባቱን ለማግኘት ሳምንታት ወይም ወራት ልትጠብቅ ግድ ይላታል፡፡

ይህን ያሉት ለአፍሪካ ክትባቱን ለማስገኘት እየጣሩ ያሉ ድርጅቶች ናቸው፡፡

እስከአሁን 900 ሚሊዮን ጠብታ ተገኝቷል፡፡ ይህ የተገኘው ከተለያዩ አገራትና ለጋሾች በተደረገ ልገሳና ርብርብ ነው፡፡

900 ሚሊዮን ጠብታ የአፍሪካን 30 ከመቶውን ለመከተብ እንኳ የሚበቃ አይደለም፡፡ የአፍሪካ ሕዝብ ብዛት አንድ ቢሊዮን ሦስት መቶ ሚሊዮን ደርሷል፤ አሁን፡፡

ይህን ያህል ሕዝብ ያላት አህጉር አፍሪካ በቂ ክትባት ሳታገኝ ታዲያ ሀብታም አገራት ግን ክትባቱን ከወዲሁ እየገዙ ማጠራቀም ይዘዋል፡፡

ክትባቱን ለመግዛት ስምምነት መፈረም የጀመሩት ገና ድሮ ነው፡፡ ክትባቱ ሳይፈለሰፍ፡፡ ተስፋ ሰጪ ምርምሮችን በተመለከቱ ቁጥር ቶሎ ብለው ያስፈርማሉ፡፡ ‹ቅድሚያ ለኔ› እያሉ፡፡

ይህም ማድረግ የማይችሉ የአፍሪካ አገራት እየተቁለጨለጩ ነው የቆዩት፡፡

ሀብታም አገራት ክትባቶቹ መመረት ሲጀምሩ እየገዙ ማጠራቀማቸው ብቻም ሳይሆን ለድሀ አገራት እጃቸውን ለመዘርጋት ዳተኞች ሆነዋል፡፡

በአጭሩ አፍሪካና ሌሎች የኢሲያ ድሀ አገራት ገሸሽ ተደርገዋል፡፡

ለአፍሪካ ክትባቱ እንዲርቅ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ያልተቆራረጠ የማቀዝቀዣ ሰንሰለት(Cold Chain) አለመኖር ነው፡፡

ያልተቆራረጠ የማቀዝቀዣ ሰንሰለት ማለት አንድ ክትባት ከምርት ጀምሮ ለማጓጓዝ ወደ አውሮፕላን እስኪሄድ፣ በአውሮፕላን እስኪጫን፣ ከአውሮፕላን ሲራገፍ እና ለሕዝብ እስኪዳረስ መጋዘን ሲከማች ከመነሻ እስከ መድረሻ እጅግ ቀዝቃዛ በሆነ ቅዝቃዜ ብልቃጥ የማስቀመጥ ሂደት ነው፡፡

ክትባቶቹ የሚቀመጡበት የማቀዝቃዣ ዓይነት ውስብስብ መሆን የክትባት ሥርጭቱን ፈታኝ አድርጎታል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ስኬታማ የተባሉት ፋይዘርም ሞደርናም ከፍተኛ ማቀዝቀዣ የሚፈልጉ የክትባት ዓይነቶች ናቸው፡፡

ይህ ለአፍሪካ አገራት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል፡፡ አንድም ክትባቱ አልተገኘ፣ ሁለትም ማጓጓዣና ማስቀመጫም አልተበጀ፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ባለፈው ሳምንት ‹ዓለም የሞራል ልእልናዋ ላሽቋል፤ ለዚህ ስግብግብነት ዋጋ እየከፈሉ ያሉት ደግሞ በድሀ አገራት የሚኖሩት ናቸው› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ ይህን ያሉት ሀብታም አገራት ክትባቱን ከእቅፋቸው ለመልቀቅ ባለመፍቀዳቸው ነው፡፡

በዚህ ረገድ ዶ/ር ቴድሮስ ብቻም ሳይሆኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፍትሐዊ ክፍፍል ይኑር ሲሉ ጥሪ እያሰሙ ነው፡፡

መድኃኒት ከተገኘ እስከዛሬ ድረስ በ49 አገራት 40 ሚሊዮን ጠብታዎች ተሰጥተዋል፡፡ በአፍሪካ ግን እስከዛሬ 25 ጠብታ ብቻ ነው የተሰጠው፡፡

ይህ ቁጥር በእርግጥም የድህነትን አስከፊ ገጽታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስለዚህ ሀቅ ሲናገሩ፣ ‹‹…25 ሚሊዮን አላልኩም፣ 25ሺም አላልኩም፣ 25 ጠብታዎች ብቻ›› ሲሉ ነው ነገሩ እንዴት አሳሳቢ እንደሆነ የገለጹት፡፡

እስከአሁን ከዋና ዋናዎቹ የክትባት ዓይነቶች አንዳቸውም በአፍሪካ ምድር ለሰው አልተሰጡም፡፡

በአውሮፓ ግን የመጀመርያው ጠብታ ከ2 ወር በፊት ነው የተጀመረው፡፡

ይህ የሀብታምና ድሀ አገራትን ልዩነት እና የዓለም ሥርዓት አድሏዊነትን ፍንትው አድርጎ ያሳየ አጋጣሚ ነው፡፡

ክትባት በደቡብ አፍሪካ

ሰልፍ እየጣሱ የሚገቡ አገራት

ዘ ፒፕልስ ቫክሲን አሊያንስ የሚባል አንድ የመብት ተቆርቋሪ ቡድን ባወጣው መረጃ የዓለምን ሕዝብ 14 ከመቶ ብቻ የሚሸፍኑ ሀብታም አገራት 53 ከመቶ የሚሆነውን ክትባት በእጃቸው አስገብተዋል፡፡

ይህ አሀዝ የ2012 የሞደርና ክትባት ምርትን እና 96 ከመቶ የሚሆነውን የፋይዘር ቀጣይ ወራት ምርትን ይጨምራል፡፡

በዚህ መረጃ መሰረት ካናዳ ከብልጹግ አገራት በመጀመርያ ረድፍ የምትገኝና ክትባቱን በገፍ የወሰደች አገር ናት፡፡

ካናዳ የሰበሰበችው የክትባት መጠን እያንዳንዱን ካናዳዊ 5 ጊዜ ደጋግሞ ለመከተብ የሚያስችል ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ የብልጹግ አገራት ራስ ወዳድነት አፍሪካ ለሀብታም አገራት ሸቀጥ ማራገፍያነት ካልሆነ ውልብ የምትልባቸውም አትመስልም፡፡

ይህ ነገር በፈረንጆቹ 1990ዎቸ አካባቢ ለኤች አይቪ ኤድስ ታማሚዎች ዕድሜ ማራዘምያ በአሜሪካ መድኃኒት የተገኘ ወቅት የሆነውን የሚያስታውስ ነው፡፡

ያን ጊዜ አፍሪካ ምንም እንኳ አብዛኛዎቹ ታማሚዎች የሚገኙባት አህጉር የነበረች ቢሆንም መድኃኒቶቹን ለማግኘት ግን 6 ዓመታትን ወስዶባታል፡፡

ይህም የሆነው ሀብታም አገራት መድኃኒቱ ከሚያስፈልጋቸው በላይ ማጠራቀም ስለጀመሩ ነበር፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ መድኃኒቱ የሚመረትበት ዋጋ ሰማይ መንካቱ ነው፡፡

በ10 ዓመት ውስጥ በአፍሪካ 12 ሚሊዮን ሰዎች ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ ሞተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ መድኃኒቱ በወቅቱ ደርሶ ቢሆን ብዙዎችን ዕድሜ ማራዘም በተቻለ ነበር፡፡ መድኃኒቱ የደረሰው ግን ከ6 ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ነበር፡፡

ዩኤን ኤይድስ ዳይሬክተር ዊኒ ቤያንዪማ ለኮቪድ ክትባት ፍትሐዊ ክፍፍል እንዲኖር ከሚታገሉት ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡

‹‹እኛ መድኃኒት አምራቾች ይክሰሩ አይደለም እያልን ያልነው፡፡ ልክ ዕድሜ ማራዘምያ በሕዝቦች የተባበረ ጥረት ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለው ይህንንም እንደዚያ እናድርግ ነው የምንለው›› ብለዋል ለቢቢሲ፡፡

ከኤች አይ ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ባደረጉት ከፍተኛ ግፊት አገሮች የዕድሜ ማራዘምያ እንዲመረት በመፍቀዳቸውና መድኃኒት አምራቾች ፍቃድ በመስጠታቸው ዋጋው ሊወርድ ችሏል፡፡

ለምሳሌ አንድ የዕድሜ ማራዘምያ መድኃኒት ለመግዛት የዓመት ወጪ መጀመርያ አካባቢ ከ10ሺህ ዶላር በላይ ነበር፡፡ በኋላ ነው ወደ 100 ዶላር ነው ዝቅ እንዲል የተደረገው፡፡

ዊኒ አሁንም የሚሉት ለኮቪድም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪው በትርፍ ብቻ እንዳይቅበዘበዝና ሰብአዊነት እንዲያስቀድም ነው እየጠየቁ ያሉት ዊኒ ቤያንዩማ፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ እንደተናገሩት አንዳንድ አገሮች ስለ እኩልነትና ፍትሐዊ ክፍፍል እያወሩም ራሳቸውን ያስቀድማሉ፡፡

ብልጹግ አገራትና ኩባንያዎች የሁለትዮሽ ስምምነቶቻቸውን ውስጥ ውስጡን ይፈራረማሉ፡፡

በዚህ የተነሳ ለድሀ አገራት ክትባቱን ያደርሳል የተባለው ‹ኮቫክስ› ፕሮጀክት በአገሮችና በመድኃኒት አምራቾች ገሸሽ እየተደረገ ነው፡፡

‹‹ወረፋ ሳይጠብቁ የሚገቡ አገሮች አሉ፤ መድኃኒት አምራቾች ደግሞ ዋጋ እየጫኑ ነው›› ሲሉ ወቅሰዋል ዶ/ር ቴድሮስ፡፡

በቫክሲን አሊያንስና የዓለም ጤና ድርጅት ጥምረት የሚሠራው ኮቫክስ ክትባቱን በፍትሐዊነት ለዓለም ለማድረስ የተቋቋመ ነበር፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት የክትባት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ሪቻርድ ሚጎ እንደተናገሩት ደግሞ አብዛኛዎቹ አገሮች ከመድኃኒት አምራቾች ጋር ስምምነት የተፈራረሙት መድኃኒቱ ገና ፈዋሽ መሆኑ ሳይረጋገጥና ወደ ምርት ሳይገባ ነው፡፡

‹ለምን ኮቫክስ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አልቻለም?› ተብለው በጋዜጠኞች የተጠየቁት ዶ/ር ሪቻርድ ገንዘብ ማፈላለግ የመጀመርያው ተግባሩ ስለነበረ ነው ብለዋል፡፡

እስካሁን ለድሀ አገራት ክትባቱን ለማድረስ እንዲቻል በኮቫክስ በኩል 6 ቢሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ተችሏል፡፡ የሚያስፈልገው ገንዘብ ግን 8 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡

በዚህ ገንዘብ 92 የሚሆኑ ድሀና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራትን ለማገዝ ታስቧል፡፡

እስከአሁን ለነዚህ 92 አገራት የሚሆን 2 ቢሊዮን ዶዝ ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን 600 ሚሊዮኑ ደግሞ ለአፍሪካ የሚደርሳት ነው፡፡

የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ከአበዳሪዎች የተዘጋጀ 7 ቢሊየን ዶላር ፈንድ እንዲያመለክቱ መክሯል፡፡ ይህም 270 ሚሊዮን ጠብታዎች ለማግኘት ይረዳል፡፡

ለድሀ አገራት ፈተናው ክትባቱን ማግኘት ብቻ አይደለም፡፡

የማጓጓዙና ለክትባቱን የማከማቻ ምቹ ቦታ ማግኘት እጅግ ፈተኛ ነው፡፡

ለምሳሌ ፋይዘር ክትባት 70 ዲግሪ ከዜሮ በታች በሆነ ማቀዝቀዣ ነው መቀመጥ ያለበት፡፡ ይህን ማሳካት ለየትኛውም ድሀ አገር እንደሚታሰበው ቀላል ነገር አይደለም፡፡

ለጊዜው ዩኒሴፍ በኮቫክስ በኩል ይህን የማጓጓዙን ሥራ እንዲወጣ አደራ ተጥሎበታል፡፡

ዩኒሴፍ ወትሮ የልጆችን ክትባቶች በማዳረስ ነው የሚታወቀው፡፡

አሁን ያን ልምዱን ተጠቅሞ የዚህን የጉዞ መሠረተ ልማትና ግብአት (ሎጂስቲክ) በማጓጓዝ ከባድ አደራ የተሰጠው ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ካሳካቸው ሁሉ እጥፍ የሚሆን አቅሙን የሚጠይቅ ነው፡፡

ክትባቱ ለብልጹግ አገራት ፊት አልሰጠም፡፡ሰዎችን በሀብት ደረጃ አልለየም፡፡ አሜሪካ ምናልባት በሚቀጥለው ወር በተህዋሲው የሟቾች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን ትደርሳለች፡፡ ይህ ይሆናል ያለ ማንም አልነበረም፡፡

አፍሪካ ክትባቱ ቢዘገይባትም ለጊዜው ሳይንስ ባልተረዳው መንገድ ክትባቱ የጨረሰባት ዜጋ ብዛት ግን ከተፈራው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ተፈጥሮ እያካካሰች ይሆን?