ታጠቅ መ ዙርጋ

23 January 2021

በአንድ ስሙን በማላስታውሰው ከህወሃት ሚዲያ አውታሮች አንዱ ከአንዲት እንስት ጋዜጠኛ ስለትግላቸው ወቅት ሲወያዩ ‘በህይወት በጠላት እጅ ላለመውደቅ አንድም የህወሃት ታጋይ መርዝ በኪሱ ሳይዝ አይንቀሳቅስም ነበር፤ ከመማረኩ/ማረኳ በፊት መርዝ ውጠው ይሞቱ ነብር’ አሉ፡፡

ታዲያ በጀግናው መከላኬያችን ከዝንጅሮ ገደል እጅ ከወርች ከመያዛቸው በፊት ለምን መርዝ አልዋጡም? ወደ ሠፈሩበት ቦታ ሲሸሹ የመርዝ እንክብሎቹን እቤታቸው ረስቷቸው ሂደው ይሆን? እንክብሎቹ በዋሻው አካባቢ ከኪሳቸው ወድቀውባቸው ይሆን? የሚገል እንክብል ውጬ ዛሬ ከምሞት የቀረኝ ዕድሜ በከርቸሌ ላሳልፍ ከሚል ይሆን? በኢትዮጵያ በትረ አገዛዝ የፍጹም ፈላጭ ቆራጭ ሥልጣን ማማ ከጨበጡ በኋላ በጠላት እጅ ብወድቅስ ከሚል ሥጋት ስለተላቀቁ ፤ የመርዝ እንክብሎች መግዛትን ስለአቆሙ ይሆን?

በወጣትነት ዕድሜያቸው ያወሩትን ዓይነት ቆራጥ አቋም ከነበራቸው እንዴት ወደ ዘጠና በተቃረበ ዕድሜያቸው በውርደት መያዝን መረጡ? የመርዝ እንክብሉ ባይኖራቸው እንኳ እንዴት ተዋግተው አልሞቱም ወይም በያዙት መሳርያ ነብሳቸው ከስጋቸው ማላቀቅ ፈሩ? ወይስ የተለመደ የህወሃት ውሽትና ጉራ ፍጆታ ነው ያንን ያሉት ? ወይስ በመርህ ሳይሆን በምኞት ለምን ኢ ሕ አ ፓዎች አንመስልም በማለት ያወሩት ይሆን?

ስላለፈው ገድላችንና ማንነታችን ስናውራ ፣ ያኔ የሚያውቀኝ የለም ፣ የሚያጋልጠኝ የልም ፣ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ሁኔታ ተከስቶ እፈተን ይሆናል ሳንልና ሳንጠነቀቅ እንዳሻን የምናውራቸው ነገሮች የትላንቱን ድብቅ ማንነታችንና የትላንቱን ውሽታምነታችን ያጋልጣል፡፡

በርግጥ :- ውሸት፣ ጉራ፣ የድንቁርና ድፍረት፣ ኩረዣ ወዘተርፈ የወያኔዎች ሥነምግባር <ethos> ነው ፡፡ በውጭ ሚዲያ ለቃለመጠይቅ ሲጋበዙ ፤ We have ( collective leadership, the office of the Ombudsman, social welfare/safety net,democratic constititution and institions etc) እያሉ ይገልጹ ነበር፡፡ ስለሚናገሯቸው ነገሮች ጽንሰ ሃሳብና ትርጉም ሳያውቁ ፤ከከበርቴውና ከሶሻሊስቱ ርዕዮት ዓለም የቃረሙትን ጠላፊና የሚማርኩ ቃላትና ሃረጎች (fancy and catchy words and phrases) በመጠቀም በዕውቀት የተካሃኑ ያስመስሉ ነበር ፡፡ መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ እንደሚባለው፡፡