የአቶ ጌቱ ታደሰ አጭር የህይወት ታሪክ።

አቶ ጌቱ ታደሰ ከአባታቸው ከአቶ ታደሰ ውቤና ወ/ሮ መዓዛ ካብትህይመር በሲዳሞ ጠቅላይግዛት በይርጋዓለም ከተማ እ.. አቆጣጣር ግንቦት 5/1960 ተወለዱ።

       አቶ ጌቱ እድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ በይርጋዓለም ከተማ በቀድሞ መጠሪያው በራስ ደስታ ዳምጠው ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል  በመማር የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
        
አቶ ጌቱ ታደሰ እምሮ ብሩህና ታታሪ ተማሪ ስለነበሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ክፍለ ሀገሩ የሚሰጠውን የመግቢያ ፈተና በሚገባ ውጤት በማለፍ በጀነራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመከታተል በጥሩ ውጤት አጠናቀቁ።       

  ምንም እንኳን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ የመማር ፍላጎት ቢኖራቸውም በሀገሪቱ በጊዜው ይካሄድ የነበረውን እንቅስቃሴ በመደገፍና በመቀላቀል ወደትግሉ በመግባት ከሚወዷት አገራቸው እስከተሰደዱበት እለት ድረስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፖርቲ (ኢሕአፓ) ጎን በመሰለፍ ሰፊ አስተዋጽዖ አድርገዋል።          

አቶ ጌቱ በ1980 ወደ ጣልያን በመጓዝ በመርከብ ላይ የስራ አገልግሎት በመቀጠር (Quarter Master) በመሆን ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደ አሜረካ በመግባት ከቀድሞ የትግል አጋሮቻቸውና የሚወዱትን ድርጅታቸውን ኢሕአፓ እንደገና በመቀላቀል ትግላቸውን ቀጠሉ።

በአሜሪካ ቆይታቸው በሞንት ጎመሪ ኮሌጅ የኮምፕዩተር ሳይንስ AA አሶስየት ዲግሪ ከመመረቁ ባሻገር በካቶሊክ ዩንቨርስቲ በJohndon and Johnson  በዩሴ ፓተንት ኦፊስና በማርየት ሆቴል በማመላለሻ አገልገሎት ሰራ ላይ በመሰማራት ከዋናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ዓላማው በሌላ የግል ችግሮች ሳይዘናጉ ለድርጅቱና ለጓዶቹ በለጋ እድሜ ጥርሱን የነቀለበትን ድርጅት አሕአፖ በሚያካሂደው መራራ ታግል አኩሪ ተሳትፎ አድርጎ በኢትዮጵያ የትግል ታሪክ አሻራውን አሳርፎ አልፏል።


          
1990 መባቻዎች አንስቶ ከኢሕአፖ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት በሚታወቀው የኢትዮጵያ ጥናትና ህትመት ማዕከል ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ  መጻሕፍት ቤቱን በማደራጀት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ብዙ ደክሟል። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ቀደምት የፖለቲካ ፖርቲ እንደመሆኑ ከጅምሩ ያሳለፏቸው የአቋም ሠነዶች በጥንቃቄ መያዝ የሚገባቸው በርካታ ጽሑፎችና የድምፅና የምስል ቅጂዎች ወዘተ በቀንና በርዕስ ዘመናዊ ፋየሊንግ ሲስተም በመከተል የድርጅቱን የእለት ተእለት ስራ ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረግ ዋናውን ሚና ተጫውቷል። በተለይም የማህበራዊ ሚድያና ኤሌክትሮኒክስ መረጃ ልውውጥ ባልነበረበት ጊዜ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብንና የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎችን ተደራሽ የሆኑ ዜናዎችና ደብዳቤዎች አስተማሪ ጽሁፎችና ፖሊሲዎች ማኒፌስቶዎች ከህትመት እስከ መጠረዝ ተባዝተው አስከ መሰራጨት ያለውን ሥራ ያለ ጌቱ ታደሰ አይጠናቀቅም ነበር።


        
አቶ ጌቱ ታደሰ ወደ ጽ/ቤት የሚመጡ ጓዶችንና ደጋፊዎች በማስተናገድ ጋባዥ በሆነ አቀባበሉ በፈገግታ የሚቀበል ከመናገር በመቆጠብ ማዳመጥ የሚመርጥ ትጉህ  ሁሉንም ሰው በእኩል ደረጃ የሚመለከት ክፉ ቃል የማይወጣው ለክስ የማይቸኩል አሸማጋይነትና የአግባቢነት ተፈጥሮአዊ ፀጋ የተላበሰ በስነ ስርዓት የታነፀ ሰው ነበር።


አቶ ጌቱ ታደሰ ረዘም ላለ ጊዜ የጤና መታወክ ቢገጥመውም በጽናት ሲታከም ቆይቶ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ በሚለው የፈጣሪ ቃል በዕለተ ሐሙስ  በJanuary 21/2021 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
       
በዚህ ሁሉ አመታት ከጎኑ ሆናችሁ ችግሩንና መከራውን ለተካፈላችሁ ለረዳችሁት ቤተሰቡንም ላጽናናችሁ እንዲሁም በዚህ የስንብት ሰዓት በዚህ አስቸጋሪ የኮሮና ዘመን አገር አቋርጣችሁ ከሩቅም ከቅርብም ለተገኛችሁት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን።


     
ቸሩ ፈጣሪያችን ነፍሱን ከገነት ያኑርልን።


              
ከቤተሰቦቻቸው።