ትግራይ እንዴት ሰነበተች? (የመጨረሻ ክፍል)

January 22, 2021

– የአዲግራት የሁለት ሰዓታት ቆይታ

– የትግራይ ተጓዦች በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ ምን ገጠማቸው? 

በተስፋለም ወልደየስ

ዕኩለ ቀን ሆኗል። ቢጫና ነጭ ቀለም የተቀቡት እና በዋናው መንገድ መሃል ባለው አካፋይ ላይ በተርታ የተተከሉት የአዲግራት የመንገድ መብራቶች አይን ይስባሉ። በመንገዱ ላይ የሚታዩት መኪኖች ቁጥር አነስተኛ ነው። በመንገድ ዳር ቆመው ተሳፋሪ የሚጠብቁ ባጃጆች አለፍ አለፍ ብለው ይታያሉ። በከተማይቱ ዳርቻ ያለውን ይሄን መሰሉን ነገር እያስተዋልኩ እያለ መኪናችን ድንገት ቆመ። ከእኛ ጋር በስተኋላ ተቀምጣ የነበረችውና ከዕዳጋ ሐሙስ በኋላ ወደ ጋቢና የተዛወረችው ወጣቷ ተሳፋሪ ነበረች መኪናውን ያስቆመችው። ለሹፌሩ የቤተሰቦቿን ቤት አቅጣጫ ከጠቆመችው በኋላ ከዋናው መንገድ ታጥፈን ወደ ውስጥ ገባን። 

ዝምተኛዋን ወጣት ተጓዥ አውርደን ወደ ዋናው መንገድ ተመለስን። ብዙም ሳንሄድ አጠገቤ የተቀመጠው የጋራዥ ሰራተኛ “ተመልከት የኤርትራ ወታደሮች” አለኝ። አይኖቼ የመንገዱን ግራ እና ቀኝ በፍጥነት አሰሱ። በቀላሉ ልለያቸው አልቻልኩም። “እነዚያውልህ” ብሎ ወጣቱ ከመኪናችን በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ እኛ ፊታቸውን አድርገው የሚጓዙ ሁለት ሰዎች አሳየኝ። ከመቅጽበት እጄ ላይ የነበረውን ሞባይሌን ወደ እነርሱ አቅጣጫ ለመደገን ሳነሳ፤ አጠገቤ የተቀመጠችው ተለቅ ያለችው ሴት እጄን አፈፍ አድርጋ ይዛ ከመቀመጫው ጋር ጠፍንጋ ያዘችው። “ስታነሳ ቢያዩህ ይገሉናል” በማለት በአይኖቿ ጭምር ፎቶ እንዳላነሳ ለመነችኝ። የሰው ህይወት አደጋ ላይ ከማጋለጥ ቢቀርብኝ ይሻላል ብዬ በእሺታ አንገቴን አወዛወዝኩላት።   

በዚህ ምክንያት ፎቷቸውን ማንሳት ባልችልም፤ በነጻነት ዘና ብለው በመንገድ ዳር እያወጉ የሚጓዙትን ሁለት ወታደሮች ግን አተኩሬ ነገረ ስራቸውን ከመመልከት የከለከለኝ አልነበረም። ሁለቱም አረንጓዴ ወታደራዊ ልብስ ለብሰው፤ ጠመንጃቸውን በትከሻቸው አንግበዋል። ወታደራዊ የደንብ ልብስ አለባበሳቸው እንደነገሩ ነው። ከወታደር ይልቅ ታጣቂ ይመስላሉ። የተጫሙት ያው ከመቐለ ጀምሮ ስሰማው የነበረው፤ በተለምዶ የታጋዮች ጫማ የሚባለው የኮንጎ ላስቲክ ጫማ ነው። መኪናችን አልፋቸው እስክትሄድ ድረስ ስመለከታቸው ቆየሁ። 

ሹፌራችን ወደ ከተማ መሃል በመንዳት ፈንታ፤ ዋናውን መንገድ ተከትሎ በቀጥታ ወደ ተዘረጋው ኮብል ስቶን ሲያመራ ቀልቤን ሰብስቤ ቀጣዩን ነገር መከታተል ቀጠልኩ። አጠገቤ የተቀመጠችው ሴት ለሹፌሩ አቅጣጫ እያመላከተቸው ወደ ቤተሰቦቿ ቤት አቀናን። በመንገዳችን ላይ በነበረን ጨዋታ፤ ሴትዮዋ የቤተሰቦቿ ሁኔታ በጣም እንዳሳሰባት ተረድቻለሁ። በትግራይ ውጊያ ተጀምሮ የስልክ አገልግሎት ከተቋረጠ አንስቶ የቤተሰቦቿን ደህንነት ማወቅ ባለመቻሏ ተጨንቃለች። መኪናችን ቤታቸው ደጃፍ ደርሶ ሲቆም፤ ውቅሮ ላይ ለቤተሰቦቿ በፌስታል የገዛችውን ቆሎ አንጠልጥላ እመር ብላ ወረደችና የውጭውን በር አንኳኳች። 

መንገድ ዳር ቆመው የነበሩ ጎረቤቶቿ የሆኑ አራት እናቶች፤ እርሷን ሲመለከቱ የተገረሙ መሰሉ። የናፍቆቷን ያህል እያንዳንዳቸውን እያገላበጠች ሳመቻቸው። በር እንድትከፍት የተላከች ታዳጊ ልጅ ከእኛ ጋር የመጣችውን ሴት ስትመለከት፤ ስሟን እያነሳች፣ መምጣቷን በሚያበስር ከፍ ያለ ድምጽ ቤተሰቦቿን መጣራት ጀመረች። የሴትዮዋ እህት የሰሙትን ባለማመን ተንደርድረው ወደ በር ወጡ። ከዚያ በኋላ ለደቂቃዎች ተቃቅፎ መላቀስ ሆነ። በሁሉም ፊት ላይ የናፍቆት እና የስጋት ሰቀቀን ይነበባል። 

ሰላምታው እና “እንዴት ነሽ” መባባሉ ጋብ ሲል፤ “መቐለ እንዴት ነች? እናንተ እንዴት ናችሁ” የሚል ጥያቄ ተከተለ። አብራን የተጓዘችው ሴት ለቤተሰቧ ስትሰጋ እንደከረመችው ሁሉ፤ እነርሱም የእርሷ ነገር ሲያስጨንቃቸው ነው ጊዜውን የፈጁት። የትግራይ ሰው የራሱን አካባቢ አስጨናቂ ነገር ወደ ጎን አድርጎ፤ የሌላውን ደህንነት የሚያጠያይቀው ነገር በተለያየ ቦታ ገጥሞኛል። ራሳቸው ያሉበትን ሁኔታ በአንጻራዊነት እንደተሻለ የሚወስዱት የየከተሞቹ ነዋሪዎች፤ ሀሳባቸው የጸጥታም ሆነ ሌሎች ችግሮች ጸንቶባቸዋል ብለው ለሚያስቧቸው ቦታዎች ነው። ለሴትዮዋ ቤተሰቦች በመቐለ ሁሉም ነገር ሰላም መሆኑ ከተነገራቸው በኋላ፤ “ምሳ ብሉ፤ ቡና ጠጡ” ሲሉ ጋበዙን። “ከተማ ጉዳይ አለን” በሚል ሰበብ ተሰናብተን ወደ መሃል ከተማ ሄድን። 

በከተማ መሃልም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉ መንገዶች ስንዘዋወር ያስተዋልኩት ነገር፤ ከመቐለ ጀምሮ ባሉ ከተሞች ላይ የሚታየው መፋዘዝ በአዲግራት ላይ ጎልቶ እንደሚታይ ነው። በርካታ መኪኖችን የሚያስተናግዱት መንገዶቿ ላይ የሚታዩት ተሽከርካሪዎች በቁጥር አነስተኛ ናቸው። በትግራይ ክልል የነበረው ውጊያ መጠናቀቁ በይፋ ከተነገረ ከወር በኋላም በርካታ አገልግሎት መስጪያዎች እና የንግድ መደብሮች በራቸውን እንደጠረቀሙ ናቸው። ጭርታው ብርቱ ነው። 

በአዲግራት በመንገዴ ላይ እንዳየኋቸው ከተማዎች የውጊያው ጉልህ ምልክቶች አይታዩም። የተቃጠሉ ወይም የተጎዱ ተሽከርካሪዎችም አልተመለከትኩትም። ምናልባት እኔ ከመድረሴ በፊት በነበሩት ጊዜያት ተነስተው እንደው አላውቅም። በመጀመሪያ አፍታ፤ በጨረፍታ የቃኘኋቸው በከተማይቱ ያሉ ህንጻዎች የመስታወት መሰባበር ቢያጋጥማቸውም በአንጻራዊነት በደህና ሁኔታ ላይ ያሉ ይመስላሉ። 

አዲግራትን ከምሳ በኋላ ይበልጥ ተዟዙሮ ለመመልከት እቅድ ይዤ፤ ሹፌሩን እና የጋራዥ ሰራተኛው “ጥሩ ምግብ አለበት” ወዳሉበት ቦታ አብሬያቸው ሄድኩ። ወደ ምግብ ቤቱ የሚወስደው፤ የኮብል ስቶን መንገድ በመሃል ከተማ ካየሁት ይልቅ በተሻለ እንቅስቃሴ ያለበት ነው። በርከት ያሉ ባጃጆች በመንገዱ ላይ ይመላለሳሉ። 

ከመንገዱ ግራና ቀኝ ባሉ እና በተዘጉ የንግድ መደብሮች ደጃፍ፤ አልባሳት እና ሌሎች ሸቀጦችን የደረደሩ ነጋዴዎች በቁጥር በርከት ብለው ይታያሉ። ዘንቢል እና ፌስታል ያንጠለጠሉ ሸማቾች ቁጥርም የሚናቅ አይደለም። ቦታው የከተማይቱ ዋና የመገበያያ ቦታ እንደሆነ የጋራዥ ሰራተኛው ነገረኝ። እኛ ወደ ቦታው ከመሄዳችን ከሁለት ሳምንት በፊት ግን ይሄም አካባቢ በጭርታ የተዋጠ እንደነበር አከለልኝ። 

ገበያው ጎን ካለው፤ ለምሳ ከተመረጠው ምግብ ቤት ደጃፍ መኪናችንን ስናቆም፤ አንድ ሸበቶ አባት ወደ መኪናችን ተጠጉና ከሹፌራችን ጋር በትግርኛ ወግ ጀመሩ። ከሹፌራችን ጋር ለደቂቃዎች ሲጠያይቁ ቆይተው፤ አንድ ነገር ለማሳየት ከደረት ኪሳቸው የማስታወሻ ደብተራቸውን መዘዙ። ለካንስ እንደምንጓዝባት መኪና አይነት ተሽከርካሪያቸው በኤርትራውያን ወታደሮ ተወስዶባቸው፤ በመንገድ ላይ አይተናት እንደሆነ እየጠየቁ ነው። ማስታወሻ ደብተራቸው ደግሞ የመኪናቸው የታርጋ ቁጥር ተመዝግቦ የተያዘባት በመሆኗ፤ ከዚያ ላይ እያነበቡ ለእኛ ለማስገልበጥ ነበር አወጣጣቸው። በአዲግራት የስልክ አገልግሎት ባይኖርም፤ ድንገት በቀጣይ ቀናት ከተከፈተ ያየነውን እንድንነግራቸው ስልክ ቁጥራቸውን አጻፉን። 

ብርማ ቀለም እንዳለው የነገሩን መኪናቸው፤ በኤርትራውያን ወታደሮች ከተወሰደ በኋላ እስከ ዕዳጋ ሐሙስ ባለው መንገድ ሲመላለስ እንደከረመ ያዩ ሰዎች ነግረዋቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መኪናውን አየሁ የሚል በመጥፋቱ፤ እንደ እኛ መኪና ሹፌር አይነት ሰው ሲያገኙ እያቆሙ ይጠይቃሉ – “መኪናዬን በመንገድ አይታችኋታል?” እያሉ። 

ኤርትራውያን ወስደዋቸዋል ስለሚባሉ መኪናዎች ጉዳይ ብዙ ሰምቻለሁ። ወደ አዲግራት እየመጣን እያለ፤ ሹፌራችን እና የጋራዥ ሰራተኛው አንድ ሲኖትራክ መኪና በመንገድ አይተው እንዴት በመደነቅ ሲነጋገሩ እንደነበር አይቻለሁ። ምን እንዳስገረማቸው ብጠይቃቸው፤ ወደ ኤርትራ ከመወሰድ የተረፈ ሲኖትራክ በማየታቸው እንደሆነ ነግረውኝ ነበር። ሸበቶውን አባት ተሰናበተን ከምግብ ቤት አረፍ እንዳልን ሹፌሩ እና የጋራዥ ሰራተኛው የእነርሱም መኪና ከመወሰድ የተረፈችው በሰዎች ጥረት እንደሆነ እየተቀባበሉ ያጫውቱኝ ገቡ።

ውጊያው የተጀመረ ሰሞን በአዲግራት የነበረው ሹፌራችን፤ ለክፉም ለደጉም በሚል መኪናውን ቤተክርስቲያን አቁሟት ወደ መቐለ ይጓዛል። ዝርፊያም ሆነ ሌላ ነገር ቢፈጠር ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሰዎች “ቤተክርስቲያንን አይደፍሩም” በሚል እሳቤ ነበር ይህንን ማድረጉ። ውጊያው አብቅቶ፣ መንገድ ሲከፈት፤ መኪናውን ፍለጋ ከጋራዥ ሰራተኛው ጋር ወደ አዲግራት ተመልሶ ይመጣል። መኪናውን ጠብቀው ያቆዩለት የሃይማኖት አባቶች፤ የኤርትራ ወታደሮች ከአንድም ሶስት ጊዜ መኪናዋን ሊወስዱ መምጣታቸውን እና በስንት እግዚኦታና ልመና ድርጊቱን ሳይፈጽሙት መቅረታቸውን እንደነገሩት አጫውቶኛል። 

በአዲግራት ከተማ እንደልብ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎች፤ ኤርትራውያን ከየሰው ላይ የወሰዱት እንደሆነ ሁለቱም አስረድተውኛል። ከምሳ በኋላ ከተማዋን ለማየት ዞር ዞር ባልንበት ጊዜም፤ የከተማይቱ ነዋሪዎች መኪናችንን በጥርጣሬ ሲመለከቱ አስተውያለሁ። በዚህ ሁኔታ መገረሜን ያየው ሹፌራችን፤ በውስጥ ለውስጥ ባሉ መንገዶች መኪናዋን አቁሞ ወጪ ወራጁን ሲያነጋግር፤ የሚያሳዩትን ገጽታ እንድመለከት ጋበዘኝ። ሹፌራችን የትግርኛ ቃላት ሲወረውር፤ በእርግጥም በመኪናዋ ውስጥ ያለነው ሰዎች ኤርትራውያን መስለናቸው ሲደነብሩ አይቻለሁ። እንዲህ ውስጥ ለውስጥ እያሳበረን ወደ አዲግራት ዩኒቨርስቲ የሚወስደው የኮብል ስቶን መንገድ ላይ ወጣን። 

ዩኒቨርስቲው በከተማይቱ በኤርትራውያን ወታደሮች ከፍተኛ ዘረፋ ከተፈጸመባቸው ቦታዎች አንዱ እንደሆነ ተነግሮኛል። ወታደሮቹ ፍራሽ ሳይቀር ከዩኒቨርስቲው ዘርፈው መውሰዳቸውን ከሶስት የተለያዩ ሰዎች ሰምቻለሁ። በአዲግራት ሆቴሎችን ጨምሮ በርካታ የንግድ ተቋማት መዘረፋቸውን ብሰማም፤ ባለው የጸጥታ ሁኔታ እና በነበረኝ የጊዜ እጥረት ምክንያት በአይኔ ተመልክቼ ያረጋገጥሁት ጥቂቶቹን ብቻ ነው። ከዋና መንገዶች አቅራቢያ ባሉ ቦታዎች፤ ውስጥ ለውስጥ በተዘዋወርኩባቸው አፍታዎች እንደ ሞባይል ቤት ያሉ ዘረፋ የተፈጸመባቸው የንግድ መደብሮች አይቻለሁ።    

ወደ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ቅጽር ግቢ ከሚያስገቡ በሮች ወደ አንደኛው ስንጠጋ በጥበቃ ላይ ያለ የመከላከያ ሰራዊት አባል ተመለከትኩ። በአካባቢው ብዙም እንቅስቃሴ የለም። ህንጻዎቹን አሻግሬ ተመለከትኩ። ሁሉም ነገር ጸጥ ብሏል። ከዩኒቨርስቲው በር ትይዩ ያለው የወጋገን ባንክ የወልዋሎ ቅርንጫፍ የማስታወቂያ ሰሌዳ፤ ከተሰቀለበት ተገንጥሎ ወርዶ የበረንዳውን መሬት ነክቷል። 

ሌሎች የከተማይቱን ክፍሎች ለመመልከት ከዩኒቨርስቲው ደጃፍ ተንቀሳቀስን። ከአክሱም አቅጣጫ ወደ ከተማይቱ የሚያስገባውን መንገድ ተከትለን ዙሪያ ገባውን መቃኘት ቀጠልን። እስከ ከተማይቱ መሃል የተዘረጋውን መንገድ በብቸኝነት የተቆጣጠሩት ባጃጆች ናቸው። የእነርሱም ቁጥር ቢሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ የሚባል ነው። በዚህኛው የመንገድ ክፍል ዳር ያሉ የንግድ መደብሮች፣ ባንኮች እና ሌሎች ቤቶች ሙሉ ለሙሉ እንደተዘጉ ናቸው። 

ጠንካራውን ጸሀይ ተቋቁመው በእግራቸው የሚጓዙ የከተማይቱን ነዋሪዎች እየተመለከትን ወደ መሃል ከተማ በመመለስ ላይ ሳለን፤ አራት የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶችን ከአንድ ህንጻ ስር አየሁ። እስካሁን በዞርኩባቸው የከተማይቱ ክፍል ያየኋቸው ወታደሮች እና ፖሊሶች ከአምስት አለመብለጣቸው አስገርሞኛል። ይህ ገረሜታዬ አብሮኝ የቆየው ግን ተጨማሪ አራት የኤርትራ ወታደሮችን እስከተመለከትኩበት አፍታ ድረስ ነው። ወታደሮቹን በአንድ ላይ የመመልከት ዕድል ያገኘሁት ባልተጠበቀ አጋጣሚ ነው። 

ሹፌራችን ወደ መቐለ የሚሄዱ ተጨማሪ ተጓዦች ለማግኘት በመፈለግ ወደ ከተማይቱ መናኸሪያ የሚወስደውን መንገድ ደጋግሞ ይዞረዋል። መዞሩ ሲታክተው፤ መናኸሪያው አቅራቢያ ካለ እና ከፍ ብሎ የተሰራ በረንዳ ካለው ካፌ አጠገብ ሄዶ ያቆማል። የመኪናውን መሪ እንደያዘ፤ በመስኮት ጭንቅላቱን አውጥቶ ከወጣት የመኪና ደላላዎች ጋር ይነጋገራል፤ ተጓዥ የመሰሉትን አልፎ ሂያጆችንም ያግባባል። ከተማውን እንደልብ ለመመልከት በሚል ከጋቢና ከተቀመጥሁ ቆይቻለሁ። ከጋቢናው ውስጥ ሆኜ ፊት ለፊታችን ካለው በረንዳ ላይ የተቀመጡትን ሰዎች አስተውላለሁ። 

“ ‘የኤርትራ ወታደሮች ናቸው እንዴ?’ ብዬ ራሴን ጠይቄ ሳልጨርስ፤ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ሁለቱ ሰዎች ሲነሱ ጫማቸው ታየኝ። ሚሊሺያ የመሰለኝም፤ የሲቪል ልብስ የለበሰውም የተጫሙት የኮንጎ ላስቲክ ጫማ ነው። ክላሺንኮቭ መሳሪያቸውን ከጎናቸው አንስተው ከጓዶቻቸው ጋር ሰላም ተባባሉ”

አንደኛው ሰው የለበሰው ሱሪ የቀድሞውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ የመሰለ ነው። ሚሊሺያዎች እንዲህ ይለብሱ እንደነበር ከዚህ ቀደም በነበሩኝ ጉዞዎቼ ተመልክቼ ስለነበር፤ “በዚህ ጊዜ እንዴት ሚሊሺያዎች እንዲህ ደፍረው ሊንቀሳቀሱ ቻሉ?” እያልኩ እገረማለሁ። በዚያ ላይ የደንብ ልብሱን የለበሰው ሰው አጠገቡ ከተቀመጠው እና ሰው ጋር በመዝናናት መንፈስ ነው የሚያወራው። ሁኔታቸው አስገርሞኝ አተኩሬ እያያኋቸሁ እያለ፤ ሁለት ክላሺንኮቭ መሳሪያ የያዙ ሰዎች ወደ ካፌው በረንዳ አቅጣጫ መጡ። ሁለቱም ታጣቂዎች፤ ሚሊሺያ የመሰለኝ ሰው ያደረገውን አይነት ወታደራዊ የደንብ ልብስ አድርገዋል። 

“የኤርትራ ወታደሮች ናቸው እንዴ?” ብዬ ራሴን ጠይቄ ሳልጨርስ፤ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ሁለቱ ሰዎች ሲነሱ ጫማቸው ታየኝ። ሚሊሺያ የመሰለኝም፤ የሲቪል ልብስ የለበሰውም የተጫሙት የኮንጎ ላስቲክ ጫማ ነው። ሁለቱም እስካሁን ዕይታዬ ውስጥ ሳይገባ የቆዩ፤ ክላሺንኮቭ መሳሪያቸውን ከጎናቸው አንስተው ከጓዶቻቸው ጋር ሰላም ተባባሉ። ጓዶቻቸውም ያደረጉት የላስቲክ ጫማ መሆኑን አስተዋልኩ። 

በመሳሪያ አንጋቾቹ ሁኔታ ተመስጬ ሁኔታቸውን ስከታተል፤ ከአዲስ መጤዎቹ ውስጥ ጎልማሳ የሆነው ሰው መኪናችንን ተመለከታትና ተቆጣ። ወዲያው ትዕዛዝ እና ቁጣ በቀላቀለ መልኩ የሆነ ነገር በትግርኛ ተናገረ። ከሁኔታው ከፊታቸው ዞር እንድንል እንደፈለገ ገባኝ። የገመትኩት ልክ ነበር። ከኋላ የተቀመጠው የጋራዡ ሰራተኛ መሳሪያ አንጋቹ “መኪናችንን በፍጥነት ከአካባቢው እንድናነሳ” ትዕዛዝ እንደሰጠ ገለጸልኝ። አከታትሎም “የኤርትራ ወታደሮች ናቸው” ሲል የጠረጠርኩትን አረጋገጠልኝ። 

የጋራዡ ሰራተኛ የተባለውን ለሹፌሩ ቢነግረውም፤ በወሬ የተጠመደው ሹፌር በቅጡ አልሰማውም። ጎልማሳው የኤርትራ ወታደር ጣቱን እያወዛወዘ በቁጣ በድጋሚ ትዕዛዝ ሲሰጥ፤ እኔም የጋራዡ ሰራተኛም ሹፌሩ ላይ ጮኽንበት። እየተነጫነጨ መኪናዋን አቅራቢያው ወዳለው የከተማው መሃል ወሰዳት።

 ሹፌሩ የሆነውን በዝርዝር እስክንነግረው ድረስ ነገሩ አልገባውም፤ ኤርትራውያኑን ወታደሮችም አላያቸውም። የጋራዥ ሰራተኛው፤ ጎልማሳው የኤርትራ ወታደር የተጠቀማቸውን ቃላቶች ለሹፌሩ በትግርኛ ደገመለት። በትግራይ ያሉ ነዋሪዎች፤ ኤርትራውያን ወታደሮቹን ለመለየት የቃላት አጠቃቀም እና ዘያቸውን ነገሬ ብለው እንደሚከታተሉ አስቀድሜ ስለሰማሁ የሹፌሩ እና የጋራዥ ሰራተኛው ምልልስ አልገረመኝም። አምስት ደቂቃ ባማይሞላ ጊዜ ግን ሹፌሩ የራሱን ማረጋገጫ አገኘ።

ካፌ በረንዳ ላይ አስቀድመው ያየናቸው ሁለቱ ወታደሮች፤ መኪናችን ከቆመችበት ባሻገር ያለው የመንገድ አቅጣጫ በመከተል ወደ ከተማ መሃል ሲሄዱ አየን እና አሳየነው። ሹፌር ከቦታው ያስነሳነው ለረዥም ጊዜ አንድ አካባቢ ላይ በመቆማችን ተሰላተችተን መስሎት ነበር። ያየውን ካየ በኋላ ግን አመነ። 

መኪናችን ተጨማሪ ተጓዦችን ለመፈለግ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ መናኸሪያ አቅጣጫ ስታቀና አይኖቼን ወደ ካፌዋ በረንዳ ላኩ። ሁለቱ አዲስ መጤ ወታደሮች በረንዳው ላይ ተቀምጠው ዙሪያ ገባውን በተጠንቀቅ ይቃኛሉ። የቀድሞዎቹም ሆኑ አዲሶቹ ወታደሮች አካባቢውን በመጠበቅ አሊያም በመቃኘት ስራ ላይ የተሰማሩ ሳይሆኑ አይቀርም። መኪናችንን በረንዳው አጠገብ አቁመን የነበርንበት ሰዓትም፤ ወታደሮቹ ፈረቃ የሚቀያየሩበት ሰዓት እንደነበር ከሁኔታው ተነስቼ ገመትኩ። 

የእኔ እና የኤርትራውያን ወታደሮች ጉዳይ በዚህ አላበቃም። ሹፌራችን ሁለት ተጓዦችን ከመናኸሪያ ጭኖ፤ ከመቐለ አብረውን የመጡትን ሁለት ሴቶች ከየቤታቸው ለማምጣት እየተጓዘ ነው። ዋናውን መንገድ ለቅቆ ወደ አዲግራት ማዘጋጃ ቤት ወደሚወስደው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሲታጠፍ ከሌሎች የኤርትራ ወታደሮች ጋር ተገጣጠምኩ። አንድ በቆርቆሮ የታጠረ መስሪያ ቤት የመሰለ ግቢ ደጃፍ ላይ አራት ወታደሮች ተቀምጠዋል። መሳሪያ ባይታጠቁም፤ የደንብ ልብሳቸውና ጫማቸው ግን ቀደም ሲል እንዳየኋቸው ወታደሮች ነው። መኪናችን በዝግታ በአጠገባቸው ስታልፍ ወታደሮቹ በጥርጣሬ አተኩረው ተመለከቷት። 

ያየኋቸው ኤርትራውያን ወታደሮች አንዳቸውም የሀገራቸውን የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ አልለበሱም። ወደ ዛላምበሳ እና ሌሎች የድንበር ከተሞች ብሄድ፤ የራሳቸውን የደንብ ልብስ እንደለበሱ እንደልብ መመልከት እንደምችል አዲግራት ያሉ ሰዎች ነግረውኛል። ይሄንን እንዴት እንዳወቁ ስጠይቅ፤ ወደ አካባቢው ደርሰው ከተመለሱ የአዲግራት ነዋሪዎች መስማታቸውን አብራርተውልኛል። 

መናኸሪያ አካባቢ በቆየንባቸው ደቂቃዎች፤ በእግርጥም ወደ ዛላምበሳ የሚሄድ መኪና እንዳለ አጠያይቄ ነበር። ከወጣት መኪና ደላላዎች አንዱ እንደልብ ባይሆንም አልፎ አልፎ ሚኒባሶች እንደሚሄዱ ነገሩን። ሚኒባሶቹ የሚጠይቁትን ከፍ ያለ ዋጋ መክፈል የምችል ከሆነ ወደ ዛላምበሳ ብቻ ሳይሆን አድዋ እና ሽረም የሚሄዱ ሚኒባሶች ማግኘት እንደሚቻል ጨመረልኝ። ዋጋውን ጠየቅሁ። ለመሄጃ ብቻ አንድ ሺህ ብር መሆኑ ተነገረኝ። 

የእውነትም ወደ አካባቢው መሄድ የምፈልግ የመሰላቸው ሹፌሩ እና የጋራዥ ሰራተኛው ነገርየውን እንዳልሞክረው ተከላከሉኝ። በዛላምበሳ መንገድ እና አካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስጊ መሆኑን አንስተው፤ መኪና ቢኖርም አደጋው ከፍ ያለ መሆኑን ገለጹልኝ። ወደ አድዋ እና ሽረ የሚሄዱ መኪናዎች፤ አዲግራት መውጪያ ላይ ካለ ኬላ በኋላ ማለፍ እንደማይችሉና የሚፈቀድላቸውም ካሉ የመንግስት ተሽከርካሪዎች ብቻ እንደሆኑ ጠቆሙኝ። ወጣቱ ደላላ ግን የሁለቱን ሀሳብ ችላ ብሎ፤ ወደ ቦታው የሚጓዙ መኪናዎች እንዳሉ ሊያሳምነኝ ጣረ። የሁለቱንም ወገን ማብራሪያዎች ከሰማሁ በኋላ ወደ መቐለ እንደምመለስ አሳውቄ የተጨማሪ ጉዞ ውይይቱን በዚሁ ቋጨሁት።

ወጣቱ ደላላ ከእኔ ጉዞ “ሽቀላ” ባለማግኘቱ የተከፋ ይመስላል። እንደቀድሞ ጊዜ ስራ በሽ ባለመሆኑ መቸገሩ በግልጽ ያስታውቃል። ወጣቱ ኑሮው የተመሰረተው ቀነ ተቀን በሚያገኘው ገቢ ላይ ነው። ከጠዋት ጀምሮ ምንም ስራ አለመስራቱንና እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ እህል በአፉ አለመዞሩን ለሹፌሩ ሲነግረው ሰማሁ። ከውቅሮ ጀምሮ ስንሻምደው ከነበረው አንድ ኪሎ የገብስ ቆሎ ላይ የተረፈንን ሰጠሁት። የቆሎ አዘጋገኑ መራቡን ያስታውቃል። ጥቂት የብር ኖቶች “ለምሳ ትሁንህ” ብዬ ጨመርኩለት። ፊቱ በደስታ በራ። 

የቀዘቀዘችውን እና በሮቿን የዘጋጋችውን አዲግራት ለተመለከተ፤ እንደ ወጣቱ ደላላ አይነት የተቸገሩ ሰዎች በየቦታው ሊኖሩ እንደሚችሉ ማገናዘብ አይሳነውም። በአዲግራት በእግር ከተዘዋወርኩባቸው ጥቂት ቦታዎች በአንዱ፤ የከተማይቱ ነዋሪዎች በእህል አቅርቦት ብቻ ሳይሆን፤ በመድኃኒት እጥረት ሊቸገሩ እንደሚችሉ በማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል ነገር አይቻለሁ። 

ነገሩ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፤ የትግራይ ክልል ምስራቅ ዞን ቅርንጫፍ ጋር የተያያዘ ነው። እኔ በተመለከትኩበት ወቅት በቅርንጫፉ ስር ያለው የአዲግራት መድኃኒት ቤት ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል። በቀጫጭን የብረት ርብራቦች ከተሸፈኑት መስኮቶች መታወታቸው ተሰባብሯል። ከበሩ አጠገብ ያለው አንደኛው መስኮት እንደውም የብረት ርብራቦቹ ላይ የመገንጠል ሙከራ እንደተደረገ በግልጽ ይታያል። 

ለዝርፊያ በሚመስል መልኩ የተሰበሩ መስኮቶችን በአዲግራት ባሉ የባንኮች ቅርንጫፎች ላይም ተመልክቻለሁ። የወጋገን፣ አንበሳ እና ቡና ባንኮች ቅርንጫፎች ለዚህ በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በአዲግራት በነበርኩበት ሰዓት ሁሉም የባንክ ቅርንጫፎች ዝግ ነበሩ። ከህዝብ አገልግሎት መስጪያዎች  ቢያንስ የቅጽር ግቢው ተከፍቶ የተመለከትሁት የአዲግራት ማዘጋጃ ቤት ነው። በማዘጋጁ ቤቱ አገልግሎት ተጀምሮ እንደው ግን ወደ ውስጥ ዘልቄ አላረጋገጥኩም።           

አዲግራትን የተሰናበትናት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ ነበር። መቐለ ከሰዓት እላፊ በፊት በቶሎ ለመድረስ በሚል ነበር በጊዜ ከከተማይቱ ለመውጣት ውሳኔ ላይ የተደረሰው። አብረውኝ ከመቐለ የመጡ ሁለቱን ሴት ተጓዦች አሳፍረን ወደ የመልስ ጉዞ ጀመርን። በመልስ ጉዟችን እንደገና በወፍ በረረ የተመለከትኳቸውን  ከተሞች ከአዲግራት ሁኔታ ጋር ለማነጻጸር ሞከርኩ። 

እንደ እነ እኔ ዕይታ አዲግራት፤ በጉዳት እና ውድመት ረገድ ከዕዳጋ ሐሙስ እና ውቅሮ ከተሞች በተሻለ ሁኔታ ላይ ያለች ነች። ይህን ጉዳይ ያነሳሁባቸው አብረውኝ የሚጓዙ የከተማይቱ ተወላጆች፤ “በየቦታው እየገባህ ዘረፋውን እና ጉዳቱን ስላላየኸው ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል። የተወሰነ እውነት አላቸው። ብዙ ዘረፋ እና ውድመት እንደደረሰበት የሰማሁትን የአዲግራት መድኃኒት ፋብሪካን እንኳ፤ በነበረኝ የጠበበ ጊዜ እና የጉዞዬ ሁኔታ ምክንያት በአይኔ ተመልክቼ ማረጋገጥ አልቻልኩም። 

ወደ አዲግራት ስንጓዝም ሆነ ስንመለስ በመንገድ ያስተዋልኩት ሌላው ጉዳይ፤ ከገጠር የመጡ የሚመስሉ ነዋሪዎችን ነገር ነው። በማዳበሪያ ከረጢት የተሞላ ነገር ተሸክመው እና በአህያ ጭነው የሚጓዙ በርከት ያሉ ሰዎች ተመልክቼያለሁ። የተወሰኑቱ ወፍጮ ቤት እየተጓዙ ሳይሆን እንደማይቀር ጠርጥሬያለሁ። ለጥርጣሬዬ መነሻ የሆነኝ መንገድ ዳር ባሉ እና በሰዎች በተጨናነቁ ወፍጮ ቤቶች ተመሳሳይ ሰዎችን በመመልከቴ ነው። መብራት ጠፍቶ በመክረሙ ሳይሆን አይቀርም ወፍጮ ቤቶቹ ስራ የበዛባቸው ይመስላል። በጥቂት ቦታዎች አርሶ አደሮች የደረሰ እህላቸውን ሲያበራዩ አይቻለሁ። አልፎ አልፎም ቢሆን በየሜዳው የተሰማሩ ከብቶች እና እነርሱን የሚያግዱ ህጻናትም ከዕይታዬ ገብተዋል።

መቐለ ከመግባታቸን በፊት አጉላዕ ከተሰኘችው ከተማ መውጪያ ላይ ካለ የነዳጅ ማደያ ላይ መኪናችን ቆማ ነበር። ወደ አዲግራት ስንሄድም በዚሁ ማደያ ቆመን ነዳጅ መቅዳታችንን አይቼ ስለነበር፤ ሹፌራችንን ለምን እንደ እርሱ እንዳደረገ ጥያቄ ጠየቅሁት። ምንም እንኳ የነዳጅ ዋጋው ቢወደድም፤ በአካባቢው እምብዛም ተጠቃሚ ስለሌለ፣ ከመቐለ በተሻለ ነዳጅ የሚገኝበት ቦታ በመሆኑ ነው ይህንን ማደያ መምረጡን ነገረኝ። የሹፌራችን ምርጫ፤ ጣጣ አስከትሎብን እንደነበር ግን ያን ጊዜ ማናችንም አላወቅንም። በስተኋላ ላይ ከአካባቢው የመጡ ሰዎች የተሰማው መረጃ ግን የሚያስደንግጥ ነበር። ለካንስ እኛ ቦታውን ከለቀቅን ከግማሽ ሰዓት በኋላ በአጉላዕ አካባቢ ቅልጥ ያለ ተኩስ ተከፍቶ ኖሯል። ለ30 ደቂቃ ብንዘገይ ኖሮ…. 

*  *  *

ታህሳስ 23፤ 2013 ዓ.ም.። ለአምስት ቀናት ከግማሽ የቆየሁባትን መቐለን ልሰናበታት ነው። ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ የአውሮፕላን ቦታ ማግኘት ቢያንስ አንድ ሳምንት የሚያስጠብቅ በመሆኑ፤ ሌሎች አማራጮችን ሳፈላልግ ነበር የቆየሁት። ወደ መዲናይቱ የሚጓዝ አውቶብስ እንዳለ ስሰማ፤ የተጠየቅሁትን ለመክፈል አላቅማማሁም። ከ500 ብር በታች ይከፈልበት የነበረው የአውቶብስ ጉዞ፤ ሁለት ሺህ ብር የሚጠይቅበት ሆኗል። እርሱም ቢሆን ቀድሞ በደላላ የሚገዙት ካልጨረሱት ነው። በዚያም አለ በዚህ “ግዮን ባስ” ከተሰኘ የህዝብ ማመለሻ አገልግሎት ሰጪ፤ ለዛሬ ጉዞ የሚሆን ትኬቴን ቆርጬ ተዘጋጅቻለሁ። 

የአውቶብሱ የትኬት ቢሮ ከሚገኘበት ቦታ ጠዋት አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል እንድንገኝ በተገረን መሰረት፤ በተባለው ጊዜ ተገኝቻለሁ። አንድ ሰዓት ይንቀሳቀሳል የተባለው አውቶብስ ሌሎች መንገደኞችን እስኪያስተናግድ ራቅ ብዬ ሁኔታውን አስተውላለሁ። ከመንገደኞቹ በተሻለ ማልደው በቦታው የተገኙት ግን በአቅራቢያው በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወረፋ ለመጠበቅ የተሰለፉ የከተማይቱ ነዋሪዎች ናቸው። እየተንጠባጠቡ በመጡ ተጓዞች ምክንያት 50 ደቂቃ ዘግይተን መቐለን ለቀን ወጣን። ጉዟችን በአላማጣ አቅጣጫ ነው። 

ከመቐለ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለው አሸጎዳ ሳንደርስ፤ ሶስት ጊዜ ለፍተሻ እንድንወርድ ስንደረግ ነው፤ ጉዟችን የኤሊ ሊሆን እንደሚችል የገመትኩት። የፈራሁትም አልቀረ፤ በየ30 ደቂቃ ለፍተሻ መቆም ሆነ ስራችን። አንዳንዴ ከአውቶብስ ሳንወርድ በዚያው በተቀመጠንበት መታወቂያችን እያወለበለብን እንድናሳይ እንደረጋለን። ሌላ ጊዜ ሁለት ፈታሾች ወደ አውቶብስ ውስጥ ይገቡና ግማሽ ግማሽ ተካፍለው የሁሉንም መንገደኞች መታወቂያ በጥንቃቄ እየተመለከቱ ማንነታችንን ያረጋግጣሉ። እንደ ከተሞች መግቢያ እና መውጪያ ባሉ ቦታዎች ደግሞ ከአውቶብስ ወርደን መታወቂያችንም፤ አካላታችንም፤ አውቶብሳችንም ይፈተሻል። 

በእንዲህ አይነት ሁኔታ ተጉዘን አላማጣ የገባነው እኩለ ቀን ገደማ ነው። ለምሳ ካሰብነው ጊዜ በላይ ስንወስድ፤ ረዳቱን ዛሬውኑ አዲስ አበባ እንገባ እንደሁ ጠየቅኩት። ፍተሻው እንዲሁ የሚቀጥል ከሆነ መተሐራ ላይ ልናድር እንደምንችል ነገረኝ። ከአላማጣ በኋላ በደሴ መስመር እንደምንጓዝ ገምቼ ስለነበር ለምን በአፋር በኩል እንደምንዞር በድጋሚ ጥያቄ አቀረብሁ። “የአፋሩ መንገድ ብዙም የትራፊክ ጭንቅንቅ ስለሌለው ነው” የሚል ምላሽ ተሰጠኝ። ረዳቱ እንደገመተውም በሃራ መገንጠያ አድርገን ወደ አፋር ክልል እስክንገባ ድረስ ተደጋጋሚ ፍተሻዎች ቀጥለው ነበር። 

በአፋር ያለው ፍተሻ እንደ ትግራይ እና አማራ ክልል አይነቶቹ ጥብቅ ባይሆንም፤ ለመተሐራ የሚሆን ጊዜ አላተረፈልንም። ገዋኔ ከተማ ስንደርስ አስራ ሁለት ሰዓት በማለፉ ማደሪያችን እዚያው እንደሚሆን ሹፌሩ ውሳኔ አሳለፈ። በከባድ መኪናዎች እና የነዳጅ መጫኚያ ቦቴ አሽከርካሪዎች ዘንድ የምትዘወተረው አነስተኛይቱ ገዋኔ ብዙም የሆቴል አማራጭ የላትም። የተገኘው ቦታ ፈላልገን ለሊቱን አሳለፍን። 

አርብ ጠዋት ከመቐለ ለጉዞ የተነሳን ቅዳሜንም በተመሳሳይ መልኩ መንገዱን ተያይዘነዋል። መተሐራ ላይ አፋችንን በቁርስ ካሟሸን በኋላ ጉዟችንን ያለ እክል ቀጠልን። እኩለ ቀን ሲሆን አዳማ ከተማ መግቢያ ደረስን። የአውቶብሱ ረዳት፤ አዳማ ወራጆች ካሉ እንዲዘጋጁ ሲናገር፤ ከፊት ለፊታችን ካለው ወንበር ከተቀመጡት ጀምሮ ብዙ መንገደኞች ለመውረድ መሰናዳት ጀመሩ። አንዴ ወደ ፈጣን የክፍያ መንገድ ከተገባ እስከ ቱሉ ዲምቱ ማቆም ስለማይቻል፤ ትክክለኛው መውረጃ ቦታ አዳማ መሆኑን ወራጆች ይነጋገራሉ።  

ስለ ቱሉ ዲምቱ መቐለ እያለሁ ሰምቻለሁ። ወሬው “ከትግራይ የሚሄዱ ወጣቶች፤ አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ ቱሉ ዲምቱ ላይ ተይዘው ይታሰራሉ” የሚል ነበር። “አፍንጫችን ስር አዲስ አበባ፤ ይህ ድርጊት ተፈጽሞ ከሆነ መስማት ነበረብኝ” በሚል ችላ ብዬው የቆየሁት ወሬ፤ በአውቶብሱ መንገደኞች ዘንድ ተደጋግሞ ሲነሳ “ምናልባት እውነትነት ሊኖረው ይችላል” አስብሎኛል። ሆኖም ይሄን ያህል ሰው በስሚ ስሚ ባገኘው ወሬ ተሸብሮ አውቶብሱን ጥሎ ይወርዳል ብዬ አልገመትኩም። ወራጆቹ “ከመታሰር፤ አዳማ ወርዶ በሌላ መኪና ወደ አዲስ አበባ እያሰበሩ መሄድ ይሻላል” የሚል አቋም ይዘዋል። 

ከወረዱት ውስጥ አብዛኞቹ ኤርትራውያን ስደተኞች መሆናቸውን ከኋላ የተቀመጠ የመቐለ ሰው ሲነግረኝ፤ በዚያ ሁሉ ፍተሻ እንዴት አልፈው እንደመጡ ገረመኝ። በፍተሻ ወቅት የኤርትራ ፖስፖርት ይዛ የተመለከትኳት ተለቅ ያለች ሴት ከእነ ልጇ አሁንም አውቶብስ ውስጥ እንዳለች ስመለከት ደግሞ ግር አለኝ። የወረዱት ወርደው አውቶብሳችን ሲንቀሳቀስ በውስጡ የቀረነው ሃያ ገደማ መንገደኞች ነን። “ቱሉ ዲምቱ የሚያጋጥመን ያው ፍተሻ ነው። እንደተለመደው መታወቂያችንን አሳይተን ማለፋችን አይቀር” ያልን ሰዎች ነበር በአውቶብሱ የቀረነው። 

እንደገመትነውም የፍጥነት የክፍያ መንገድ ማብቂያ ከሆነው ቱሉ ዲምቱ ስንደርስ ለፍተሻ እንድወርድ ተደረገ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የደንብ ልብስ የለበሰ ፖሊስ፤ ሴቶች እና ወንዶቹን በተለያየ መስመር ለፍተሻ አሰለፈን። ከዚያም የሁላችንንም መታወቂያ እና ፓስፖርት ከተቀበለ በኋላ ባለንበት እንድቆም ነገረን። ለደቂቃዎች በከራራው ጸሀይ ላይ ቆመን ጠበቅን። ፖሊሱ መታወቂያዎቹን በእጁ ይዞ ስልክ ይደውላል። ጥቂት ቆይቶ ደግሞ በአካባቢው ካሉ ሌሎች ፖሊሶች ጋር መታወቂያውን እያሳየ ይነጋገራል። 

ጸሐዩ የበረታብን መንገደኞች ጥላ ፍለጋ መንገዱ ዳር ወዳለው ጉብታ ወጥተን ተቀመጥን። በዚያ እንደተቀመጥን ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ በርካታ የህዝብ ማመላሻ ሚኒባሶች እና አውቶብሶች እንደነገሩ ተፈትሸው ሲያልፉ ስንታዘብ ቆየን። የእኛን መታወቂያ የያዘው ፖሊስ እና ሌሎች፤ ከአውቶብሳችን ፊት ቆሞ በሮቹ በተከፋፈተ ዘመናዊ የቤት መኪና እና መንገደኞቹ ላይ አተኩረዋል። ስለ ጉዟችን ህጋዊነት ፖሊሶቹን ለማስረዳት ሞክረው የሰለቻቸው ሹፌራችን እና ረዳቱ፤ አሁንም አሁንም ስልክ ይደውላሉ። ጠብ ያለ ነገር ሳይኖር ግማሽ ሰዓት አለፈ። 

በአውቶብሱ ኋለኛ ክፍል ተቀምጠን የነበረን መንገደኞች፤ “አዳማ የወረዱት ተጓዦች ያሉት ነገር እውነት ይሆን እንዴ?” በሚል መንፈስ እንነጋገራለን። አንዳንድ መንገደኞች ላይ ጭንቀት ይነበባል። “የበላይ አለቆች ሲፈቅዱ ጉዟችንን እንቀጥላለን” የሚለው እምነቴ አሁንም ባይሟጠጥም፤ ያንን ሁሉ መንገድ ተጉዘን መጉላላታችንን ግን አልወደድኩትም። ከዚያ በኋላ የተከሰተው ግን እኔንም ስጋት ውስጥ የጨመረኝ ነበር። 

ከጸሐይ ከተጠለልንበት ተጠርተን፤ ወደ አውቶብሱ እንድንሳፈር ከተደረገ በኋላ በቀጥታ ወደ ቱሉ ዲምቱ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደን። ፖሊስ ጣቢያው አጠገብ፤ ከመቐለ የተነሳ ሌላ አውቶብስ ስመለከት ልቤ ዝቅ አለ። በኖህ ትራንስፖርት ባለቤትነት ስር ያለው ይህ አውቶብስ ከእኛ በኋላ ዘግይቶ ከመቐለ እንደተነሳው ሁሉ ማደሪያችን በነበረው ገዋኔም የደረሰው አምሽቶ ነው። ወደ አዲስ አበባ በነበረው ጉዞ ግን መዘግየቱን ለማካካስ ያሰበ በሚመስል መልኩ፤ ቀድሞን ነበር ከገዋኔ ጥሎን የሄደው። ይህን አውቶብስ ነው እንግዲህ ፖሊስ ጣቢያው ላይ ቆሞ ያገኘንው። 

ወደ ቱሉ ዲምቱ ፖሊስ ጣቢያ ቅጽር ግቢ በሰልፍ ስንገባ፤ በስተቀኝ ባለው ክፍት ቦታ ላይ በርከት ያሉ ሰዎች ተሰብስበው አየሁ። በኖህ አውቶብስ ከመቐለ የመጡ መንገደኞች መሆናቸውን አልተጠራጠርኩም። ከመካከላቸው አንዳንዶቹን ገዋኔ ላይ ልብ ብዬ አይቼያቸዋለሁ። ፖሊስ ጣቢያው እንደ በረንዳ በሚጠቀምበት ቦታ ላይ ወረቀቶች የያዘ ፖሊስ እና ሌሎቹ ባልደረቦቹ ይታያሉ። ወረቀቶቹን የያዘው ፖሊስ አለቃ ነገር ይመስላል። ከዚያ በኋላ የቀረቡልንን አብዛኞቹን ጥያቄዎች የሚጠይቀው እርሱ ነበር።  

ይሄው ፖሊስ ከመካከላችን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዳሉ ጠየቀ። ሰባት ገደማ የሚሆኑት በአዎንታ ምላሽ ሰጡ።  አብዛኞቹየአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ (AASTU) ተማሪዎች ናቸው። ተማሪዎቹ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ መክረማቸውን፤ ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ የተላለፈውን ጥሪ ሰምተው መምጣታቸውን እና የዚህ ዓመት ተመራቂዎች መሆናቸውን ተናገሩ። አለቃ ከሚመስለው ፖሊስ ኋላ የቆመው ወጣት ፖሊስ ለተማሪዎቹ አንድ ሁለት ጥያቄ እንደ ቀልድ ወርወር አደረገ። ጥያቄዎቹ በትክክል ተማሪዎች መሆናቸውን ለማረጋገጥ የተደረጉ ይመስላሉ። 

ወጣቱ ፖሊስ ከአጠያየቁ፤ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አጠገብ የሚገኘውን የተማሪዎቹን ዩኒቨርስቲ የሚያውቅ ይመስላል። ዩኒቨርስቲው ስንት መግቢያ እንዳለው፣ መግቢያዎቹ በየት አቅጣጫ እንደሚገኙ፣ ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ “የሚፎርፉት” በየትኛው በር በኩል እንደሆነ፣ ተማሪዎቹ ፎርፈው ያውቁ እንደሆነ ተማሪዎቹን ቀልድ እያስመሰለ ይጠይቃቸዋል። በዚህ መሃል አለቃ መሳዩ ፖሊስ የተዘጋጀ ፎርም አምጥቶ የተማሪዎቹን ስም እና ዝርዝር መረጃ መመዝገብ ጀምሯል። 

ተማሪዎቹ የቀረበላቸውን ጥያቄዎች ቢመልሱም፤ ወጣቱ ፖሊስ አለቀቃቸውም። ድንገት ያልተጠበቀ ጥያቄ ጠየቃቸው። “ባለፈው ዓመት እናንተ ግቢ ራሱን ያጠፋው ልጅ የስንተኛ ዓመት ተማሪ ነው? የየት አካባቢ ልጅ ነው?” ሲል ጠየቀ ወጣቱ ፖሊስ፤ አቃቤ ህግ ተከሳሽን በመስቀለኛ ጥያቄ በሚያፋጥጥበት ድምጸት። ብዙውን ጊዜ ምላሽ የሚሰጠው ተማሪ፤ በጥያቄው ግር ቢሰኝም ሁለቱንም ጥያቄዎች መለሰ። አሁን ወጣቱ ፖሊስ በምላሹ የረካ መሰለ። “ትክክል ነው” አለ ወደ ባልደረቦቹ ዞሮ። ያንን ምላሽ እስኪሰማ ድረስ ተማሪዎቹን ተጠራጥሯቸው እንደነበርም ተናገረ። 

አለቃ መሳዩ ፖሊስ፤ የተማሪዎቹን ምዝገባ ሲጨረስ ከመንገደኞቹ መካከል የትግራይ መታወቂያ የያዙ ነዋሪዎች በአንድ ወገን እንዲሆን አደረገ። ከመካከላችን የአዲስ አበባ ነዋሪ እንዳለ ሲጠይቅ የተወሰነው እጃችንን አወጣን። እኛን በሌላ ወገን እንድንሰበሰብ አመለከተን። አለቃ መሳዩ ፖሊስ የትግራይ ነዋሪዎችን ዝርዝር መረጃ መመዝገብ ሲቀጥል፤ ወጣቱ ፖሊስ ተመሳሳዩን ለማድረግ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አሰለፈ። ሁሉን ነገር ለማየት ከሰልፉ በስተመጨረሻ ቆምኩ። ተራዬ  ሲደርስ ስሜን፣ የመኖሪያ አድራሻዬን፣ የጉዞዬን ምክንያት እና ስልክ ቁጥሬን አስመዘገብኩ። 

የሁላችንም ምዝገባ ሲጠናቀቅ ከእኛ ቀድመው ከመጡት ከኖህ ባስ መንገደኞች ጋር እንድንቀላቀል ተደረገ። አርባ ገደማ የምንሆን የመቐለ ተጓዦች በጠባቧ የፖሊስ ጣቢያ ግቢ ውስጥ ተከማችተን ደቂቃዎች መቁጠር ጀመርን። በግቢው ውስጥ የነበረን ቆይታ አንድ ሰዓት ሲሻገር፤ “አጣርተው ይለቁናል” የሚለው ተስፋችን እየተመናመነ መጣ። በዚያ ላይ ፖሊሶቹ “ጠብቁ” ከማለት ውጪ የሚሰጡት ተጨማሪ መረጃ የለም። ለድብርታችን ትንሽ ማስታገሻ የሆነን ከፖሊስ ጣቢያው ውጪ ቡና ከምትሸጥ ሴት፤ የጀበና ቡና ያገኘን ጊዜ ነው። በእርግጥ የአውቶብሳችን ረዳትም  የታሸገ ውሃ አምጥቶ አከፋፍሎናል።

ፖሊስ ጣቢያ ከገባን ሁለተኛ ሰዓት ሲቆጠር ነገርየው እንደመረረ ተረዳን። በአንድ አውቶብስ ውስጥ የነበረውን ተጓዦች እንለዋወጠው የነበረው የቢሆናል ግምት፤ “ምሽቱን በእስር ማሳለፍ” የሚለውን ጨመርንበት። ሰዓቱ ወደ አስር ሲጠጋ፤ በሁለቱም አውቶብሶች የነበሩ ተማሪዎች ወደ ፖሊሶቹ ዘንድ ተጠሩ። ለግማሽ ሰዓት ገደማ ድምጻቸው ከጠፋ በኋላ፤ ከተማሪዎቹ መካከል የተወሰኑት የራሳቸውንና የሌሎች መታወቂያች ከግቢ ውጪ ፎቶ ኮፒ አድርገው እንዲያመጡ ተላኩ። የታዘዙትን ፈጽመው ተመለሱ። ከሃያ ምናምን ደቂቃዎች በኋላ፤ ተማሪዎቹ አንድ በአንድ ከግቢ ሲወጡ እየተቁለጨለጨን በአይናችን ሸኘናቸው። 

ከአስር ሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ እስር ቤትን የሚያስታውሱ ነገሮችን የተመለከትኩበት ነበር። መንገደኞች በፖሊሶች አጀብ ሽንት ቤት ሲመላለሱ እና ከቤተሰብ የመጣላቸውን ምግብ ተቀብለው ከበው ሲመገቡ ማየቴ ነበር የእስር ቤት ጊዜ ትውስታዬን የቀሰቀሰው። መንገደኞች በፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ መደረጋቸውን በስልክ የሰማ ቤተሰብ፤ ምግብ እና ውሃ ይዞ ከመምጣት ባሻገር ከፖሊሶች ጋር እሰጥ እገባ ሲገባ አስተውያለሁ። ሰዓቱ ወደ አስራ አንድ ሰዓት ሲጠጋ፤ ሁለት ከፍ ያለ ሹመት ያላቸው ፖሊሶች ወደ ግቢው መሃል መጡ። 

ሁለቱ ፖሊሶች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሆኑ ሰዎች እንዲሰለፉ ጠይቁ። በእጃቸው ይዘውት የነበረውን የስም ዝርዝር ከመታወቂያ እና ፖስፖርት ጋራ እያመሳከሩ ወደ በረንዳው እንድሄድ አደረጉ። አካሄዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ሁኔታ የተከተለ ስለነበር፤ ከፖሊስ ጣቢያው የመለቀቃችንን ተስፋ አለመለመው። የእኛን ተለይቶ መቆም ተከትሎ፤ ቀሪዎቹ መንገደኞች ዕጣ ፈንታቸውን ወደ ሁለቱ ፖሊሶች ተጠግተው ጥያቄ ያከታተሉ ጀምር። አንደኛው ፖሊስ “ጠብቁ” የሚል ምላሽ ሰጥቶ ሄደ። መንገደኞቹ ቀሪውን ፖሊስ ከብበው ማብራሪያ መጠየቃቸውን ቀጠሉ። ፖሊሱ በጫጫታ መሃል “እኔም እንደናንተው ነኝ። የማውቀው ነገር የለም” ሲላቸው ሰማሁ። 

ከደቂቃዎች በኋላ የአዲስ አበባ መንገደኞች ስማችን እና መታወቂያችን በድጋሚ ታይቶ ከተረጋገጠ በኋላ ከግቢው እንድንወጣ ተደረገ። ወደ ኋላ የቀሩ፣ አብረውኝ የተጓዙ መንገደኞችን እጄን እያወዛወዝኩ ስሰናበት በሀዘን ስሜት ውስጥ ተዘፍቄ ነበር። ላደርግላቸው የምችለው ነገር አለመኖሩም አስከፍቶኛል። ከፖሊስ ጣቢያ ወጥቼ፤ አውቶብሱ ውስጥ የነበረኝን ሻንጣ ካወረድኩ በኋላ የረዳቱን ስልክ ተቀበልኩ። የቀሪዎቹን መንገደኞች ሁኔታ ለመከታተል በሚል ነበር ስልኩን መቀበሌ። 

አውቶብሱ አጠገብ ቆሞ የነበረ ላዳ ታክሲ ውስጥ ስገባ አስራ አንድ ሰዓት አልፏል። በሁኔታው ማዘኔን ያየው የታክሲ ሹፌር፤ ሊያጫውተኝ ሞከረ። ባለፉት ሁለት ቀናት ከመቐለ የተነሱ አውቶብሶች ከነመንገደኞቻቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ወደዚህ ፖሊስ ጣቢያ እንዲመጡ መደረጋቸውን ነገረኝ። የተወሰኑት ሲለቀቁ፤ የተወሰኑት ወደ ሌላ ሰፋ ወዳለ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን ጨመረልኝ። በዚህ አይነት የቀሩት መንገደኞች “በፖሊስ ጣቢያ ማደራቸው አይቀርም” በሚል ይበልጥ ተከዝኩ። 

በእኛ አውቶብስ ውስጥ ከነበሩ መንገደኞች አንድ ሰው ሲቀር ሊሎቹ የዚያኑ ቀን ምሽት አንድ ሰዓት ላይ መለቀቃቸውን የአውቶብሱ ረዳት በስተኋላ በስልክ ነገረኝ። የኖህ ባስ መንገደኞች ግን እንደ እኛዎቹ ዕድለኞች እንዳልነበሩም አከለልኝ። ይህን ስሰማ አዳማ ላይ የወረዱት መንገደኞች ትዝ አሉኝ። ማንኛችን ነን ትክክል? እነርሱ ወይስ እኛ? ህግን ያመንነው – እኛ ወይስ ከሌሎች መከራ የተማሩት – እነርሱ?። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

የዚህን ልዩ ዘገባ ቀደምት ክፍሎች ለማንበብ ተከታዩቹን ሊንኮች ይጫኑ፦
ክፍል አንድ – https://ethiopiainsider.com/2021/2374/
ክፍል ሁለት –  https://ethiopiainsider.com/2021/2398/ 

ክፍል ሶስት –  https://ethiopiainsider.com/2021/2461/ 

ትግራይ እንዴት ሰነበተች? (ክፍል 3)

January 21, 2021 13093

– የውቅሮ እና ዕዳጋ ሐሙስ የወፍ በረር ቅኝት

በተስፋለም ወልደየስ

ድንገት ከእንቅልፌ ባነንኩ። ተከታታይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ የሰማሁ መስሎኛል። “በህልሜ ነው በእውኔ?” የሚል ጥያቄ ለራሴ አቅርቤ ሳልጨርስ ተከታታዩ ተኩስ ተደገመ። ከአልጋዬ ተፈናጥሬ ወረድኩና ወደ ሆቴሌ በረንዳ በረርኩ። በጨለማ ውስጥ የሚፈነዳ ነገር ይታይ እንደሁ በሚል ዙሪያ ገባውን ቃኘሁ። ምንም ነገር የለም። ሰዓቱን ተመለከትኩ – አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ሆኗል። ደቂቃዎች እንኳ ሳይቆይ ተኩሱ ቆመ። ወደ አልጋዬ ተመለስኩ።

ከግማሽ ሰዓት በኋላ ለጉዞ መዘገጃጀት ጀመርኩ። ከመቐለ 47 ኪሎ ሜትር ገደማ የምትርቀውን ውቅሮ ከተማን ለመመልከት አቅጄያለሁ። ዕለቱ ማክሰኞ፤ ቀኑ ደግሞ ታህሳስ 20፤ 2013 ዓ.ም. ነው። በዚያው ልደር፤ አሊያም ተመልሼ ልምጣ የሚወስነው በአካባቢው ያለው ሁኔታ ነው። በውቅሮ የስልክ አገልግሎት ስለሌለ ስለ ከተማይቱ መሰረታዊ መረጃዎችን እንኳ ለመቃረም ዕድል አላገኘሁም። 

ስለ ከተማይቱ በተባራሪ የሚሰሙ ወሬዎች እርስ በእርስ የሚጣረሱ ናቸው። አንዳንዶች ከተማይቱ በከፍተኛ ሁኔታ ውድመት ደርሶባታል ይላሉ። ሌሎች ከፍተኛ ዘረፋ እንደተፈጸመባት ይናገራሉ። ጥቂቶች አሁንም በአካባቢው ሰላም እንደሌለ እና በአቅራቢያዋ ባሉ ቦታዎች ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ። በዚያም አለ በዚህ፤ ርቃ ከምትገኘው አዲግራት ይልቅ፤ “ለክፉም ለደጉም መቐለ አቅራቢያ የምትገኘው ውቅሮ ትሻለኛለች” በሚል ነበር ወደዚያ ለመሄድ የወሰንኩት። ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ እንደ መሄድ በሉት።  

ከመቐለ ወደ ውቅሮ በህዝብ ትራንስፖርት ለመጓዝ ቀደም ሲል ይከፈል የነበረው ከ20 እስከ 30 ብር ነበር። ከውጊያው በኋላ ግን ዋጋው በአስር እጥፍ ጨምሮ እስከ 200 እና 250 ብር ደርሷል። የመጀመሪያዎቹ ቀናት ሰሞን 500 ብር ሁሉ ከፍለው የሚጓዙ ነበሩ። የአዲግራትም የትራንስፖርት ዋጋ እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል። በደህናው ጊዜ 50 ብር ገደማ ይከፈልበት የነበረው ከመቐለ- አዲግራት ያለው መንገድ፤ “ውጊያው አልቋል” ተብሎ መንገዱ ለተጓዦች ክፍት ሲደረግ እስከ አንድ ሺህ ብር አሻቅቦ ነበር። ከሳምንት በኋላ ዋጋው ወደ 700 ብር ወርዷል። እኔ በተጓዝኩበት ቀን የነበረው የአዲግራት የህዝብ ትራንስፖርት ዋጋ 500 ብር ገደማ ነበር።    

መናኸሪያ ስደርስ ወደ ውቅሮ የሚጓዙ ሚኒባሶች እዚያ እንደሌሉ፤ የሚገኙት ሌላ ቦታ እንደሆነ ሰማሁ። የሚኒባሶቹ መገኛ የመሰለኝ እዚያው መናኸሪያ አካባቢ ስለነበር ከከተማው እያራቅን ስንሄድ ግር አለኝ። የጫነችኝ ባጃጅ በከተማ መውጪያ አካባቢ ያለውን የመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ ስታልፍ፤ ወዴት እየሄድን እንድሆነ ጠየቅኩ። እየደረስን መሆናችንን ሹፌሩ ነገረኝ። ብዙም ሳንጓዝ በተለምዶ “ኮብራ” ተብሎ የሚጠራው ቶዮታ መኪና አጠገብ ቆምን።

ሁለት ደላላ መሳይ ወጣቶች የት መሄድ እንደምንፈልግ እና ስንት እንደሆንን በመሳሰሉ ጥያቄዎች ያዋክቡን ያዙ። የባጃጁ ሹፌር ለ“ኮብራው” አሽከርካሪ በትግርኛ ጥያቄ ሲያቀርብ፤ እነርሱም ተደርበው ምላሽ ይሰጣሉ። በማጣሪያ ጥያቄዎቹ በቂ ምላሽ ያገኘ የመሰለው አስጎብኚዬ ወደʼኔ ዞሮ፤ መኪናው ሰንቃጣ ድረስ እንደሚጓዝ ገለጸልኝ። “ፍሬወይኒ” በሚለው በሌላኛው ስያሜዋ የምትጠራው ሰንቃጣ ከተማ፤ በውቅሮ እና በአዲግራት መሃል ያለች ነች። ከተማይቱን ቀደም ሲል ወደዚያ አካባቢ ባደረግኳቸው ጉዞዎቼ ደጋግሜ አልፌባታለሁ። 

የጉዞ መዳረሻዬ ውቅሮ ከተማ መሆኑን እየተናገርኩ በመኪናው ጋቢና ተደላድዬ ተቀመጥኩ። ወሬ ለመመልከት ሁነኛ ቦታ በማግኘቴ እና መኪናውም ለክፍለ ሃገር ጉዞ ተመራጭ የሆነው የቶዮታ “ፎር ዊል ድራይቭ” መሆኑ አስደስቶኛል። ከመኪናው የኋላ ወንበር አንዲት ተጓዥ ተቀምጣለች። ከከተማ ውጭ ባለ በዚህ ቦታ ላይ፤ ሌሎች ተጓዦችን ለማግኘት ያለውን አስቸጋሪነት እያሰብኩ፤ “በቃ እዚሁ ጊዜውን መፍጀታችን” ነው አልኩ ለራሴ። በጠዋት ብንወጣ፣ ውቅሮን በውሎ ገብ ለመጎብኘት ያስችለኛል በሚል ነበር ለሰዓቱ መሰሰቴ። 

ያመጣኝን የባጃጅ ሹፌር ተሰናብቼ እንኳ ሳልጨርስ፤ መኪናው ከአንድም ሁለት ተጓዥ አገኘ። አንደኛው ተጓዥ አካል ጉዳተኛ ስለሆኑ፤ ቀድሜ የያዝኩትን የጋቢና ቦታ ለእርሳቸው ለቅቄ ወደ ኋላ ወንበር መዛወሬ ግድ ሆነ። ሁለተኛው ተጓዥ የእርሳቸው ረዳት በመሆኑ አብሯቸው ተቀመጠ። ጋቢናው ሞላ። ከኋላ ወንበር ግን ያለነው ሁለት ብቻ በመሆናችን፤ መኪናው ገና ሁለት ሰው ይፈልጋል። 

አጠገቤ የተቀመጠችውን ተጓዥ ወዴት እንደምትሄድ ጠየቅኋት። ወደ አዲግራት ቤተሰብ ለመጠየቅ እየሄደች እንደሆነ እና በዚሁ መኪና ዛሬውኑ ወደ መቐለ እንደምትመለስ ነገረችኝ። ከሹፌሩ ጋር ቤተሰብ እንደሆኑ እና በእርግጠኝነት ይዟት እንደሚመለስ ማስተማመኛ ስትሰጠኝ ውቅሮ ድረስ ለመጓዝ የነበረውን ሀሳቤን ቀይሬ አዲግራት ደርሼ ለመመለስ እዚያውኑ ወሰንኩ። 

ብዙም ሳይቆይ፤ ቅድም ሲያዋክቡን ከነበሩ “ደላላ” ወጣቶች አንዱ፤ የመኪናውን የበስተኋላ በር ከፍቶ አጠገባችን ተቀመጠ። ወጣቱ “ለሆነ ሰው ቦታ ይዞ መሆን አለበት” ስል ገመትኩ። መኪናው ወደ ፊት ከመንዳት ይልቅ ወደ ኋላ አዙሮ፤ ወደመጣንበት የከተማ አቅጣጫ ሲመለስ፤ በእርግጥም ቦታ የተያዘላቸውን ሰው ከቤታቸው ልንጭን እየሄድን እንደሆንን አረጋገጥኩ። 

“ኮብራው” ቀበሌ 16 የሚባለው ሰፈር ሲደርስ ቆመ። ሹፌሩ እና ደላላ መሳዩ ወጣት፤ ከጎናችን ካለው የሴቶች ጸጉር ቤት ላይ አይናቸውን ተከሉ። የሚጠበቁት ተጓዥ “ከአሁን አሁን ይመጣሉ” ተብለው ለደቂቃዎች ቢጠበቁም ድምጻቸው ጠፋ። ተጓዦች ትዕግስታችን አልቆ ማጉረምረም ጀመርን። ወጣቱ ጉዳዩን እንዲያጣራ ተላከ። ከደቂቃዎች በኋላ ተጓዡ ብቅ አሉ። እንደጠበቅኩት ትልቅ ሰው ሳይሆኑ፤ ወጣት ሴት ናት። መቆየቷ ምንም ግድ ያልሰጣት ይህች ሴት ወጣቱን ደላላ ተከትላ ወደ መኪናው ገባች። መኪናው፤ አራታችንንም በስተኋላ መቀመጫ አጣብቦ፤ ወደ ከተማይቱ መውጫ አቀና። 

እኛን መጀመሪያ የጫነበት ቦታ ላይ ሲደርስ፤ ጠዋት ላይ በአካባቢው ስለነበረው የከባድ መሳሪያ ተኩስ ጉዳይ ተነሳ። ተኩሱ ቦታው ላይ ከመድረሴ ከአስር ደቂቃ ገደማ በፊት እንደነበር እና ብዙም ሳይቆይ መቆሙ ተወራ። ለሊት ላይ ከነበረው ተመሳሳይ ተኩስ ጋር ተዳምሮ አካባቢው ሰላም መሆኑ ያጠያይቅ ጀመር። ጉዟችንም ስጋት ያዳመነበት ሆነ። ሆኖም ማናችንም፤ ይህን ሰምተን የጉዞ ዕቅዳችንን አልሰረዘንም። 

አጠገቤ የተቀመጠው ደላላ መሳዩ ወጣት፤ በዚህ መንገድ ከሰሞኑ በየቀኑ እንደሚመላለሱና እስካሁንም ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው በመንገር ሊያረጋጋን ሞከረ። መንገዱን ካወቀው ዘንድ በሚል፤ “በየመንገዱ በጣም ብዙ ፍተሻ አለ አይደል?” ስል ጠየቅኩ – መቐለ የሰማሁትን ወሬ ተተንርሼ። “አንድ ፍተሻ ብቻ ነው ያለው። እሱን ካለፍን ችግር የለም” አለኝ ወጣቱ በተዝናና መንፈስ። አላመንኩትም። “የህወሓት ተፈላጊ ሰዎችን እያደንን ነው” በሚባልበት እና አሁንም ውጊያ መኖሩ በሚነገርበት አቅጣጫ እየተጓዝን፤ 137 ኪሎ ሜትር ሙሉ እንዴት አንድ የፍተሻ ጣቢያ ብቻ ይኖራል?

በደቂቃዎች ውስጥ፤ መቐለ መውጪያው ላይ መሰቦ የሚባለው አካባቢ ባለው ዋናው ፍተሻ ጣቢያ ደረስን። በሌሎች መኪናዎች እንዳሉ ተጓዦች ሁሉ እንድንወርድ ተነገረን። ሁሉም መታወቂያውን እየያዘ ወረደ። ተራችን እስኪደርስ የሌሎቹን ፍተሻ እያየን ቆየን። ፍተሻውን የሚያከናውኑት ወታደሮች ናቸው። 

ለእኛ የደረሰን ፈታሽ በማመናጨቅ ስሜት ነው ጥያቄዎችን የሚጠይቀው። ሌሎቻችንን በዚያው ስሜት ፈትሾ ሲያበቃ፤ ያስረፈደችን ወጣት ሴት ላይ ሲደርስ ነገሮች ከረሩ። ወጣቷ በመታወቂያ ምትክ በእጇ የያዘችው የአንበሳ ባንክ የሂሳብ ደብተር ነው። የባንክ ደብተሩ ስሟን፣ ፎቶዋን እና በዛ ያለ የገንዘብ ዝውውሯን መረጃ ይዟል። 

“ይሄ ምንድነው?” አላት ወታደሩ በቁጣ።

“የባንክ ቡክ” ስትል መለሰች ወጣቷ። 

“የባንክ ቡክ መታወቂያ መሆን ይችላል?” በድጋሚ በቁጣ ጠየቃት። 

“መታወቂያዬ ጠፍቶብኝ ነው” አለች በሚለማመጥ ቅላጼ። ወታደሩ የወጣቷ መልስ አላሳመነውም። 

“ስልክሽን አምጪ” አላት በእጇ የያዘችውን የተጎሳቆለ “ስማርት ፎን” እያመለከተ። ሰጠችው። ወታደሩ ስልኩን ከፍቶ ለመመልከት ሞከረ እና ግራ የተጋባ መሰለ።  

“ፎቶዎቹን አሳይኝ” ሲል ወጣቷን አዘዛት። ወጣቷ የተባለችውን አደረገች። ሌሎችን ሲፈትሽ የነበረው ወታደር መጣና ጉዳዩ ምን እንደሆነ ጠየቀ። ይሄኛው ወታደር ትህትና የተላበሰ ነው። የእኛ ፈታሽ ስለ ጉዳዩ ነገረው። አብረው ስልኩን ሲመለከቱ ቆዩ። ‘በስልኩ ላይ ያለው የፎቶ ቁጥር እንዴት አነስተኛ ሊሆን ቻለ?’ በሚል የእኛ ፈታሽ ከወጣቷ ጋር ሲነታረክ ቆየ።  

የወጣቷ የአማርኛ ቅላጼ በጣሙኑ የትግርኛ ቋንቋ የተጫነው ነው። አንዳንድ ሀሳቦቿን በቅጡ በአማርኛ ለመግለጽ ትቸገራለች። ወታደሩ ይህንን ሁኔታዋን እንደማጭበርበር ወስዶታል። ድንገት፤ “አንቺማ የልዩ ኃይል ወታደር ነሽ” ሲል ሰማነው። ይህ አባባሉ የመቐለው አስጎብኚዬ ወጣት የነገረኝን አስታወሰኝ። “በከተማው የሚዘዋወሩ ወታደሮች እኔን የመሰሉ ወጣቶችን በተመለከቱ ቁጥር የልዩ ኃይል አባላት እንመስላቸዋለን” ብሎኝ ነበር። “አንድ ወታደር እንዲያውም የልዩ ኃይል አባላት የት እንደሚገኙ እንድነግረው ጠይቆኛል” ሲልም በገረሜታ አጫውቶኝ ነበር። 

ወታደሮች፤ የትግራይ ልዩ ኃይል አባል የሆኑ ወጣቶችን ለይተው ለማውጣት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል፤ ትከሻ ገልጦ መመልከት እንደሚገኝበት ከተለያዩ ሰዎች ሰምቻለሁ። ነገሩ ግር ቢለኝ “ለምን ትከሻ?” በማለት መጀመሪያ ነገሩን የሰማሁ ጊዜ ጠይቄ ነበር። “የልዩ ኃይል አባላት መሳሪያ የሚያነግቱት እና ሌሎች ተተኳሾች የሚሸከሙት በትከሻቸው ስለሆነ፤ በዚያ አካባቢ ምልክት አይጠፋም በሚል ነው ወታደሮቹ ልብስ ገልጠው የሚመለከቱት ” የሚል ምላሽ ተሰጥቶኛል። 

ይህ ገለጻ፤ በአዲስ አበባ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በከተማይቱ በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች የተሳተፉ ወጣቶችን ለመለየት በሚል የፌደራል ፖሊሶች ያደርጉት የነበረውን ነገር ወደ አእምሮዬ አመጣው። በወቅቱ ተቃውሞ በሚካሄድባቸው ቦታዎች በብዛት የተሰማሩት ፖሊሶች፤  ያገኙትን ወጣት ሁሉ እያስቆሙ “እጅህን አሳይ” እያሉ ይመለከታሉ። እጆቹ በአቧራ የተሸፈኑ አሊያም የቆሸሹ፤ ከድንጋይ ወርዋሪዎቹ ተቃዋሚ ወጣቶች አንዱ ነው በሚል ይያዝ ነበር። 

የመቐለ ሰዎች፤ ወታደሮቹ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላትን ለመለየት የሚጠቀሙበትን ሌላም ዘዴ ነግረውኛል። ይሄኛው ደግሞ ወደ ቁርጭምጭሚት አካባቢ ያለውን የእግር ክፍል ገልጦ ማሳየት ያስገድዳል። የልዩ ኃይል አባላቱ ያደርጉት የነበረው ወታደራዊ ጫማ፤ በዚህኛው የሰውነት ክፍል አካባቢ የሚተወውን ምልክት እንደ አንድ ማረጋገጫ እንደሚወሰድ ሰምቼያለሁ። በደቂቃዎች ውስጥ በልዩ ኃይል አባልነት ወደተጠረጠረችው፤ አብራን ወደምትጓዘው ወጣት ትኩረቴን አደረግኩ።  

የነገሩ መክረር ያሳሰባቸው ሹፌሩ እና ደላላ መሳዩ ወጣት ነገሩን ለማለዘብ ጣልቃ ገቡ። ወጣቷን እንደሚያውቋት እና የጸጉር ስራ ባለሙያ እንደሆነች ነገሩት። በዚህም ምላሽ ፈታሻችን አልረካም። ወጣቷን ተጨማሪ ጥያቄዎች ጠየቃት። እምብዛም ሳትደናገጥ አጠር አጠር ያለ ምላሾች ሰጠችው። በስተመጨረሻ ፈታሻችን፤ ከትሁቱ ወታደር ጋር ተነጋግሮ እንድንሄድ ፈቀደልን። ሁሉም ተጓዥ እፎይ አለ። በስተኋላ ላይ ስሰማ ወጣቷ የጸጉር ስራ ባለሙያ ብቻ ሳትሆን፤ ጠዋት የተመለከተነው ተለቅ ያለ ጸጉር ቤት ባለቤት ጭምር ናት።  

ወደ መኪናችን ተመልሰን ጉዞ እንደጀመርን ተለቅ ያለችውና አጠገቤ የተቀመጠችው ሴት፤ ወዲያውኑ ስልኳን አውጥታ ፎቶዎችን ማጥፋት ጀመረች። ለምን እንደዚያ እንደምታደርግ ጠየቅኋት። “ስልክሽን አምጪ ስትባል እናንተ እኮ ምንም አልመሰላችሁም። እኔ እየተንቀጠቀጥኩ ነበር” አለች ለሁላችንም በሚሰማ ድምጽ። አሁንም ስላልገባኝ ነገሩን አንድታብራራልኝ ጠየቅኋት። “እንዴ! ስልኬ ላይ ያለው የደብረጽዮን፣ የመለስ ፎቶ ቢያዩ አይለቁኝም” አለች። ይሄ አባባሏ ከዓመታት በፊት “በስልካቸው ላይ የኦነግ ባንዲራ ተገኝቶባቸዋል” ተብሎ በፍርድ ቤት በክስ ማስረጃነት የቀረበባቸውን ሰዎች አስታወሰኝ። 

* * *

ስጋት የተጫነው ጉዟችንን በዝምታ ተያይዘነዋል። ዝምታው ግን እምብዛም አልዘለቀም። በትግራይ የነበረውን የውጊያ መጠን የሚያሳዩ ቅሪቶችን መመልከት ስንጀመር በማብራሪያዎች የታጀበ የተጓዦች ውይይት ተከፈተ። በውጊያው ጉዳት የደረሰበት እና መንገድ ዳር የቆመ የመጀመሪያውን ታንክ ያየነው ከመቐለ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ካለቸው አጉላዕ ከተሰኘችው አነስተኛ ከተማ እንኳ ሳንደርስ ነው። ደቂቃ ሳይቆይ ሌላ ታንክ ተደገመ። 

አጉላዕን አለፍ እንዳለን ደግሞ በአንድ ቦታ ላይ የተቃጠሉ እና ወደ ጎናቸው የተገለበጡ አራት ወታደራዊ እና የጭነት ተሽከርካሪዎችን ከዕይታችን ገቡ። አጠገቤ ያለችው ሴት ድንጋጤዋን “ዋይ” በሚሉ ቃላት እያጀበች ትገልጻለች። ትንሽ ፈቀቅ እንዳለን በቃጠሎ ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ሁለት አውቶብሶችን አየን። በሁለቱ መጓጓዣዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የቀደመ ቀለማችውን እና ስሪታቸውን እንኳን ለመለየት ያዳግታል። አጠገብ ለአጠገብ ካሉት ከእነዚሁ አውቶብሶች አቅራቢያ የተቃጠሉ እና የተገለበጡ ሶስት ተሽከርካሪዎች አሉ። 

ውቅሮ መግባታችንን የሚያመለክተው በብረት የተሰራ የከተማይቱ በር ጋር ከመድረሳችን በፊት ባሉት ሶስት ደቂቃዎች ውስጥ እንደዚሁ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች መኪናዎች ተመልክተናል። ጣሪያው የተሰረጎደ ፒክ አፕ፣ በእሳት የነደዱ እና በግራ እና በቀኝ የተፈነገሉ አራት ወታደራዊ የጭነት መኪናዎች፣ “አንደኛ ደረጃ” የሚል መለያ ከፊቱ የለጠፈ፥ መስታወቶቹ የረገፉ፥ አረንጓዴ እና ነጭ ቅብ ሜርሴዲስ ቤንዝ የህዝብ መጓጓዣ አውቶብስ፣ “ኦራል” በሚል መጠሪያቸው የሚታወቁ የተገለበጡ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፤ በመንገድ ዳር ቆመው ለመጪ ሂያጁ ውጊያው ምን ይመስል እንደነበር ይመሰክራሉ። 

በመንገዳችን ላይ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላትን የጫኑ ቢያንስ ስድስት ተሽከርካሪዎች ተመልክቻለሁ። በፒክ አፖች ላይ ያሉቱ፤ በተሽከርካሪው ጣሪያ ላይ የተደገነ መትረየሳቸውን ቃታ የያዙ ወታደሮች እና ፖሊሶችን ከፊት አሰልፈዋል። ሌሎቹ ወታደሮች እና ፖሊሶችም መሳሪያዎቻቸውን በተጠንቀቅ ይዘው ዙሪያቸውን እየቃኙ ነበር የሚጓዙት። አንዳንዶቹ ፊታቸውን ከንፋሱም ሆነ ከአቧራው ለመከለከል በሚመስል ሁኔታ ተሸፋፍነዋል። 

ወደ ውቅሮ ስንገባ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ሆኗል። ጥቂት በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ከተማይቱን አቋርጧት በሚያልፈው አውራ ጎዳና ውር ውር ይላሉ። ከጠበቅኩት ከፍ ያለ የሰው እንቅስቃሴ ይታያል። ደላላ መስሎኝ የነበረው እና በጨዋታችን መሃል የጋራዥ ሰራተኛ መሆኑን የነገረኝ ወጣት፤ በከተማው ስለተገደሉ ወጣቶች፣ በህንጻዎች እና የንግድ መደብሮች ላይ በጥይት እና በከባድ መሳሪያ ስለደረሰው ጉዳት ማብራሪያ መስጠት ጀመረ። በከተማይቱ ጎልቶ የሚታየውን ባለ አራት ፎቅ ህንጻ  እንድመለከት በጣቱ ጠቆመኝ። 

በማህበር መሰራቱ የተነገረኝ፣ “ዕዳጋ ማእከል” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ህንጻ በተንጣለለ ስፍራ ላይ የተገነባ ነው። ወደ ጎን ረዥም ነው። ለሚመለከተው ስድስት አነስተኛ ህንጻዎች ተቀጣጥለው የተሰሩ የሚመስል ስሜት ይሰጣል። ስድስቱም የህንጻው ክፍሎች በአብረቅራቂ መስታወት ተሸፍነዋል። ወጣቱ ተመልከት የሚለኝም በጥይት የተበሳሱትን እና መሃል ላይ በርካታ ቀዳዳዎችን ያበጁትን መስታወቶቹን ነው። ስድስቱም የህንጻው ክፍሎች በዚህ መልኩ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ወጣቱ ሹፌራችን መኪናዋን ከህንጻው ብዙም ሳይርቅ አቆማት። ይሄኔ ውቅሮ የምትታወቅበትን የሽምብራ እና የገብስ ቆሎ የያዙ ወጣቶች ወደ እኛ ተጠጉ። ለራሱም፣ ለቤተሰቡም መግዛት የፈለገ ሁሉ በኪሎ ያሰፍር ገባ። ቆሎ ለመግዛት በቆምንበት ደቂቃዎች ውስጥም ሆነ ውቅሮን ተሰናበትን እስክንወጣ ድረስ በተቀመጥኩበት ሆኜ ዙሪያ ገባውን በተቻለኝ መጠን ለመቃኘት ሞክሬያለሁ። 

ከመንገዳችን ግራ እና ቀኝ በተደረደሩ ህንጻዎች፣ የንግድ መደብሮች፣ ባንኮች እና ሌሎች በርካታ አገልግሎት መስጪያዎች መጎዳታቸውን ተመልክቻለሁ። ከሚታዩት ውስጥ የብዙዎቹ ህንጻዎች ተሰባብረዋል። በጥይት የተበሳሱም በርካቶች ናቸው። አንዳንዶቹ ዘረፋ እንደተካሄደባቸው በአቅራቢያቸው ከተዝረከረኩ ቁሳቁሶች መረዳት ይቻላል። ከአንድ የጫማ መሸጪያ ሱቅ ፊት ጫማዎች የሚቀመጡባቸው በርካታ ባዶ ካርቶኖች በየቦታው ተበታትነው አይቻለሁ። በርካታ ሞባይል መሸጪያ ሱቆች የዘረፋው ሰለባ መሆናቸውን በወፍ በረሩ ምልከታዬ ታዝቤያለሁ።      

አብረውኝ የሚጓዙት ሰዎች በህዝብ ንብረት ላይ በዚህ መልኩ ጉዳት በመድረሱ አዝነዋል። በውቅሮ ለተገደሉ ሰዎች እና ለደረሰው አብዛኛው ጉዳት ተጠያቂዎቹ የኤርትራ ወታደሮች መሆናቸውንም ይነጋገራሉ። ወደ ከተማይቱ መውጫ ስንቃረብ ሁለት ነጭ መጋዘን መሰል ነገሮች እና አንድ መለስተኛ ህንጻ ከርቀት ተመለከትኩ። ዙሪያውን በታጠረ ግቢ ውስጥ የሚገኙት መጋዘኖች የሰማይታ እምነበረድ ፋብሪካ ማምረቻዎች መሆናቸውን ወደ ቦታው ስንጠጋ ተረዳሁ። 

በትግራይ ክልል በነበረው ውጊያ፤ ከፍ ያለ ውድመት እና ዘረፋ ከደረሰባቸው ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነው ሰማያታ አራት ሄክታር በሚጠጋ የተንጣለለ መሬት ላይ የተገነባ ነው። የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ማምረት የጀመረው ፋብሪካው 400 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት በወቅቱ ተነግሮ ነበር። ፋብሪካው አጠገብ ስንደርስ ከሁሉ አስቀድሞ አይኔ የገባው፤ በቅጥር ግቢው መግቢያ በስተግራ ካለው ባለ ሶስት ፎቅ ህንጻ ፊት የቆመች ፒክ አፕ መኪና ነች። መኪናዋ አራቱንም ጎማዎቿን አጥታ ተሰናክላ ቆማለች። ባለ ሁለት ጋቢና የሆነችው የዚህችው መኪና አራት በሮችም ተገንጥለው መለመላዋን ቀርታለች። የዕቃ መጫኛ ክፍሏ የኋላ መከለያም በቦታው የለም።

በአብረቅራቂ መስታወት ወደተሸፈነው የፋብሪካው ህንጻ አማተርኩ። በስተቀኝ ጎኑ ባለው መስታወት ላይ ከሚታየው ሽንቁር ባሻገር የከፋ ጉዳት የደረሰበት አይመስልም። ፋብሪካው ላይ በከባድ መሳሪያ የደረሰ ውድመት ይኖር እንደሁ በሚል፤ ካለፍነውም በኋላ ዞሬ አተኩሬ መረመርኩት። ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት፤ በትግራይ ያሉ ፋብሪካዎች በከባድ መሳሪያ መመታታቸውን የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ሲዘዋወሩ በመመልከቴ ሰማያታም ያ ዕጣ ፈንታ ገጥሞት እንደሁ ማረጋገጥ ነበረብኝ። ከርቀት እንደተመለከትኩት ከሆነ ነጭ ቀለም የተቀቡት ሁለቱ የማምረቻ መጋዘኖች ላይ ጉልህ የሆነ ውድመት አይታይም።

አብረውኝ የሚጓዙት ሰዎች ስለ ፋብሪካው እየተወያዩ ነው። ሹፌሩ እና የጋራዥ ሰራተኛው፤ ፋብሪካው በኤርትራውያን ወታደሮች እንደተዘረፈ መስማታቸውን ነገሩን። በመቐለ ካነጋገርኳቸው ሰዎች ውስጥ አንድ ሁለቱ፤ ኤርትራውያን ወታደሮች የዚህን ፋብሪካ ማሽን ነቅሎ ለመውሰድ ቀናቶች እንደወሰዱባቸው አጫውተውኝ ነበር። 

መኪናችን ጉዞዋን ቀጥላለች። ሹፌራችን በጨዋታችን መሃል በስተቀኝ ያለ ኮረብታን እንድናይ አመለከተን። በአረንጓዴ ቁጥቋጦዎች በተሸፈነው ዳገታማ ቦታ ላይ ወጣ ያለ ድንጋያማ ኮረብታ ይታያል። ኮረብታው ጫፍ ላይ፤ ግድግዳው አረንጓዴ እና ነጭ የተቀባ ቤተክርስቲያን ተቀምጧል። ሹፌራችን ቤተክርስቲያኑ የአማኑኤል እንደሆነ እና በካባድ መሳሪያ መመታቱን ነገረን። አጠገቤ የተቀመጠችው ሴት በድንጋጤ ክው ብላ “እዋይ….እዋይ” አለች። ቤተክርስቲያኑ ከዋናው መንገድ ርቆ የሚገኝ በመሆኑ፤ ጉዳቱ ምን ያህል እንደሆነ ግን በቅጡ መመልከት አልቻልኩም።  

ሹፌራችን በአል ነጃሺ መስጊድ ላይም ተመሳሳይ ጉዳት መድረሱን እያጫወተን፤ ዳገታማ እና ጠመዝማዛ በሆነው መንገድ ላይ በዝግታ ያሽከረክራል። ወደ አንደኛው መታጠፊያ ስንደርስ አስፋልት የነበረው መንገድ ተቀይሮ የተቆፋፈረ፤ በአፈር እና በድንጋይ የተሞላ ቦታ ገጠመን። የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት፤ ወደ መቐለ እያመራ የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት ጉዞ ለማስተጓጉል መንገዱን አፍርሰውት እንደነበርና በስተኋላ መጠገኑን ሹፌራችን ገለጸልን። ያገጠጠ አለት በአንድ ወገን እንደ ግድግዳ የቆመበትን፤ ይህን ቦታ ከተሻገረን ከደቂቃዎች በኋላ ወደ አነስተኛዋ ነጋሽ ከተማ ገባን።

ከተማይቱ እምብዛም እንቅስቃሴ አይታይባትም። የጋራዥ ሰራተኛው ከርቀት የሚታይ፣ የሚያንጸባርቅ ወርቃማ የመስጊድ ሚናራን እያመለከተ “ያውና የተመታው መስጊድ” አለ። ወደ መስጊዱ ስንቃረብ፤ አዛን የሚተላለፍበት ድምጽ ማጉያ ከተሰቀለበት የሚናራው ክፍል በላይ ያለው ቦታ፤ ጠቁሮ ተመለከትኩ። “የተመታው እርሱ ነው” አለን የጋራዥ ሰራተኛው ወጣት። ሚናራው በካባድ መሳሪያ ተመትቶ አለመፍረሱ ገረመኝ። በሩ በተዘጋው መስጊድ ላይ የደረሰውን ሙሉ ጉዳት ከዚህ በላይ ማየት አልቻልኩም። ሹፌራችን በጊዜ አዲግራት ለመግባት መኪናዋን በፍጥነት ማሽከርከሩን ተያይዞታል።

ከነጋሽ ከተማ እንደወጣን ከመንገድ ዳር ተሰናክሎ ከቆመ ታንክ ጋር ተገጣጠመን። ለሹፌሩ እንደ ረዳት ሆኖ የሚያገለግለውና ከሰሞኑ በመንገዱ የተመላለሰው የጋራዥ ሰራተኛ ታንኮቹን የሸመደዳቸው ይመስላል። አንዳቸውን ከሌላቸው ጋር በሚያነጻጽር አገላለጽ “ይሄኛው ዘመናዊ ነው” አለ። ታንኩ ባለ ሰንሰለታማ እግር ያለው ነው። ከስድስቱ የብረት ጎማዎቹ አንዱ ተፈርክሶ ሰንሰለቱም ተበጥሷል። ታንኩ የነዳጅ በርሜል የሚጭንበት የብረት አቃፊም ቀፎውን ቀርቷል። 

ከሃያ ገደማ ደቂቃ ጉዞ በኋላ ፍሬወይኒ (ሰንቃጣ) ስንደርስ ከተማይቱ በዝምታ ተውጣ አገኘናት። ከተማይቱን አቋርጦ በሚያልፈው አውራ ጎዳና ዳር ያሉ አብዛኞቹ የንግድ መደብሮች እና ሌሎች ቤቶች በር እና መስኮታቸው እንደተከረቸመ ነው። በመንገዱ ዳር የሚታዩት ሰዎችም በቁጥር አነስተኛ ናቸው። ከተማይቱን እንዲህ በጨረፍታ አይተን አለፍናት። ዕዳጋ ሐሙስ ልንደርስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩ በሹፌሩ እና  አጠገቡ በተቀመጡት ሰዎች ሁለት ተጓዦች መካከል ድርድር የመሰለ ውይይት ተከፈተ። 

ተጓዦቹ መውረጃቸው እንደደረሰ ከንግግራቸው ተረድቻለሁ። ድርድሩ የነበረው፤ ጋቢና ከተቀመጡት የአካል ጉዳተኛ ተጓዥ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ከዚህ ቀደም ሹፌር የነበሩት እኚህ ተጓዥ፤ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ሁለት እግሮቻቸው መንቀሳቀስ የማይችሉ በመሆናቸው ተንቀሳቃሽ ወንበር የሚጠቀሙ ናቸው። መኪና ላይ ለመውጣት እና ለመውረድ እንኳ በረዳታቸው ታዝለው ነው። የአካል ጉዳተኛው መኖሪያ ከዋናው መንገድ ታጥፎ ወደ ውስጥ ወደ ገጠር የሚያስገባ በመሆኑ፤ ሌላ ተጨማሪ ማጓጓዣ ማፈላለግ ግድ ይላል። ይህን ችግር የተረዳው ሹፌር ወደ ዕዳጋ ሐሙስ አቅጣጫ የሚጓዝ አንድ ባጃጅ ሲያገኝ መኪናውን አቆመ። 

አካል ጉዳተኛው ተጓዥ ወደ ባጃጁ ተሸጋግረው እኛ ጉዟችንን እንደምንቀጥል ስጠብቅ፤ መኪናችን መንገድ ዳር በቆመችበት ተጨማሪ ድርድር በትግርኛ ቋንቋ ቀጠለ። ከአፍታ ቆይታ በኋላ መኪናችን ተንቀሳቀሰች። የሚባባሉት ባይገባኝም ድርድሩ ግን አሁንም ቀጥሏል። ድንገት መኪናችን በስተግራ ወዳለ ኮረኮንች መንገድ ታጠፈች። ይሄኔ ሹፌራችን አካል ጉዳተኛውን ቤታቸው ሊያደርሳቸው እንደተስማማ ገባኝ። ጥቂት እንደሄድን አንዲት ጥቁር ፒክ አፕ መኪና አይናችን ገባች። 

ባለ አንድ ጋቢናዋ መኪና፤ ከሰማያታ እምነበረድ ፋብሪካ ፊት ለፊት እንዳየኋት ፒክ አፕ ሁሉ በሮቿ ተነቅለው ተወስደዋል። የኋላ ጎማዎቿም ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል። የኮፈኗ መሸፈኛ ብረት ተገንጥሎ ተወስዶ አጽሟን ቀርታለች። አካል ጉዳተኛው እና ረዳታቸው መኪናዋ የኢሳያስ መሆኗን ተናገሩ። ኢሳያስ በአዲግራት በትልቅነቱ በመጀመሪያ ረድፍ ላይ የሚቀመጥ እና ግንባታው ወደ መጠናቀቁ የደረሰ ህንጻ ባለቤት ነበር።

በከተማይቱ የታወቀ ባለሃብት የነበረው ኢሳያስ ከእነ ልጆቹ፤ በኤርትራ ወታደሮች መገደሉን መቐለ ጭምር እያለሁ ሰምቻለሁ። በመቐለ ያገኘሁት አንድ ሰው እንደውም ስለዚህ ባለሃብት አንድ ወታደር የነገረውን አጫውቶኛል። ወታደሩ “መሞት ያልነበረበት ሰው ሞተ” ሲል በሀዘን ተሞልቶ እንደነገረው የመቐለው ነዋሪ ጠቅሶልኛል። የኢሳያስ ጉዳይ፤ በአዲግራት በኤርትራውያን ወታደሮች ተፈጽመዋል ለሚባሉ ግድያዎች እንደ አንድ ሁነኛ ማሳያ በተደጋጋሚ ሲነሳ ሰምቼያለሁ። የአዲግራት ተወላጅ የሆነው ሹፌራችን፤ ኤርትራውያኑ ወታደሮች ኢሳያስን ከገደሉ በኋላ፤ ይጠቀምበት የነበረውን ላንድክሩዘር ተሽከርካሪ መውሰዳቸውን ነግሮናል። በጥቁሯ ፒክ አፕ ላይ የተፈጸመውን የመኪና መለዋወጫ ዘረፋም እነርሱው ሳያደርጉት እንዳልቀረ ጥርጣሬውን አጋርቶናል።

ይህን መሰሉን ጉዳይ እያወራን በኮረኮንቹ መንገድ ወደ ገጠር ውስጥ መጓዛችንን ቀጥለናል። የጋራዥ ሰራተኛው ወጣት፤ አሁን እየሄድንበት ባለው አካባቢ በርካታ ወጣቶች ቤተክርስቲያን ተሳልመው ሲመለሱ መገደላቸውንም ነገረኝ። በዕዳጋ ሐሙስ በጅምላ ተገድለዋል ስለተባሉ ሰዎች ሲነገር በተደጋጋሚ ሰምቼያለሁ። ሟቾቹ ከ120 እስከ 150 ይደርሳሉ ሲባል ብሰማም፤ ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ቅርብ የሆኑ ሰው ግን የተገደሉት ሰዎች 86 መሆናቸውን ከታማኝ ምንጭ መረዳታቸውን ነግረውኝ ነበር። “የዕዳጋ ሐሙስ ግድያ” እየተባለ የሚጠራው ሁነት በትክክል በዚህ አካባቢ የተፈጸመ መሆኑን ለማረጋገጥ ጠየቅኩ። አካባቢው ይሄው መሆኑ ተነገረኝ።  

የግጥምጥሞሹን ነገር ማመን አልቻልኩም። ወደ አዲግራት ለመሄድ በተሳፈርኩበት መኪና፤ በአጋጣሚ የተሳፈሩ ሰው አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ምክንያት፤ መኪናችን ሰተት ብሎ ድርጊቱ የተፈጸመበት ቦታ እንደወሰደኝ ተመልክቼ በገረሜታ ራሴን ወዘወዝኩ። ሹፌራችን ለመኪና አስቸጋሪ በሆነ ኮረኮንቻማ መንገድ፤ ወደ ገጠር ውስጥ ብዙ እንዲገባ በመደረጉ እየተነጫነጨ ይጨቃጨቃል። እኔ ደግሞ ሰዎቹ ቤታቸው ከመውረዳቸው በፊት ስለ ሁነቱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጣደፍ ጣደፍ እያልኩ ጥያቄ አከታትላለሁ። ሁለቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ለሹፌሩም፤ ለእኔም ይመልሳሉ። 

ከሁለቱ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተረዳሁት ድርጊቱ የተፈጸመው ህዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዕለቱን የቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ በዓል አድርጋ በየዓመቱ ታከብረዋለች። ክብረ በዓሉ በተለይ በደመቀ ሁኔታ የሚከበረው በዚያው በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በሚገኘው ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ነው። ይህንኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል፤ ዕዳጋ ሐሙስ አቅራቢያ በምትገኘው ቤተክርስቲያን አክብረው ሲመለሱ የነበሩ ምዕመናን ላይ ነው እንግዲህ የኤርትራ ወታደሮች ግድያ ፈጸሙ የሚባለው። አብሮን የሚጓዘው የአካባቢው ነዋሪ፤ በዕለቱ የ70 ሰዎችን አስክሬን ተመልክቼያለሁ ብሎኛል።

ኤርትራውያን ወታደሮች ነዋሪዎቹን የገደሉት በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ሚሊሺያዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸው የተወሰኑ ጓዶቻቸው ከሞቱ  በኋላ እንደሆነ ከአንድም ሁለት ሰዎች ነግረውኛል። በምዕመናኑ ላይ የወሰዱትም የበቀል እርምጃ እንደሆነ እነዚሁ ሰዎች ያስረዳሉ። ጥቃቱ ተፈጽሞበታል የተባለው ቦታ አቅራቢያ ስንደርስ መኪናችን ቆመች። የአካል ጉዳተኛውን ተጓዥ፤ ከኮብራዋ መኪና በጥንቃቄ አውርደው በተንቀሳቃሽ ወንበር እስኪያደላድሉ ድረስ፤ ምዕመናኑ በዓል ሲያከብሩባት ነበር የተባለችውን የማርያም ቤተክርስቲያን እና ዙሪያ ገባውን ለመመልከት እንደነገሩ ከታጠረው የገጠር መኖሪያ ቅጽር ግቢ ወጣሁ። 

በአካባቢው ያለው ጥልቅ ጸጥታ ከርቀት ያሉ ህጻናት የሚጯጯሁትን ሁሉ ያሰማል። ከርቀት ግዙፍ ድንጋያማ ኮረብታ ይታያል። ከዚሁ ኮረብታ ወረድ ብሎ፤ ከፍ ያለ ቦታ ላይ አንድ ቤተክርስቲያን ጉብ ብሏል። ይህ ቤተክርስቲያን የተገደሉት ምዕመናን ለክብረ በዓል የመጡበት እንዳልሆነ፤ አብሮን የተጓዘው ወጣቱ የአካባቢው ነዋሪ ቀደም ብሎ ገልጾልኛል። ከቆምኩበት ቦታ ለአይን የማይታየው የማርያም ቤተክርስቲያን የተገነባው ከመጀመሪያው ቤተክርስቲያን በቅርብ ርቀት ላይ ነው። ሸለቆ ከሚመስለው የማርያም ቤተክርስቲያን ካለበት ቦታ ወደ ኮረብታ የሚያወጣ በአቧራ የተሸፈነ ጥርጊያ መንገድ ይታያል።

በአካባቢው ግማሽ ሰዓት ያህል እንኳ ብንቆይ፤ ወደ ቤተክርስቲያኑ መውረድ እችል እንደነበር እያሰበኩ ተቆጨሁ። ተጨማሪ የዓይን ምስክሮችንም የማነጋገር ዕድል ይኖረኝ ነበር። ወደ አካል ጉዳተኛው ቅጥር ግቢ ተመልሼ እየሆነ ያለውን ስመለከት ምኞቴ እውን የሆነ መስሎኝ ተነቃቃሁ። የተጓዡ ቤተሰብ የሆኑ በእድሜ የገፉ እናት፤ “የሆነ ነገርማ ሳትቀምሱ አትሄዱም” በማለት ሹፌሩን እና ሌሎች ተጓዦችን እየለመኑ ነው። ሹፌሩ በቶሎ አዲግራት ደርሰው ወደ መቐለ መመለስ እንዳለባቸው ነግሮ ግብዣቸውን በጨዋነት ሊያስቀር ይሞክራል። እርሳቸው ይለምናሉ። በስተመጨረሻ ሌሎቹም ተጓዦች በጉዳዩ ላይ ገቡበትና ወዲያውኑ የመመለሳችን ነገር እርግጥ ሆነ።  

በአካባቢው የነበረንን ቆይታ አጠናቀን ዕዳጋ ሐሙስ ወደሚወስደን አውራ ጎዳና ላይ ለመውጣት የመልስ ጉዞ ስንጀምር ሰዓቱ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ተሻግሮ ነበር። ወደ ዋናው መንገድ መውጪያ ስንቃረብ፤ ውልቅልቋ ወጥቶ በኮንረኮንቹ መንገድ ላይ ተጥላ የነበረችው ጥቁር ፒክ አፕ፤ በመኪና ጎታች ተሽከርካሪ ለመወሰድ ስትዘገጃጅ አየናት። ሹፌሩ መኪናውን ለመውሰድ ከመጡት የጋራዥ ባለሙያዎች ጋር ሰላምታ ተለዋወጠ። አጠገቤ የተቀመጠው የጋራዥ ሰራተኛ፤ ባለሙያዎቹን እንደሚያውቃቸውና ከአዲግራት የመጡ እንደሆኑ ነገረኝ። 

መኪናችን በዋናው አውራ ጎዳናው መሽከርከር በጀመረች አምስት ደቂቃ ባለሞላ ጊዜ ወደ ዕዳጋ ሐሙስ ከተማ “እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚል በትግርኛ፣ በእንግሊዘኛ እና በአማርኛ ቋንቋዎች የተጻፈበት የብረት ቅስት ከፊታችን ተደቀነ። ወደ ከተማይቱ መሃል ስንዘልቅ መጀመሪያ አይኔ ተወርውሮ ያረፈው፤ በመብራት አካፋይ የተለየውን ባለሁለት መስመር መንገድ፤ የግራውን ክፍል ዘግቶ የቆመ አንድ ወታደራዊ የጭነት ተሽከርካሪ ነው። ተሽከርካሪው ከኋላው ይጎትተው ከነበረው አነስተኛ መድፍ ጋር ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል። 

እኛ በምንጓዝበት የመንገዱ አቅጣጫ ሌላም የተቃጠለ የተሽከርካሪ ቅሪት ከርቀት ተመለከትኩ። ስንቀርበው ተሽከርካሪው አውቶብስ መሆኑን ተረዳሁ። አውቶብሱ በቃጠሎ እንዳልነበር ሆኖ አጽሙ ብቻ ቀርቷል። አጠገቤ የተቀመጠችው ሴት እንደተለመደው የድንጋጤ ድምጽ አሰማች። የአውቶብሱ ሁኔታ ለመጀመሪያ ቀን ለተመለከተችው ለእርሷ ክፉኛ ቢያስደነግጣትም፤ ለከተማይቱ ነዋሪዎች ግን እምብዛም ግድ የሰጣቸው አይመስልም። ከአውቶብሱ ጎን ባለው የእግረኛ መተላለፊያ መንገድ ላይ ቁጭ ያለች ሴት ዘይት እና በማዳበሪያ የተቀመጠ እህል ተቸረችራለች። በአጠገቧ አትክልት በሚጓጓዝባቸው የእንጨት ሳጥኖች ላይ የተቀመጡ የከተማይቱ ሰዎች ይታያሉ። በአንደኛው ሳጥን ላይ ሚዛን ተቀምጧል። 

በርከት ያሉ የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ በዋናው መንገድ ሁለቱም አቅጣጫዎች፤ ዕለታዊ ጉዳያቸውን ለመከወን በእግራቸው ወዲያ ወዲህ እያሉ ነው። ባጃጆች እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች በመንገድ ዳር ቆመው ቢታዩም ብዙም ሲንቀሳቀሱ አይስተዋልም። ወደ ከተማይቱ መውጪያ ስንቃረብ በመግቢያችን ላይ ካየናቸው በተጨማሪ ሌሎች ሶስት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ ቆመው ተመለከትኩ። እነዚህ ተሽከርካሪዎች ምን ሆነው እንደዚያ እንደቆሙ ማብራሪያ የሚሰጠኝ ባላገኝም በአካባቢው የነበረውን ውጊያ መጠን ይበልጥ የሚያሳዩ ሆነው አገኝቼያቸዋለሁ። 

የመጀመሪያው በምንጓዝበት አቅጣጫ ተሰናክሎ የቆመ ታንክ ነው። ባለሰንሰለታማ የሆነው አንደኛው እግሩ የእግረኞች መተላለፊያን ሸፍኖ የቆመው ይህ ታንክ በቃጠሎ ውድሟል። አስተኳሾች የሚቆበት የላይኛው ክፍሉ ተገንጥሎ ከእግረኛ መተላለፊያ አጠገብ ወድቋል። ሁለተኛው ወታደራዊ ተሽከርካሪ፤ ገና ከፋብሪካ የወጣ የሚመስል እና የተወሰኑ ክፍሉ በጥቁር አረንጓዴ ጨርቅ የተሸፈነ መድፍ ነው። በዚያው አቅጣጫ ከተማይቱ ጫፍ ላይ፤ ወደ አንድ ጎኑ አዘንብሎ የቆመ “ኦራል” የጭነት ተሽከርካሪም አለ። አንድ ጎማ ብቻ የተረፈለት ተሽከርካሪው፤ እንደ ድጋፍ ድንጋዮች ከስር ተደረድረውታል። በሹፌሩ በኩል ያለው በሩም ወለል ብሎ ተከፍቷል። 

ዕዳጋ ሐሙስ እስካሁን ካየኋቸው ከተሞች ሁሉ የውጊያው ጠባሳ በደንብ የሚታይበት ከተማ መሆኗን ተመልክቻለሁ። ብዙዎቹ የንግድ መደብሮቿ እና አገልግሎት መስጪያዎቿ ከፍ ያለ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በራቸው የተገነጠለ፣ የተቃጠሉ፣ መስታወታቸው የተሰባበረ እና ዝርፊያ የተፈጸመባቸው የሚመስሉ በቁጥር በርከት ይላሉ። የአንበሳ ባንክ ቅርንጫፍ ያለበት የከተማይቱ ክፍል በተለይ ክፉኛ ተጎድቷል።

አነስተኛይቱን ከተማ ተሰናብተን ወደ አዲግራት ስንጠጋ፤ ውጊያው ያደረሰበት ከፍ ያለ ውድመት በግልጽ የሚታይ ፋብሪካ ተመለከትኩ። ፋብሪካው ጎዳ ጠርሙስ እና የብርጭቆ ፋብሪካ ይባላል። መንገድ ዳር ባለው በዚህ የፋብሪካ ቅጽር ግቢ ውስጥ ባለ አራት ፎቅ ህንጻ እና ሶስት ነጫጭ መጋዘን መሳይ ማምረቻዎች ይታያሉ። ከሶስቱ ማምረቻዎች መካከል ትልቁ እና በመሃል ላይ የተገነባው መጋዘን በአንድ ጎኑ በፍንዳታ የወደመ ይመስላል። ከፍንዳታው ያመለጡት የማምረቻው ግድግዳ የነበሩት ጠንካራዎቹ ኤጋ ቆርቆሮዎች፤ ንፋስ እንዳበላሸው ሻተር ተወለጋግደው እና ተዘንጥለው ቆመዋል። 

ሹፌራችን ፋብሪካው እንዲህ የሆነው በካባድ መሳሪያ ተመትቶ እንጂ በፍንዳታ አለመሆኑን ነገረን። ፋብሪካው ከደረሰበት ውድመት በተጨማሪ በኤርትራ ወታደሮች ዘረፋ እንደተፈጸመበት ገለጸልን። ኤርትራውያኑ ወታደሮች፤ ጣሊያን ስሪት የሆኑትን ማሽኖቹን ነቅሎ ለማጓጓዝ፤ የአካባቢው ነዋሪዎችን አስገድደው የጉልበት ስራ እንዲሰሩ ማድረጋቸውንም አከለልን። ስለ እነዚህ የአካባቢው ነዋሪዎች የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ሁለት የተጣረሱ መረጃዎች ሰምቻለሁ።

ገሚሱ “ነዋሪዎቹ ማሽኖቹን የመንቀል እና የማጓጓዝ ሚናቸውን ከተወጡ በኋላ ተገድለዋል” ይላል። ሌሎች ደግሞ “ነዋሪዎቹ ከማሽኖቹ ጋር ወደ ኤርትራ ተወስደዋል” ሲል ሌላ መረጃ ያቀርባል። በአካባቢው ያለው ሁኔታ፤ እንዲህ አይነት መረጃዎችን ከባለስልጣናትም ሆነ ከገለልተኛ አካል ለማጣራት የማያስችል መሆኑ በትክክል የሆነውን ነገር ለማወቅ አዳጋች አዳርጎታል። ፋብሪካውን ካለፍን ከደቂቃዎች በኋላ አዲግራት ገባን።

የመጨረሻውን ክፍል ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2021/2514/

የዚህን ልዩ ዘገባ ቀደምት ክፍሎች ለማንበብ ተከታዩቹን ሊንኮች ይጫኑ፦
ክፍል አንድ – https://ethiopiainsider.com/2021/2374/

ክፍል ሁለት –  https://ethiopiainsider.com/2021/2398/