ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ያለውንና በቅርቡ መልሳ የወሰደችውን መሬት እንደማትለቅ አስታወቀች።

የሱዳኑ ሱና ከፍተኛ የመከላከያ ኃላፊን ጠቅሶ፤ ሱዳን በምዕራባዊ ድንበሯ ላይ የሚገኘውንና ከኢትዮጵያ ጋር ያወዛግባት የነበረውን መሬት እንደማትመልስ ዘግቧል።

ሱዳን ከአልፋሻጋ ይዞታ ቅንጣት ታህል እንደማትሰጥ ሜጀር ጀነራል ሀይደር አልቲራፊ አረጋግጠዋል። ለወታደራዊ ኃይል ምልመላ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋልይላል የመንግሥታዊው ሱና ዘገባ።

ኢትዮጵያ በበኩሏ አለመግባባቱን በድርድር ለመፍታት ሱዳን የያዘችውን መሬት እንድትለቅ እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች።

የሱዳኑ ጄነራል ግን አልገዳሪፍ ውስጥ ፋላታ ከተባለው ጎሳ ድጋፍ በተቀበሉበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ሁሉም ዜጎች ልጆቻቸው ወታደራዊ ኃይሉን ተቀላቅለው የአገራቸውን ዳር ድንበርና ክብር እንዲያስጠብቁ እንዲያነሳሱ እጠይቃለሁብለዋል።

የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ድንበር ላይ ያለውን ቀጠና ለማሳደግ የመንገድና የድልድይ ግንባታ ላይ እንደተሰማራ ተናግረዋል። በቀጠናው የአገልግሎት ዘርፍ በመገንባት እንቅስቃሴን ምቹ ለማድረግም እየሠሩ ነውሲሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ፤ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ሱዳን ወደቀደመ ይዞታዋ ካልተመለሰች ለድርድር መቀመጥ እንደማይቻል ተናግረዋል።

ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ እንድትጠብቅም ሆነ መሬት እንድትይዝ የተደረሰ ስምምነት እንደሌለም ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና መናገራቸው ይታወሳል።

ሱዳን የያዘችውን መሬት እንድትለቅ ኢትዮጵያ በቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧንና ይህ ከተሳካ ሁለቱ አገራት በዋናነትም ችግራቸውን ተነጋግረው መፍታት እንደሚችሉም አስረድተዋል።

ሱዳን እና ኢትዮጵያን የሚያወዛግበው አልፋሽጋ የግብርና ሥራ እየተከናወነበት የሚገኝ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ጥቅምት ሱዳን አካባቢውን ሙሉ በሙሉ እንደምትቆጣጠር አስታውቃለች።

ይህም ከኢትዮጵያ ጋር የሚያወዛግባትንና በኢትዮጵያ ሚሊሻ ተይዞ የነበረውን የድንበር አካባባቢ ይጠቀልላል።

ቢቢሲ