ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክInternational Ethiopians Solidarity Foru

                                                  የጋራ ትግል ጥሪ

ጥር 22 ቀን 2013ዓም(30-01-2021)

እመብዛም ሞኝነት ለበግም አልበጃት፣

አሥራ ሁለት ሆና አንድ ተኩላ ፈጃት።

 ይህ ከላይ የምናነበው ምሳሌ መሰል የግጥም መልእክት በፍርሃትና በየዋህነት የተነሳ ብዙ ሆነው የመጣባቸውን ጠላት ከመቋቋምና ከመትረፍ ይልቅ በሆነ ባልሆነው ወይም በግል ጥቅም የተነሳ ተከፋፍለው እራሳቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡትን የዋሆች የሚያሳይ ምሳሌ ነው።

እንደሚታወቀው ላለፉት ብዙ ዓመታት በአገራችንና በሕዝቡ ላይ እዬተፈራረቁ ሥልጣን ላይ በወጡ ሕገወጥ አምባገነኖች ተመሳሳይ የግፍ በደል ሲደርስ ኖሯል።ያንን የግፍ ስርዓትና በደል ለማሶገድ ሕዝቡ ያላሰለሰ ትግል አድርጓል፣ መስዋእትነትም ከፍሏል።በዬጊዜው በስሙ የተቋቋሙት ቡድኖችና የፖለቲካ ድርጅቶችም ምንም እንኳን ባይሳካላቸውም ብዙ ትግል አድርገዋል፣ብዙም መሪዎቻቸውንና አባላቱን ለከፋ ስቃይና እልቂት ዳርገዋል።የዚህ ሁሉ የትግል ውጤት ሲታዬ ግን ከድጡ ወደማጡ የገቡበት እንጂ ወደ ሚፈልጉበት ውጤት አላደረሳቸውም ።ለምን ቢባል የሚታገሉት ሃይል ከነሱ የበለጠ እውቀትና የሕዝብ ድጋፍ ኖሮት ሳይሆን በዓላማው የጠናና ሃይሉን አሰባስቦ የቆመ በመሆኑና የሚታገሉት ሃይሎች በአንጻሩ በስም ብቻ ሳይሆን በዓላማና በድርጅታዊ አወቃቀራቸው የተለያዩ፣ብሎም እርስ በርሳቸው የሚጠላለፉና በጠላትነት የሚተያዬ ሆነው ለሚታገሉት ሃይል የስውር ዱላ አቀባይ በመሆናቸው ነው።እስከትናንትናውና ዛሬም ቀን በዚሁ ድክመት ላይ የተሰለፉ ሆነው ለተመሳሳይ ጥቃት ተጋልጠው ይገኛሉ።

ታዲያ ያለው መፍትሔ ምንድን ነው?ካለፈው ውድቀትና ትምህርት ወስዶ የጋራ ጠላትን በጋራ ለማሶገድ የሚያስችል ቁመና መፍጠር ነው።ሌላው ቢቀር ለተወሰነው የጋራ ዓላማ በግንባር መሰለፍ ነው።የፖለቲካ ዓላማ ከዚያ በዃላ የሚታሰብና የሚሠራበት ይሆናል።አሁን አገር ወደ መፍረሱ ሕዝብም እርስ በርሱ ወደ መጫረሱ ጠርዝ ላይ እንዳለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በተግባርም የሚታይ መሆኑ የሚካድ አይደለም።ገዢው መንግሥት የያዘውን የቡድንና የጎሳ ፖለቲካና ሥልጣን ለማራዘም ምርጫ  ውስጥ ሕዝቡ እንዲገባ የሚያደረርገውን ግርግር ተቀብሎ አብሮ ከመንጎድ ይልቅ ለምርጫ የሚያበቃ ሁኔታ መኖሩን ማረጋገጥ ያሻል።በተያዘው መንግዽ ምርጫ ይካሄድ ቢባል ውጤቱ በዘረኝነት ላይ የተነደፈውን አገር አጥፊ ሕገመንግሥት ተሸክሞ ቀውስና የባለተረኞች ወንጀል በቀጣይነት እንዲኖር ሕጋዊ ፈቃድ መስጠት ይሆናል፤ያም ብቻ ሳይሆን አገርንና እራስን ለአደጋ አሳልፎ ለመስጠት ከጭዳ ሰልፍ ውስጥ ፈቃደኛ ሆኖ መግባት ነው።

ሁሉም የኛ” የሚለው ይሉኝታ ቢስ ቡድን ሁሉንም ነገር ለመሰልቀጥ አሰፍስፎ በሚገኝበት፣ብሎም በተግባር በሚያሳይበት  በአሁኑ ጊዜ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተባለው የፖለቲካ ድርጅት የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ሲዘጋጅ በባለሥልጣናቱ መታገዱ ትክክል አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሕግ የሚፈረጅ የመብት ጥሰት ነው።ይህንን የመብት ጥሰትና ሌላውንም በአገር ላይ ያንዣበበ አደጋ በህብረት መከላከል ተገቢ ነው።በሆነ ባልሆነው ድርጅታዊ፣ቡድናዊና የግለሰቦች ጥቅምና ፍላጎት የተነሳ የአገርና የሕዝብ መብት መዘንጋት የለበትም። በተያዘው መንገድ መቀጠል ማለት ከላይ በበጎቹ ላይ የደረሰውን ዪ,ተኩላ  ጥቃት በጸጋ ፈቅዶ መቀበልን ይመስላል።ለራስም አይጠቅምም።

የዚህ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ አስፈላጊነትም ለዚህ አይነቱ የጋራ ጉዳይ አብረው እንዲቆሙ ለማድረግ ነው።ስለሆነም በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የተጠራውን የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ በማገዝ፣በማስተባበር ሁሉም ተቃዋሚ ነኝ ባይ  በመንግሥት ተብዬው ተረኛ ቡድን የተዘረጋውን የእገዳ ሰንሰለት ጥሶ እንዲወጣ ጥሪ ያደርጋል።መብትን በትግል እንጂ በልመናና በፍርሃት ሊያስከብሩ እንደማይቻል ካለፈው ያገራችንና ከሌላውም አገር ሕዝብ የትግል ታሪክ መማር ይገባል።የሰላማዊ ሰልፉ ምክንያት የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አገር አቀፍና ሁሉንም ዜጋ የሚመለከት ጉዳይ ነው።በተለይም ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ነን የሚሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ማንሳትና መታገል የሚገባቸውን ጥያቄ ያነሳ በመሆኑ እነሱም የትግሉ አካል መሆን አለባቸው፤ከዳር ቆመው ሊመለከቱ አይገባም። ከምርጫው በፊት ያልተነሱ ጥያቄዎችንም ጨምረው ለምሳሌም የሕገመንግሥቱ መቀዬር አስፈላጊነት፣ሰላምና መረጋጋት መስፈን፣በሁሉም ያገሪቱ ምድር ተዘዋውሮ ቅስቀሳ የማድረግ መብት መረጋገጥ እንዳለበት፣ግድያና ዘረፋ የፈጸሙ ወንጀለኞችና  ያስፈጸሙ የመንግሥት አካላት  ለፍርድ እንዲቀርቡ ዜጋ በሰላም ወጥቶ መግባቱ እንዲረጋገጥ፣ ከአንድ ዓመት በላይ፣በወንጀለኞች ታፍነው አድራሻቸውም ሆነ መኖራቸው ያልተረጋገጠው ንጹሃን ወጣት ተማሪዎች ጉዳይ መልስ ማግኘቱ ቅድሚያ እንዲሰጠው ማድረጉ የትግሉን ይዘትና ፍትሃዊነት ሊያጠናክሩት ይችላሉ።በተጨማሪም አገራችን በውጭ ወራሪ ሃይሎችና በአገር ውስጥ ጸረ ኢትዮጵያ በሆኑ ተባባሪዎች ደባ ፈተና ውስጥ ባለችበት ወቅት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊቆሙ ይገባል።የሚወስዱት አቋም ለማንነታቸውና ለምንስ ዓላማ እንደቆሙ የሚፈተሹበት ነው። የውጭ ወራሪ ሃይልም የሚደፍረው አገር ወዳዱ በአንድ ላይ ሆኖ አለመቆሙን ሲያይ ነው።የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ለመደምሰስ የአገር ወዳዱ በአንድነት መቆም ወሳኝ ነው።ባለቤት ያቀለለውን ባለዕዳ አይቀበለውም እንዲሉ!

የተለያዩት ተቃዋሚ አገር ወዳድ ድርጅቶችና የማህበራዊ ስብስቦች ለዚህ የጋራ ትግላቸው የሚያስተባብራቸውን አካል መፍጠር ነገ የማይሉት የዛሬ ግዴታቸው ነው።ለዚያም መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ያዘጋጀውን የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪን ተከትለው አብረው ሊቆሙ ይገባል።

በአንድነት ፣ለአንድነት!!

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ