February 1, 2021 – Konjit Sitotaw
የአዲስ አበባ ህዝብ ትዕግስቱ ሲያበቃ የሚያቆመው ሀይል እንደሌለ በተደጋጋሚ ታይቷል ! – አቶ ክቡር ገናከሲራራ ጋዜጣ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ የተወሰደ…

” ኢዜማን ከሌሎች በተለየ የመረጥኩበት የራሴ የሆኑ በርካታ ምክንያቶች አሉኝ። ፓርቲውን ተቀላቅዬ ከነሱ ጋር አንድ ላይ እንድሰራ ቀደም ብሎ ጥያቄ ያቀረበልኝ ኢዜማ ነው። ጥያቄውን ካቀረቡልኝ ቆይቷል። በሰአቱ ብዙም እርግጠኛ ስላልነበርኩ ፓርቲውን አልተቀላቀልኩም ነበር። ነገር ግን የፓርቲውን ፕሮግራምና ድርጅታዊ ሁኔታ ወስጄ ከመረመርኩ በኋላ ኢዜማን ብቀላቀል ለሃገሬና ለወገኔ በጎ አስተዋፅኦ እንደማደርግ በማመን ጥያቄውን ተቀብዬዋለሁ። “…” አዲሳባ የአዲሳባ ህዝብ ናት። ከዚህ የተለየ ነገር የለም። የኦሮሚያ ክልል አዲሳባን በሁሉም አቅጣጫዎች ቢያዋስናትም የኦሮምያ ክልል አካል አይደለችም። አዲሳባ የአዲሳበቤዎች ነች። ከተማዋ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሚያስተዳድራት የሚኖርባት ልጆቹን የሚያሳድግባት ጤናውን የሚጠብቅባት ከተማ ነች እንጂ አሁን እንደሚባለው አንዱ የኔ ብቻ ናት የሚለው ነገር ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው። ይሄ የኔ ብቻ ሃሳብ ሳይሆን የከተማዋም ነዋሪ ሃሳብ ነው። በሁሉም ኢትዮጵያዊ ድካምና ጥረት የተገነባችውን ከተማ በብቸኝነት ለመቀራመት በዚህ ደረጃ መጠላለፍ አሳፋሪ ነው። “…” የአዲሳባ ህዝብ ሲበዛ ትእግስተኛ ነው። ትእግስቱ ሲበዛ የሆነ ቦታ ላይ የሚያበቃ ይመስለኛል። የአዲሳባ ህዝብ ዝም ስላለ ህዝቡ ፈርቶ የሌሎችን ባለቤትነት ተቀብሎ ይቀጥላል ማለት አይደለም። የአዲሳባን ህዝብ ትግስትና ዝምታ በዚህ መልኩ የሚረዱ ሰዎች በጣም ተሳስተዋል ። ሁሉም የየብሄሩንና ክልሉን ጉዳይ ይዞ እርስበርሱ ሲጠላለፍ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ አርቆ ከማሰብ የሚመነጭ ዝምታና ትእግስት አለ። እሱ ግን ወሰን አለው። የአዲሳባ ህዝብ ትግስቱ ሲያልቅ የሚያቆመው እንደሌለ በተደጋጋሚ ታይቷል። አዲሳበቤ ሲወስን ደግሞ ያውቅበታል። “
