February 2, 2021

EBC : የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ 31/3/ ላይ ማሻሻያ አድርጓል።የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አቡ በክሪ የውሳኔ ሀሳብ ሪፖርቱን አቅርበዋል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2013 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ አንቀፅ 31/3 የግል ተወዳዳሪዎች እጩዎች በሕጉ መሠረት መሰብሰብ ከነበረበት ከ5 ሺህ የማያንስ ፊርማ በ50 በመቶ ቀንሶ ከ2 ሺ 500 ያላነሰ እንዲሆን፤ ለአካል ጉዳተኞች እጩዎች ደግሞ ከ3 ሺህ የማያንስ የሚለው ከ1 ሺህ 500 የማያንስ እንዲሆን የውሳኔ ሀሳብ ቀርቦ ፀድቋል።

እንዲሁም አንቀፅ 32/2 ደግሞ የፓርቲዎች እጩዎች በሕጉ መሠረት መሰብሰብ የነበረበት የድጋፍ ፊርማ ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ብቻ ተፈፃሚ እንዳይሆን እንዲታገድ መደረጉ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የሚያግዝ ሆኖ በመገኙቱ ይህ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከፀደቀበት ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የፀና እንደሚሆን የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጊዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን ውሳኔ ሀሳብ ሪፖርት ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።

አንቀፅ፦ 32(2) የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ እንዳለባቸው ይደነግጋል፤ ሆኖም ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ብቻ ተግባራዊ እንዳይሆን ለማገድ የተወሰነበት ምክንያት፦

1.በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ የወረቀት ልውውጥ እና ንክኪን በተቻለ መጠን መቀነስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣

2.ባለው የተጣበበ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ የተነሳ ከፓርቲዎች ፊርማዎች ለማሰባሰብ በቂ ጊዜ ስለማይኖራቸው በቦርዱ በኩል ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ስለሚሆን ለማጣራት ስለሚቸግረው፤

3. በፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ከፍተኛ ቅሬታ የሚቀርብበት በመሆኑ እንደሆነ ተብራርቷል።