ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ!
የሴራ ፖለቲካ ምዕራፍ የሚዘጋበት፣ የጥላቻና የፍረጃ ፖለቲካ ላንቃ የሚዘጋበት ጊዜው አሁን ነው ! – አብን

ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በአገራችን ውስጥ እስካሁን የተካደው ኢትዬጵያዊ ዜግነት ተገቢውን እውቅና እንዲያገኝ፣ ዜግነት የፖለቲካችን ማዕከል እንዲሆን የሚያስችል መሰረታዊ የትርክት ለውጥና የመዋቅር ክለሳ እንዲደረግ በርካታ ጥሪዎችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ለአገራችችን የፖለቲካ ምስቅልቅል(crisis) መነሻ የጥላቻ ትርክት በሕገ-መንግስትና በመዋቅሮች መስረፅ ምክንያት መሆናቸውን በመገንዘብ ሕዝባችን ከባድ መስዋእትነትን የጠየቀ የለውጥ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም ቀላል የማይባሉ እመርታዎችን ያስመዘገበ ቢሆንም በዋናነት የአፋኙ ስርዓት አካልና ወራሽ የሆነ ስብስብ የሕዝባችንን ቅን ልቦና ባጎደፈ መልኩ የፅንፈኝነት ባህሪውን ለጊዜው ደብቆና ስሙን ብቻ ቀይሮ የሕዝባችንን የለውጥ ሂደት አግቶት ይገኛል።
የአማራ ሕዝብና አብን በትሕነግ ላይ የነበረው አቋም የተፈተሸ፣ የጠራና የነጠረ ስለመሆኑ አስረጅ አያስፈልገውም። አብን ከሁለት አመታት በፊት ትሕነግ ሽብርተኛ ድርጅት መሆኑን በመጥቀስ ከሰላማዊ የፖለቲካ ፖርቲዎች ዝርዝር እንዲሰረዝና ጉዳዩ በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ እንዲታይ ማሳሰቡ ይታወሳል። በወቅቱ መንግስት ከትሕነግ ጋር አብሮ በአንድ ጥምረት ውስጥ ሆኖ የሚሰራበት ነበር። አብዛኛው የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች በአብን መግለጫ ቢያንስ ተደናግጠው እንደነበር የሚታወስ ኃቅ ነው።–አብን የአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ ንቅናቄ አካል እንደመሆኑ መጠን ዝቅተኛው የፖለቲካ ስምሪቱ አገራችን በፅንፈኛ ኃይሎች ቅንጅት እጅ ዳግም እንዳትወድቅ መከላከል ነው። የኮሮና (COVID-19) ወረርሽኝ ስጋትን ተከትሎ በአገራዊ የምርጫ መርኃ ግብር ላይ በታየው የፖለቲካ ችግር ወቅት የወሰድነው አቋም አብን ኢትዬጵያን በተመለከተ ላለው የማያወላዳ አቋም አይነተኛ ጠቋሚ መሆኑ አያከራክርም።
ድርጅታችን አብን የኢትዬጵያ ፖለቲካ ችግር ሊፈታ የሚችለው መሰረታዊ ለውጦችን በማድረግ እንጅ በስምና በቅብ ለውጥ ሊሆን እንደማይችል በመረዳት አገራችን በሽግግር መንግስት ምስረታ ሳይሆን በሽግግር ጊዜ ምዕራፍ ማለፍ እንዳለባት ማሳወቁ ይታወሳል። በተያያዘ ሁኔታ በሽግግር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ እልባት ማስገኘት የሚችሉ አንኳር የለውጥ ተግባራት መፈፀም እንዳለባቸው ገልፆ ጥሪ ማስተላለፉም ይታወሳል። ነገር ግን በጥሬ ስልጣን ግብግብና በጥላቻ ባሕል የተቃኘው የአገራችን አጠቃላይ የፖለቲካ ስምሪት ዘላቂ ተግዳሮት ሆኖ በመቀጠሉ ተፈላጊው ለውጥ እውን ለመሆን ካለመቻሉም በላይ በሕዝባችን ላይ ተከታታይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት ጥቃቶች ተፈፅመዋል። የዜሮ ድምር የፖለቲካ ዘይቤ የቀጠለ ሲሆን በአገራዊ መግባባትና ትብበር መሰራት ያለባቸውን ጉዳዬች በፉክክርና በጥላቻ ለመፍታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በመቀጠላቸው ምክንያት የህዝባችን ትግል ገና ተቀናጅቶና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገንዝበናል።
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን እና የኢትዮጵያዊነትን ትሩፋቶች በብቸኝነት ለመበየንና ለማከፋፈል የቋመጡ ፅንፈኛ መንግስታዊ አካላት ሀገራችንን ተፈትሾ በወደቀው የሴራ ፖለቲካቸው አዙሪት ውስጥ ለማቆየት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። በርካታው የሀገራችን ክፍል የደህንነት ስጋት ያንዣበበት ሲሆን የህዝብ በሰላም የመንቀሳቀስም ይሁን በህይወት የመኖር መብት በመደበኛነት አደጋ ውስጥ ይገኛል።አብን በዚህ አመት በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን የጥላቻና የሴራ ፖለቲካ ግንባር ቀደም ተጠቂ ድርጅት በሆነበት አግባብ ነው። የምርጫ ትርጉም በአንድ ቀን ውስጥ ተከፍቶ በሚዘጋ ሳጥን ውስጥ በሚጨመሩ ካርዶች የታጠረ እንዳልሆነ ይገነዘባል። በሀገራችን ውስጥ ያለው የቅድመምርጫ መደላድል ያለበት ሁኔታ ለህዝባችን የተሰወረ አይደለም። በተለይ የአማራን ህዝብ ማገት የፖለቲካ ስልት ሆኖ የቀጠለ እውነታ ነው። አብን የአማራ ህዝብ ሀቀኛና የማያወላዳ፣ እንዲሁም የአማራ ህዝብ ፀረ-ጭቆናና ፀረ-ዘረኝነት የትግል እንቅስቃሴ በቀጥታ የወለደው ድርጅት በመሆኑ አማራን የሚፈርጁና የሚያጠቁ ፅንፈኞች ዓይናቸውን ለአፍታ እንኳን ዘወር እንደማያደርጉለት ይታወቃል።
ከአማራ ክልል ውጭ ባሉት በተለይም በኦሮሚያና በቤኒሻንጎል ክልል ውስጥ ባሉት የአብን መዋቅሮችና አመራሮች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈፀሙ ቆይተዋል። ጥቃቶቹ አሁንም ቀጥለዋል። በተለይም የክልሎቹ ባለስልጣናት በሆኑ የብልፅግና ፖርቲ አባላት የሚፈፀሙ ችግሮች መሆናቸውን መነሻ በማድረግ ከፖርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ ባለመሳካቱ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻ አቅርቦ በምርመራ ላይ ይገኛል።
ጉዳዬቹ በዚህ አግባብ በሚገኙነት ሁኔታ ጭምር “የኦሮሞ ብልፅግና” ከፍተኛ አመራሮች በማህበራዊ ድረ ገፅ በአብን፣ በአመራሮቻችን፣ አባላቶቻችን፣ ደጋፊዎቻችንና ባጠቃላይ በአማራ ህዝብ ድርጅቶችና አመራሮች ላይ የሀሰት፣ አፍራሽና የጥቃት ጥሪዎችን በተደጋጋሚ እያስተላለፉ ይገኛሉ። የብልፅግና ፖርቲ እንደተቋም በሚፈፀሙ ጥሰቶች ላይ ምንም አይነት ተጨባጭ እርምት ለማድረግ ባለመፈለግ በቀጥታ የተቀበላቸውና የአማራን ህዝብ በተመለከተ ያለውን አቋም በምግባር፣ በድርጊትና በቸልታ አረጋግጧል።–በዛሬው እለት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተደረጉ ሰልፎች በዋናነት አብንን የሚያጠለሹና የሚያወግዙ እኖዲሁም በህዝባችን ላይ ቀጣይ ስጋትን የጋረጡ ድምፆች ከፍ ብለው ሲስተጋቡ ተሰምተዋል። አብንን “ከኦነግ ሸኔ” ጋር የሚያመሳስሉ መፍክሮች ተሰምተዋል።
ስለሆነም:-
1/ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ገደብ የለሽ የፖለቲካ ነውረኝነትና የዘረኝነት እንቅስቃሴ ለመቃወም በባልደራስ ተጠርቶ የነበረውን ህዝባዊ ሰልፍ በማንአለብኝነት የከለከለ መንግስት ለፖርቲ ፍጆታ ሲሆን ሰልፍ መጥራቱና መፍቀዱ፣
2/ በሰልፉ ላይ የጥላቻና የጥቃት ጥሪዎችን ሲመሩ የነበሩት በስምና በኋላፊነት የሚታወቁ የመንግስትና የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች መሆናቸው፣
3/ በዛሬው ሰልፍ ላይ ጎልተው የተሰሙት ድምፆች የክልሉ አመራሮች በማህበራዊ ድረገፅ ሲፅፏቸው የነበሩ ሀሳቦች ቀጥተኛ ግልባጭ መሆናቸው፣
4/ በዚህም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባጠቃላይ ያለውን የፖለቲካ አፈና ወደተሟላ እርከን ለማሸጋገር በማሰብ አብን በክልሉ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታትና በክልሉ የሚኖረውን የአማራ ህዝብና ሀገር ወዳድ ኢትዬጵያዊ በጭቆና ቀንበር ስር ለማቆየት አላማ ያነገበ ተግባር መሆኑ፣
5/ በተለይም በዛሬው ሰልፍ ላይ በአማራ ህዝብ ላይ በተደጋጋሚ የዘር ፍጅት ለመፈፀም ፅንፈኛ ሀይሎች መንደርደሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት “ነፍጠኛ” የሚለው ቃል በሰፊው ሲገለፅ የነበረና በግልፅም “ነፍጠኛ ይውጣ” የሚል ሀሳብ ሲሰማ የነበረ መሆኑ፣
6/ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሀላፊነት የጎደላቸው ፅንፈኛ አመራሮች በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት ሽፋን በመስጠትና በቀጥታ በመሳተፍ እንደሚያስፈፅሙ የተረጋገጠ ጉዳይ ሆኖ እያለ በታየው ደረጃ የተላለፈውን የጥላቻና የጥቃት ጥሪ የመንግስት ሚዲያዎች መዘገባቸውና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴርም እርምት መስጠት እየተገባቸው ቡራኬ መስጠታቸው እጅግ አሳዛኝ የሆነና በቀጣዩ የሀገራችን የፖለቲካ ሂደት ላይም ከፍተኛ ስጋትን እንደሚፈጥር መረዳት ይቻላል።
አጠቃላይ የሀገራችንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ የተለየ ፖለቲካዊ እይታ የማስተናገድ ዝንባሌና ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ በመንግስት በኩል እየታየ ያለው አቋምና አፍራሽ እንቅስቃሴ ባስቸኳይ እንዲቆም እየጠየቅን የአብን የብሄራዊ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጉዳዬን በቀጥታ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድና በግልባጭ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ አሳውቋል።
በመጨረሻም መላው ኢትዮጵያውያን በተለይም የአማራ ሕዝብ ዛሬ የተስተጋባው የጥላቻና ዘር ፍጅት ቅስቀሳ በውጤት ደረጃ አገርና ሕዝብን ለኅልውና አደጋ የሚጥል መሆኑን በመረዳት የተፈፀመውን አስነዋሪ ድርጊት በጽኑ እንዲያወግዝና አብን ከሚያደርጋቸው የፍትኅ፣ እኩልነትና ነፃነት ትግሎች ጎን እንዲሰለፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የሴራ ፖለቲካ ምዕራፍ የሚዘጋበት፣ የጥላቻና የፍረጃ ፖለቲካ ላንቃ የሚዘጋበት ጊዜው አሁን ነው!
ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ!