ፓርላማው የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲቀር ከምርጫ ቦርድ የቀረበለትን ጥያቄ አፀደቀ

ፓርላማው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበለትን ጥያቄ በሙሉ ድምፅ ሲያፀድቅ

3 February 2021

ሲሳይ ሳህሉ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪው ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ፣ ዕጩዎች ማቅረብ ይጠበቅባቸው የነበረውን የድጋፍ ፊርማ እንዲቀር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበለትን ጥያቄ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፡፡

በ2011 ዓ.ም. በወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ  አንቀጽ 32 መሠረት ድርጅትን፣ ፓርቲን፣ ግንባርን ወይም ቅንጅትን የሚወክሉ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ 2,000 እና ለክልል የሚወዳዳሩ 1,000 የድጋፍ ፊርማ በሚወዳደሩበት የምርጫ ክልል ከሚኖሩ መራጮች እንዲያመጡ ይገደዳሉ፡፡

በተመሳሳይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎች 1,500 የድጋፍ ፊርማዎችን፣ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ የአካል ጉዳተኛ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች 750 ፊርማዎችን ማሰባሰብ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 31 የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች በሚወዳደሩበት አካባቢ አስተዳደር የተረጋገጠ ዕድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውና የመምረጥ መብታቸው በሕግ፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ወይም በአዕምሮ ሕመም ምክንያት ካልተገደበ የምርጫ ክልሉ ነዋሪዎች ውስጥ ከአምስት ሺሕ የማያንስ የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡

እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ የሆነ የግል ዕጩ ተወዳዳሪ ማቅረብ ያለበት የድጋፍ ፊርማ ብዛት ከሦስት ሺሕ የማያንስ እንደሆነ በአዋጁ ተመልክቷል፡፡

ይሁን እንጂ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የወረቀት ንክኪን በተቻለ መጠን ለመቀነስና የሚመጡ የድጋፍ ፊርማዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ካለው የጊዜ መጣበብ ጋር በተገናኘ አዳጋች ስለሚሆንና ችግሩ በፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ከፍተኛ ቅሬታ እንደሚቀርብበት በመጥቀስ፣ ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ማሻሻያ እንዲያደርግበት ከአንድ ወር በፊት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡

ማክሰኞ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው ፓርላማው፣ የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች በሕጉ መሠረት መሰብሰብ የነበረባቸውን ከአምስት ሺሕ የማያንስ የድጋፍ ፊርማ በ50 በመቶ ቀንሶ 2,500 አንዲሆን አፀድቋል፡፡

እንዲሁም ለአካል ጉዳተኛ ዕጩዎች 3,000 የነበረውን ወደ 1,500 እንዲቀንስ በአዋጁ አንቀጽ 32 እንደተገለጸው፣ በፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች መሰብሰብ የነበረበት የድጋፍ ፊርማ ለቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ላይ ብቻ ተፈጻሚ እንዳይሆን እንዲታገድ የሚለውን ጥያቄ ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡