February 4, 2021

በተለያዩ አካባቢዎች ቢሮዎቻችን ተዘግተውብናል የሚል ክስ ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቢሮዎቹን አድራሻ መግለጽ ባለመቻላቸው ችግሩን ለመፍታት አስቸጋሪ እንደሆነ የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናገሩ።

“ምርጫ ቦርድን ይጠይቁ” በሚል ርእስ የማኅበራዊ ሚዲያ በተዘጋጀው የተሳትፎ መድረክ ላይ ለተጠየቁ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት ዋና ሰብሳቢዋ፣ ቢሯችን ተዘጋብን ያሉ ፓርቲዎችን ጉዳይ በተመለከተ ምርጫ ቦርድ ችግሩን ለመፍታት ጉዳዩን ለመንግሥት በማቅረብ እንደሄደበት ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ቢሮዎች አድራሻቸው ተገልጾ እንዳልመጣ እና አድራሻቸውን እንዲገልጹ ለፓርቲዎቹ ጥያቄ ቢቀርብም ብዙም ተነሳሽነት እና የማሟላት ሁኔታ እንደሌለ ተናግረዋል።

ቢሮዎችን ዘግቷል የተባለው አካል አልዘጋሁም እያለ በመሆኑ እና ቢሮዬ ተዘግቶብኛል የሚለው አካልም የቢሮውን አድራሻ በአግባቡ መጠቆም ባለመቻሉ ምርጫ ቦርድ ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት ሊሳካ አልቻለም ብለዋል።

https://youtu.be/brPZES49UKA

በተለይ ኦነግ እና ኦፌኮ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ በርካታ ቢሮዎቻቸው እንደተዘጉ ቢገልጹም የቢሮዎቻቸውን አድራሻ እንዲገልጹ ተጠይቀው አለማቅረባቸውን፣ ሌሎች ፓርቲዎችም በተመሣሣይ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

እንደዚህ ዓይንት ችግርን ከስር መሠረቱ ለመፍታት የተደረገውን ጥረት በተመለከተ ደግሞ፣ ወደ ፊት በየዞኑ አደረጃጀቶች ስለሚኖሩ ፓርቲዎችም ተወካዮቻቸውን እየላኩ ወደ ታች ተወርዶ ችግሩን በቀጥታ ለማየት ምቹ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።