February 5, 2021 – Konjit Sitotaw
የግድቡን ድርድር ከአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት ማዕቀፍ ለማስወጣት የሚደረገው የሴራ ዲፕሎማሲ ማክሸፍ ይገባል – ምሁራን
(ኤፍ ቢ ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገውን ድርድር ከአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት ማዕቀፍ ውስጥ ለማስወጣት የሚደረገውን የካይሮ የሴራ ዲፕሎማሲ ለማክሸፍ ከወዲሁ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ በውሃ ዲፕሎማሲ ላይ ጥናት ያካሄዱ የባህርዳር እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ ኢትዮጵያን ይህን አካሄድ ለማክሸፍ በአፍሪካ ህብረት ትልቅ ተሰሚነት ካላቸው ሌሎች ሀገራት እና ከተፋሰሱ አባል ሀገራት ጋር ያላትን የግንኙነት መስመር ማጠናከር ይገባታልም ብለዋል፡፡
በዘርፉ ላይ ጥናት ከሰሩ የባህርዳር እና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቆይታ አድርጓል።
ዶክተር ውብእግዜር ፈረደ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ናቸው።
የሶስተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጥናታቸውን የሰሩት በናይል ወንዝ በተለይም በምስራቅ ናይል ተፋሰስ ሀገራት ያለውን የውሃ ዲፕሎማሲ ፈተናዎችን ኢትዮጵያን እንደማሳያ በመውሰድ ነው፤ የጥናታቸው ርዕስም (Ethiopia challenging the foundation of hydro-hegemony in the eastern Nile basin) ይላል።
ዶክተር ወብእግዜር ቅድሚያ በቀጣይ ወራት በሚካሄዱ የግድቡ ድርድር ዙሪያ ተገማች ሁነቶችን ሲያብራሩ ግብፅ ከአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ጋር በማሴር ድርድሩን አሰልቺ በማድረግ ከአፍሪካ ህብረት የማስወጣት አካሄድ ልትከተል ትችላለች የሚል አስተያየት አላቸው።
ይህን እቅዷን ለማስተገበር ደግሞ በደጋፊዋ የአረብ ሊግ እና አረብ አባል ሀገራት ድጋፍ በማስተባበር የአዲሱን የአሜሪካ አስተዳደርም በአረብ እስራኤል ፖለቲካ የማሳሳት ስልት ልትከተል ትችላለች ነው የሚሉት።
ዶክተር ውብግእዜር ፈረደ የካይሮ ሰዎች ዛሬም እየተጓዙበት ያለው መንገድ መዳረሻ ድርድሩን ከአፍሪካ ህብረት የማስወጣት አካሄድ ነው ይላሉ።
ባለፈው ነሃሴ 20 2020 ላይ በአሜሪካው ፍሎሪዳ ዓለም አቀፍ ዪኒቨርሲቲ (the distribution of conflict in the blue Nile river in the case of Ethiopia, Sudan and Egypt) በሚል ጥናታቸውን ያቀረቡት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰሩ ዶክተር መብራቱ አለሙ ፤በቀጣይ የአፍሪካ ህብረትን የወቅቱ ሊቀመንበርነትን ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት በሚረከቡት የዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ላይ ስጋት አላቸው።
ዶክተር መብራቱ እንደሚያስረዱት ከሆነ ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት አሸማጋይነት አፍሪካዊ አባትነት የታየበት ነበር ብለዋል፡፡
በቀጣይ ስልጣን የሚረከቡት ሰው ግን ከዚያ በተቃራኒው ሊጓዙ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።
የስጋታቸው መነሻ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግብፅ ከዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ጋር የሰራቸው ስራ እና የፈጠረቸው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲሁም የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ከአሁን በፊት በግድቡ ዙሪያ የሰጡት የተዘናፈ አስተያየትን ነው ብለዋል፡፡
በናይል ጂዖ ፖለቲካ ላይ የሰሩትን ጥናት ወደ መፅሃፍነት ቀይረው እያሳተሙት የሚገኙት የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር መብራቱ መለስ እንደሚናገሩት፤ የናይል ፖለቲካ በቀጣይም የስጋት እና የግጭት መነሻ መሆኑ አይቀሬ ነው ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከወዲሁ ዘርፈ ብዙ ዝግጅት ማድረግ ይጋባታል ሲሉም አክለዋል፡፡
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ውብእግዜር ፈረደ እንደሚሉት ኢትዮጵያ የካይሮን እና የካርቱምን ካርታ በብልጠት ለማሸነፍ መከተል ያለባት አዳዲስ ስትራቴጂ አለ።
እነዚህ የዲፕሎማሲ አካሄዶች ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ውስጥ እንዲቆይ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
ለመሆኑ እነዚህ አዋጭ የውሃ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂዎች ምንድን ናቸው ።
ዶክተር ውብእግዜር ፈረደ ቀዳሚ ያደረጉት ለተወሰነ ጊዜ ጣል አድርገነው የቆየነው የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ዳግም እንዲያንሰራራ መስራት ቀዳሚ ሲያደርጉት፤ የግድቡን ዲፕሎማሲ ወደ ጎረቤት ሀገራት እና አጠቃላይ ወደ ናይል ዲፕሎማሲ መለወጥ ጊዜ መግዣ ወሳኝ የዲፕሎማሲ ስልቶች ናቸው ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚናገሩት ከሆነ ኢትዮጵያ በፍጥነት የዚህ ዓመት የውሃ ሙሌት እንዲሳካት ለማድረግ ከወዲሁ የሚጠበቁ የቤት ስራዎችን በፍጥነት መከወን ይገባታል ሲሉ አሳስበዋል።
ዶክተር መብራቱ አለሙ እንደሚሉት ደግሞ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን አካባቢያቸውን አሁን ላይ በጥንቃቄ እየተመለከቱ መራመድ ይገባቸዋል ብለዋል።
እርሳቸው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ወቅታዊውን የድንበር ግጭት እንደ ማሳያ ያቀርቡታል እንዲሁም የመተከል ፖለቲካም ከዚህ የጥንቃቄ እይታ ራዳር ውስጥ መግባት እንዳለበት ይሞግታሉ።
እርሳቸው የመተከል ተወላጅ እንደመሆናቸው በአካባቢው የሚስተዋለው ትርምስ እና የንፁሃን ግድያ የካይሮ እና የሱዳን እጅ እንዳለበት በርካታ ሁነቶች አመላካች ናቸው በማለት ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይህ ትውልድ በደማቅ ታሪክ የሚከትበው ዳግማዊው የአድዋ ድል መሆኑን በርካቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።