ትህነግ አብዛኛውን አመራሩን ወደ ደደቢትና አካባቢው እንዲወርድ አድርጎ ነበር። አመራሩ ቢያንስ አንድ ቡድን እስከ 20 ሰው ተደራጅቶ፣ በየቡድኑ ፋይናንስ ኃላፊ፣ የፀጥታ አስተባባሪና መሰል ኃላፊዎች ተመድቦለታል። በመጀመርያው ወር የፋይናንስ ኃላፊው ለእያንዳንዱ የቡድኑ አባል ገንዘብ ይሰጥና የቡድኑ አባላት በየትንንሽ ከተማዎቹ የሚፈልጉትን እንዲገዙ ይደረግ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ስኳር፣ ውሃና ደረቅ ምግቦችን በየቡድኑ ተይዘዋል። ይሁንና ጊዜው ሲረዝም በግል ገንዘብ መስጠት አቁመው በቡድን እየተገዛ፣ በየገበሬው ቤት ምግብ እያስተባበሩ ወደ ደደቢት እንዲወርዱ ተደርጓል።
\ከዚህም ባሻገር የመከላከያ ቁጥጥር ሲጠናከር በየከተሞቹ እንደ ፈለጉትን መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው የምግብ አቅርቦት በቡድን እንዲሆን ተደርጓል። የገጠሩን አካባቢ የሚያውቁ አመራሮች ቢኖሩም መንገድ የሚመራቸው ገበሬው ገንዘብ ተከፍሎት ነው። ለአንድ መንገድ መሪ በአማካይ ከ5 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ይከፍላሉ። የሚጓዙት ሌሊት ሲሆን ስናይፐርና መትረየስ እንዲሁም የግል ክለሽ የያዙ ጠባቂዎች ለየቡድኑ ተመድበውላቸዋል። ጉዧቸው ጨካ ለጫካ ሲሆን ጊዜ ጠብቀው መንገዶችንና ገላጣ አካባቢዎችን ይሻገራሉ። በዚህ መልኩ የተደራጀው አመራር እርስ በእርሱ ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን የመረጃ ልውውጡ ሰው በሰው ነው። አንደኛውን ቡድን ከሌላኛው ቡድን የሚያገናኙ መረጃ አቀባዮች ያሉ ሲሆን “ድርጅቱ ይህን ወስኗል፣ ይህን አድርጉ ብሏል።” ብለው መልዕክት ያስተላልፋሉ። ይህ ድርጅቱ አስተላለፈው የሚባል “መመርያ” ይተገበራል።
ትህነግ ለአመራሩ “እያሸነፍን ነው። አሸንፈን ወደ ስልጣን እንመለሳለን።” የሚሉ መልዕክቶችን የሚያደርስ ሲሆን አብዛኛው አመራር ይህን በድርጅት ትዕዛዝ በየአካባቢው ለሚያገኘው ሕዝብና በስሩ ለሚገኘው አመራርም እንዲያስተላልፍ ይደረጋል።
አመራሩ በተለያየ አደረጀጀት የሚንቀሳቀስ ሲሆን የዞንና የወረዳ አመራሩ የክልሉ ዋና ዋና አመራሮች ካሉበት አደረጃጀትና እንቅስቃሴ የተለየ ነው። በቡድን የሚንቀሳቀሰው አመራር በጭምጭምታ ካልሆነ በስተቀር ሌላኛው አመራር ቡድን በየት በኩል እየሄደ እንደሆነ መረጃ የለውም። ነገር ግን “ድርጅቱ ወደ ደደቢ ውረዱ ብሎ ወስኗል።” የሚል “መመርያ ነው” ተብሎ ተነግሮ ደደቢት የወረዱ በርካታ አመራሮች አሉ። ከእነዚህ መካከል የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አካባቢ አመራሮች “አንታገልም” ብለው ወደ ሱዳን ሸሽተዋል። የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አመራሮች በትህነግ አመራሮች ከሶስት ጊዜ በላይ የግድያ እቅድ ወጥቶባቸዋል።
መጀመርያ ከጥቅምት 30 በኋላ ተከዜ ላይ “ወልቃይት ላይ የተሸነፍነው እነሱም አማራ በመሆናቸው መረጃ እየሰጡ ነው።” የሚሉ የትህነግ አመራሮች ሊገድሏቸው ካሰሯቸው በኋላ እንደገና ተለቅቀው ሽሬ ከገቡ በኋላም ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸው በሽሬ አመራሮች ጥረት ተርፈዋል። ወደ ደደቢት ከወረዱ በኋላ ተመሳሳይ ችግር ስለገጠማቸው ባሉበት ቡድን “ድርጅቱ ወደ ሱዳን ሄደን ተልዕኮ እንድንፈፅም አዝዟል።” የሚል መረጃ አድርሰው ወደ ሱዳን ሸሽተዋል። የዚህ ቡድን አባላት “አንዋጋም” በሚል ተነጋግሮና ማሳሳቻ መረጃ ተጠቅሞ ወደ ሱዳን ማቅናቱን ተከትሎ፣ ሌሎች የትህነግ አመራር አባላትም ወደ ሱዳን እያቀኑ ነው። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የዞን፣ የወረዳ አመራሮች ሀምዳይት ከተማ የገቡ ሲሆን ሌሎችም ወደሱዳን እያቀኑ መሆኑ ምንጮች ገልፀዋል። ወደ ሱዳን እየሸሹ ካሉት መካከል ከፌደራል መንግስቱ ስልጣን ትተው ወደ ትግራይ የሄዱ ሰዎችም እንዳሉበት ምንጮች ገልፀዋል።
ወልቃይት ጠገዴ ሰፊ ከመሆኑም ባሻገር፣ ጫካና የሰብሉ ቅሬት (የማሽላ ሰብልና አገዳው) ቀን ለመደበቅ አመች ነው። የትህነግ አመራሮች ወልቃይት ጠገዴ በተለይም ወደ ሀምዳይት አካባቢ የሚያሻግሩ ደላላዎች አሏቸው።መንግስት ከደደቢት ወደ ሱዳን እየሸሹ ያሉ የትህነግ አመራሮችን ላይ ትኩረት ቢያደርግ የተሻለ ነው። ወደ ሱዳን የሚያሻግሯቸው ደላላዎች አሉ። ከተከዜ ተሻግረው ወደ ሱዳን ሊያቀኑባቸው የሚችሉ ቦታዎች አሉ። ሌሊት ሌሊት የሚደረጉ ጉዞዎችም ላይ እንዲሁ። በተለይ አንድ የአማራ ክልልና የፌደራል አካል የተዋቀረበት ኃይል ወልቃይት ጠገዴ ላይ ተቀምጦ ወደ ሱዳንና ተከዜ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ቢያጠና፣ የፀጥታ ኃይሉንም ቢያማክር የፀጥታ ኃይሉን ስራ ቀላል ያደርገዋል።
አብዛኛው ወደ ደደቢትና አካባቢው የወረደው የትህነግ አመራር ትግራይ ውስጥ በትግል እናሸንፋለን በሚል በመመርያ የተሞላ ቢሆንም ወራት በዘለቀው የሌሊት ጉዞ የተዳከመና የተሰላቸው ቀላል አይደለም። ለተልዕኮም ይሁን ትግሉን ሸሽቶ ከሚሄደው ኃይል የሚገኘው መረጃም ዋና ዋና የትህነግ አመራሮችን ለመያዝ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
የትህነግ አመራሮች ሸሽተውም ቢሆን ሱዳን ቢገቡ ለድርጅቱ መስራታቸውን ይቀጥላሉ። ይህ መንገድ ያለ ብዙ ቁጥጥር ከተለመደ ደግሞ ትህነግ አደርገዋለሁ ለሚለው ትግል አቅም ያገኛል። በመሆኑም መንግስት ወደ ሱዳን የሚወስዱ መንገዶች ላይ ልዩ ጥናት አድርጎ መፍትሄ ማበጀት ይገባዋል።
