February 9, 2021

“ሰብአዊነትና ፍቅር ለትግራይ እና ለመተከል” በሚል በትግራይ እና በመተከል ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ በዛሬው እለት በይፋ ተጀምሯል።

ግሎባል አላየንስ የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት፣ የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞች እና አርቲስቶች ማህበር፣ የትግራይ እና የመተከል ድጋፍ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኞች እና የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር በጋራ በመሆን ድጋፉን ለማሰባሰብ እንሰራለን ብለዋል።

የድጋፍ ማሰባሰብ ስራው ዓላማ ከፖለቲካ አመለካከት ወይም ሌላ ማንኛውም ዓይነት ልዩነት በላይ ኢትዮጵያዊነትንና ሰብአዊነትን ማስቀደም መሆኑ ተገልጿል።

ድጋፍ ማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ እንደሆነ በድጋፍ ማሰባሰብ መርሀ ግብር ማስጀመርያው ላይ ተጠቁሟል።

ለዚህም በአዲስ አበባ በጣይቱ ሆቴል እና በኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር፤ በክልል በቀይ መስቀል ማህበር ዋና ጽ/ቤት እንዲሁም በክልል ከተሞች በቀይ መስቀል ማህበር ጽ/ቤቶች የዓይነት ድጋፍ በመለገስ የዜግነት ግዴታን መወጣት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

በገንዘብ ድጋፍ በኩልም ዜጎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀይ መስቀል ስም በተከፈተ የባንክ ቁጥር 10003277016559 ከ5 ብር ጀምሮ እንዲረዱ የተጠየቀ ሲሆን በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በግሎባል አላየንስ በተከፈተ ጎፈንድሚ እንዲረዱ የድጋፍ አሰባሳቢ ህብረቱ ጠይቋል።