
9 የካቲት 2021

የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው ሕወሓት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ፈፅሟል መባሉን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ “የሕግ ማስከበር” የሚለውን ወታደራዊ ዘመቻ መውሰድ ከጀመረ መቶ ቀናት ሊሞላው የቀረው በጣት የሚቆጠር እድሜ ብቻ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በህወሓት ኃይሎች ላይ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያዘዙት በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል በተለያዩ ግንባሮች ጦርነት ተካሂዶ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ዋና ከተማዋ መቀለን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ ከተሞችን በሦስት ሳምንት ውስጥ መቆጣጠር መቻሉ ይታወሳል።
ኅዳር 19/2013 ዓ.ም የፌደራሉ ሠራዊት መቀለን መቆጣጠሩን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ ጦርነቱ መጠናቀቁን እና ቀጣይ የመንግሥታቸው ተግባር በሕግ የሚፈለጉ የህወሓት አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋል እና ትግራይን መልሶ መገንባት መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚያ በኋላም ከፍተኛ የሕወሓት አመራሮች በመከላከያ ቁጥጥር ስር ሲውሉ የተወሰኑት ደግሞ ተገድለዋል።
ምንም እንኳን የፌደራል መንግሥቱ መቀለን መቆጣጠሩን ተከትሎ ውጊያው ተጠናቋል ቢልም የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ አካላላት በገጠሪቷ የትግራይ ክፍል ውጊያው እንደቀጠለ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።
- “ወታደራዊው ተልዕኮ ውስን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ
- በትግራይ ለ2.3 ሚሊዮን ህፃናት እርዳታ ማድረስ አልተቻለም- ዩኒሴፍ
- ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እንዴት ትውጣ?
የአገር መከላከያ ሠራዊት መቀለ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ወደ ከተማዋ አቀንተው ከከፍተኛ የጦሩ አዛዦች ጋር ውይይት ባደረጉትበት ወቅት፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት የተልዕኮ አፈጻጸም “የየትኛውም አገር ወታደር አይደግመውም” ብለው ነበር።
የአገር መከላከያ ሠራዊት አዛዦች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሰጧቸው ቃለ መጠይቆች ሠራዊቱ “አስደናቂ” የሚባለውን ድል በአጭር ጊዜ መቀዳጀት የተቻለው በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ነው ይላሉ።
እነዚም ሠራዊቱ “በእልህ” በመዋጋቱ” እና የሎጂስቲክ አቅርቦቱ የተሟላ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ለዘመቻው ስኬት ወሳኝ ነበሩ ያሉትን ጠቅሰዋል።
የሰሜን እዝ በወፍ በረር ሲቃኝ
የሰሜን እዝ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተካሄደውን ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነትን ተከትሎ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ጀምሮ በትግራይ ክልል ውስጥ የሰፈረ ሲሆን አገሪቱ ካላት ሠራዊት ውስጥ በሰው ኃይልና በታጠቀው መሳሪያ አንጻር ግዙፉ እንደሆነ ይታመናል።
የሕወሓት ተዋጊ ኃይል በበኩሉ በርካታ ድል ያስመዘገበ ጦር ነው።
በ1993 ዓ.ም ወታደራዊውን መንግሥት ከሥልጣን ያስወገደና ለረዥም ዓመታት የተካሄደ ጦርነትን በድል አጠናቅቋል።
በ1990 ዓ.ም ደግሞ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር የነበረው ጦርነት ላይ የኢትዮጵያ ጦር የሰሜን እዝ ተሳትፏል።
በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለውጊያ ዝግጁ የሆኑ እስከ 200 ሺህ ገደማ ወታደሮች እንዳሉት ይነገር ነበር።
የሕወሓት ታጣቂ ኃይሎች
የህወሓት ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በገጠሙት ጦርነት የክልሉን ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ማሰለፋቸው ይታመናል። ነገር ግን የትግራይ ልዩ ኃይል ወታደሮችና የሚሊሻ ብዛት በትክክል አይታወቅም።
እንዲሁም ይህ ወታደራዊ ኃይል የሚታጠቀው መሳሪያ ብዛት እና ዓይነትም በግልጽ አይታወቅም።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አህመድ የአገር መከላከያ ሠራዊት መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በከተማዋ ተገኝተው ከአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ከከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት የህወሓት ኃይል ብዛት ወደ 80 ሺህ ይገመት እንደነበር ተናግረዋል።

ህወሓት ፈፀመ የተባለው ጥቃት በሰሜን እዝ ላይ ምን ያህል ጉዳት አደረሰ?
በብአዴን አባልነታቸው እና በሕወሓት ደጋፊነታቸው የሚታወቁት ሴኩ ቱሩ በህወሓት ሥር ይንቀሳቀስ በነበረው የቴሌቪዥን ጣብያ ላይ ቀርበው የሕወሓት ኃይሎች ሰሜን እዝን ስለማጥቃታቸው ተናግረው ነበር።
በዚህ በክልሉ ይተላለፍ በነበረው ቴሌቪዥን ላይ ሴኩ ቱሬ ቀርበው ሲናገሩ ” ትግራይን ለማንበርከክ በሁሉም አቅጣጫ የተሸረበው ሴራ ሊጠናቀቅ መቅረቡን ደርሰንበታል፣ በፍጥነት መወሰን ያስፈልግ ነበር. . . ለዚያም ነው የሰሜን እዝን በፍጥነት በ45 ደቂቃ ለመቆጣጣር እርምጃ የተወሰደው” ብለዋል።
- “ባለቤቴ ጫካ ውስጥ መንታ ተገላግላ አረፈች” የትግራዩ ተፈናቃይ በሱዳን
- የማይካድራ ሰቆቃ በመርማሪ ቡድኑ አባል አንደበት
- በማይካድራ ግድያ ከተጠረጠሩት መካከል 36ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ
የሕወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረፂዮን ገብረሚካዔል በበኩላቸው የሕወሓት ታጣቂዎች የሰሜን እዝን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውንና የመከላከያ አባላት ከትግራይ ወገን መቆማቸውን በወቅቱ ተናግረው ነበር።
የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያክል እንደሆነ በመንግሥት በይፋ የተነገረ ነገር የለም።
ይሁን እንጂ በሰሜን ዕዝ ሥር ከሚገኙ ቢያንስ በአራት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የጦር አዛዦች ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል።
7ኛ ሜካናይዝድ
በሰሜን ዕዝ ስር ከሚገኙት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የ7ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ግርማ ከበበው በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ላይ በተላለፈው ቃለ መጠይቃቸው፤ በሚመሩት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል።
መድፍ፣ ታንክና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን እንደታጠቁና “የህወሓት ኃይሎች የጦር መሳሪያ ለመዝረፍ” በክፍለ ጦራቸው ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ብርጋዴር ጀነራል ግርማ ተናግረው፤ ጥቃቱን ሲከላከሉ ቆይተው ከ8ኛ ሜካናይዝድ ጋር ወደ ኤርትራ መሸሻቸውን ገልጸዋል።
“ሁለቱ ክፍለ ጦሮች (7ኛ እና 8ኛ) አንድ ላይ ሆነው ትልቅ መሰዕዋትነት ነው የተከፈለው። እነዚህ ሁለት ሜካናይዝድ ጦሮች የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። ከባድ መሳሪያዎችን ይዘን ባንወጣ ኖሮ ከባድ አደጋ ይደርስ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
8ኛ ሜካናይዝድ
የ8ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ናስር አባዲጋ በተመሳሳይ በሰጡት ቃል “የህወሓት ኃይሎች በእዙ ስር በሚገኙ ክፍለ ጦሮች ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ጥቃት መፈጸማቸውን” ተናግረዋል።
ብርጋዴር ጀነራል ናስር የጥቃቱ ዓላማ “የጦር መሳሪያዎችን ለመዝረፍ ያለመ እንደነበረ” ተናግረው፤ እርሳቸው ከሚመሩት ክፍለ ጦር “ምንም አይነት መሳሪያ አለመዘረፉን” ተናግረዋል።

5ኛ ሜካናይዝድ
በሰሜን ዕዝ የ5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ሙሉዓለም አድማሱም በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ የሚመሩት ጦር በህወሓት ኃይሎች ለሦስት ቀናት ተከቦ መቆየቱን ገልጸዋል።
ማዘዣውን ዳንሻ ከተማ ባደረገው 5ኛው ሜካናይዝድ ጦር ላይ ጥቅምት 24 ጥቃት የተከፈተው “ሠራዊቱ ታጥቆ የሚገኘውን ከባድ መሳሪያዎች ለመዝረፍ” እንደሆነ ብርጋጄር ጀነራል ሙሉዓለም ተናግረዋል።
“የጥቃቱ አላማ የዕዙን ትጥቅ ለመንጠቅ ነበር። ትጥቆቻችን በእጃችን ነው ያሉት። ምንም ትጥቅ አልተዘረፈም” ብለዋል።
ብ/ጀ ሙሉዓለም ለሦስት ቀናት ያክል ተከበው ሲታኮሱ ከቆዩ በኋላ “ከበባውን ሰብረን ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረናል” ብለዋል።
4ኛ ሜካናይዝድ
በመቀለ ከተማ የሚገኘው 4ኛው ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረውት እንደነበረ በሰሜን ዕዝ የ4ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የጦር መሳሪያ ክፍል ኃላፊ ሻለቃ አድማሱ ደመቀ በኢቢሲ ላይ በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ተናግረው ነበር።
የህወሓት ኃይሎች ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ከምሽቱ 5፡30 ላይ ከሜካናይዝዱ አመራሮች መካከል ከተወሰኑት ድጋፍ በማግኘት ክፍሉን ከተቆጣጠሩ በኋላ ጦር መሳሪያዎቹንና ሰነዶችን መውሰዳቸውን ሻለቃ አድማሱ ተናግረዋል።
እንደ ኢትዮጵያ መንግሥት ከሆነ በአገሪቱ ትልቁ እንደሆነ በተነገረው የሰሜን እዝ ላይ የደረሰው ጥቃት በሚገባ ታስቦበትና ታቅዶ የዕዙን ጦር መሳሪያዎች ለመቆጣጠር ያለመ ነበር።
በርግጥ በዚህ ጥቃትም ሆነ ተከትሎ በነበረው ግጭት ዕዙን ምን ያህል እንደጎዳው ይፋዊ የሆነ መረጃ የለም።
ግልጽ የሆነው ነገር ቢኖር ለወራት የዘለቀው የፌደራል መንግሥቱና ትግራይን ሲያስተዳድር የነበረው ሕወሓት በበርካታ ጉዳዮች አለመግባባት፣ ወደ ሰሜን እዝን ማጥቃት እና በኢትዮጵያ የቅርብ ታሪክ ውስጥ ከተደረጉ ጦርነቶች መካከል አንዱና ቁልፉ ሆኖ መመዝገቡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከጥቅምት 24 ጥቃት በኋላ ሕወሓት ቀዩን መስመር በማለፍ የፌደራል መንግሥቱን ምርጫ በማሳጣት እርሳቸው “የሕግ ማስከበር” ያሉትን ዘመቻ ለማካሄድ ተገድዷል ብሏል።
በክልሉ የከሰተው ግጭት በርካቶች ቀያቸውን ጥለቀው እንዲሰደዱም አድርጓል።
ከ2 ሚሊዮን በላይም በዚያው በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው ይገኛሉ። ከ50 ሺህ በላይ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ሸሽተዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ከትግራይ ክልል እየተሰደዱ ያሉ ዜጎችን ለመድረስ እንዲቻል ያለገደብ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። በክልሉ ያለው ሁኔታም ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ሊሸጋገር ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ምን ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም።