
በአዲስ አበበ ከተማ በ700 ሚሊየን ብር የተገነባው ደረጃውን የጠበቀ የእናቶችና ሕፃናት ዘመናዊ ሆስፒታል ዛሬ ተመርቋል፡፡
የፌዴራል እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የክብር ዶክተር አበበች ጎበናን ጨምሮ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ሆስፒታሉን መርቀው የከፈቱት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ናቸው፡፡
አበበች ጎበና የእናቶችና ህፃናት ዘመናዊ ሆስፒታል የሚል ስያሜ የተሰጠው ሆፒታሉ በ22 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ከ400 በላይ ተኝቶ መታከሚያ አልጋዎች አሉት፡፡–በተጨማሪም 100 የልህቀት ማዕከል አገልግሎት መስጫ ክፍሎች እና በተመሳሳይ ሰዓት ለ7 እናቶች የኦፕራሲዮን አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ክፍሎች አሉት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የአገልግሎት ችግር ላለበት የእናቶችና ሕፃናት ጤና ቅድሚያ በመስጠት ለመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ታስቦ የተጀመረውን ሕንፃ 700 ሚሊየን ብር መድቦለት ግንባታውን በማሻሻል ወደ ሆስፒታልነት እንዲቀየር አድርጓል።
ሆስፒታሉ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን ያሟላ ከመሆኑ በተጨማሪ ወረቀት አልባ መስተንግዶ ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡በአያት አካባቢ የተገነባው ይህ ሆስፒታል በከተማዋ ያለውን የእናቶች የሕክምና አገልግሎት ለማሻሻል ያስችላልም ተብሏል፡፡
