11 የካቲት 2021, 12:07 EAT

መምህር ትምህርት እየሰጠ

የትምህርት ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) በትግራይ ክልል የሚገኙ ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ፈተናውን በዩኒቨርስቲዎች እንደሚወስዱ ገለጹ።

በአካባቢው የትምህርት መሠረተ ልማቶች ሙሉ ለሙሉ በመውደማቸው ፈተናውን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንደሚወስዱ አስረድተዋል።

በሚቀጥሉት ሳምንታት ተፈታኞች በክልሉ ወደሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደሚጓጓዙና ፈተናቸውን የሚወስዱባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማ መቀለ፣ አክሱም፣ አዲግራት እና ራያ የኒቨርስቲዎች እንደሆኑ ተገልጿል።

በኦንላይን (በበይነ መረብ) ይሰጣል ተብሎ የነበረው የ12ኛ ክፍል ፈተና ከየካቲት 29፣ 2013 ዓ. ም ጀምሮ በወረቀት እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከየካቲት 22 እስከ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የዲጂታል መታወቂያ ይሰራጫል ብሏል።

ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በበይነ መረብ (ኦንላይን) ይሰጣል ተብሎ የነበረው ፈተና በወረቀት እንደሚሰጥም የትምህርት ሚኒስትሩ መግለፃቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የፈተናው ገለጻ የካቲት 26 ቀን ተካሂዶ ፈተናው ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥም ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ፈተናው በወረቀት እንዲሰጥ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ታብሌቶች ወደ ሀገር ውስጥ ባለመግባታቸው ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴር በፈተና አሰጣጡ ላይ ለተፈጠረው መዘግየት ይቅርታ ጠይቋል።

ከየካቲት 21 እስከ የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ/ም ፈተናው እና የመልስ መስጫ ወረቀቶች ወደ ዞኖች እንደሚደርሱ ተገልጿል። በዚህም መሰረት የ2012 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ይሰጣል።

ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ላይ የትምህርት ሚኒስቴርና የአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ዝግጅት በማስመልከት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ 450 ሺህ ታብሌቶች እስከ ታህሳስ መጨረሻ ድረስ ከውጭ እንደሚገቡ እና 12 ሺህ ላፕቶፖች ደግሞ ለፈታኞች ለማከፋፈል ዝግጁ መሆናችውን መናገራቸው ይታወሳል።

በኦንላይን የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናም እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ለመስጠት እቅድ መያዙን ገልጸው ነበር።

ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ግን በተለያዩ ደረጃዎች የመማር ማስተማሩ ሂደት ይጀምራል ተብሎ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በትግራይ ውስጥ በተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል።