11 የካቲት 2021, 09:54 EAT

የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌደሬሽን በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በግጭቱ ተጎጂ ለሆኑት ተጨማሪ እርዳታ እንዲደርስ ጥሪ አቅርቧል።
የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ፍራንሴስኮ ሮካ በጉብኝታቸው ወቅት የተመለከቱት ነገር በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱን ተከትሎ ለንጹሀን ዜጎች የሚደረገውን እርዳታ የሚያስተባብሩ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ እንዳይንቀሳቀሱ ከልከሏል የሚል ክሰ ሲቀርብበት ነበር።
መንግሥት በበኩሉ እርዳታ ወደ ክልሉ እንዲገባ ከፍተኛ ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ዋና ከተማን የጎበኙት ፕሬዝዳንቷ በጦርነቱ ምክንያት በደረሰው ጉዳት ከፍተኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን መሆናቸውን አስታውቀዋል።
አክለውም ሆስፒታሎች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው መሰረታዊ የህክምና መስጫ ቁሳቁሶች እንኳን እንደሌላቸው ገልጸው በተጨማሪ ደግሞ የምግብ እጥረት አካባቢውን እንደሚያሰጋውም አስታውቀዋል።
- በትግራይ ለሕጻናት የሚደረገው ድጋፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተባለ
- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዝግጅት
- በአንዲት ሴት የስልክ ጥሪ ለመጀመሪያው ግጭት የተቀሰቀሰችው ከተማ -ቅራቅር
የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌደሬሽን ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ላይ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት በርካታ ንጹሀን ዜጎችን ተጋላጭ እንዳደረገና ችግሩ በጎረቤት አገራትም ተጽዕኖ እንደፈጠረ መግለጹ የሚታወስ ነው።
ሌላው ቀርቶ ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት እንኳን አካባቢው በምግብ እጥረት፣ የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረራ እና ኮቪድ-19 ወረርሺኝ ሲጠቃ ነበር ብሏል ድርጅቱ።
በሚቀጥሉት ሳምታት ውስጥ በተለይ የምግብ እርዳታ ወደ ክልሉ በቶሎ የማይገባ ከሆነ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ድርጅቱ አሳስቧል።
መንግሥት በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ መፍቀድ የማይፈልገው ክልሉን ገና ሙሉ በሙሉ ባለመቆጣጠሩ ምክንያት እንደሆነና ምግብ በበቂ ሁኔታ እንዳይገባ የሚያደርገውም በሽሽት ላይ የሚገኙት መሪዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ እንደሆነ አንዳንድ ተንታኞች ይገልጻሉ።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው መቃቃርና አለመግባባት ተካሮ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ሁኔታ “የከፋ” ሲል ገልጾታል።
በተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰውና የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንደሚለው በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል።
የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች ህዝቡን መደረስ እንዳልቻሉም ሲናገሩና መንግሥት እንዲያመቻች ሲጠይቁም ተሰምተዋል።
በክልሉ ውስጥ ያለው ሁኔታ አስከፊ እንደሆነና “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ” አንድ የመንግሥት ባለስልጣን መናገራቸውን ከእርዳታ ሠራተኞች ጋር ከተደረገ ስብሰባ ላይ ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ ላይ የሰፈረ ጽሁፍ ማመልከቱ የሚታወስ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ደኅንነትና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና የሰብአዊ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።
ከሰሞኑም እንዲሁ በክልሉ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና የሕክም አቅርቦቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለ1.8 ሚሊዮን ሰዎች መድረሱን የሠላም ሚኒስቴር ገልጿል።
ሚኒስቴሩ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች እየቀረበ ያለውን እርዳታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ከተጠቀሱት ሰዎች በተጨማሪ በክልሉ 2.5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አመልክቷል።