
የብልጽግና ፓርቲ በመጪው ምርጫ ጥሩ ውጤት ማስመዘገብ ከፈለገ ሁለት ነገሮችን ማድረግ አለበት። አንደኛው ሕገ መንግስቱንና የጎሳ አወቃቀሩን እንደሚቀይር በማኒፎስቶው ላይ ማስቀመጥ አለበት። ሁለተኛው ደግሞ አዲስ የፓርቲ መሪ መሾም አለበት። አሁን የብልጽግና አቋም ምን እንደሆነ አይታወቅም። የውስጥ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአማራ ብልጽግና አመራሮች “ሕገ መንግስቱ አማራ ጠል ነው ፡፡ መሻሻል አለበት፣ አወቃቀሩ መቀየር አላበት” ይላሉ ። የኦሮሞ ብልጽግናዎች ደግሞ “የሕወሃት ሕግ መንግስት ከተነሳ ሞተን እንገኛለን” እያሉ ነው። የትኛው ነው የብልጽግና አቋም ???? የሚታወቅ ነገር የለም። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አብይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት ባስተዋወቁበት ጊዜ ፓርቲው ማኒፊስቶ እንዳዘጋጀ ተገልጿል። ተዘጋጀ የተባለውም ማኒፌስቶ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ፣ ሕግ መnግስቱንና አወቃቀሩን በተመለከተ የሚነሱ ብዥታዎችን ግልጽ አላደረገም። ይመስለኛል ስምምነት በውስጣቸው ስለሌለ፣ የሚያማምሩ ባዶ ቃላቶችን በመደርደር፣ መሰረታዊ መሻሻሎችን በማድረግ ዙሪያ ዉሳኔ ማሳለፉን በይደር ለማቆየት የወሰነ ይመስላል።
በዚህ ጉዳይ ላይ እልባት የሚሰጠው ጠቅላላ ጉባዬው ነበር። ግን ጠቅላላ ጉባዬው ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ስለተገመተ እነ ዶር አብይ ጉባዬውን እንዲደረግ የፈለጉም አይመስልም።
ሁለተኛ አዲስ መሪ መሾ ነው፡፡
አሁን እየመራ ያለው ዶር አብይ አህመድ ላለፊት 3 አመታት አገሪቱን የመመራት እድል አግኝቷል፡፡ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ተችሮታል፡፡ ሆኖም በርሱ አመራር አገሪቷ የከፈ ደረጃ ላይ ነው የወደቀችው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የአማራ ክልል፣ የትግራይ ክልል ፣ እንደ ወላይታ ባሉ በርካታ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ዶር አብይ አህመድ እንኳን ድጋፍ ሊኖረው እንደውም በፊት አቶ ኃይለማሪያም፣ እነ አቶ መለስ ዜናዊ ላይ የነበረው አይነት ተቃዋሞን እያስተናገደ ያለበት ሁኔታ ነው ያው፡፡
በኦሮሞ ክልል ምን አልባት ከጂማ፣ ኢሊባቡርና ሸዋ በቀር በሌሎች እንደ ወለጋ፣ አርሲ፣ ባሌ ባሉ አካባቢዎች ጠቅላይ ሚኒስተሩ ድጋፍ ያለው አይመስልም፡፡ ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ ያው ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡አዲስ አበቤ የዶር አብይ ድርጅት የኦህዴድ የግፍና የተረኝነት ፖሊሲ ሰለባ ሆኖ እያለቀሰ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለዚህም ነው ብልጽግና ትንሽ ቢሆን ተቀባይነት እንዲኖረው መሪዎች መቀየር አለበት የሚል አስተያየት የምሰጠው፡፡ የመሪ ለውጥን በተመለከተ አንዳንዶች ከዶር አብይ ውጭ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል ? ሲሉ ይደመጣሉ።
የብልጽግና ፓርቲ ብዙ ብቃት ያላቸው በአስር እጥፍ ከዶር አብይ የሚበልጡ አመራሮች አሉት። ፓርቲው ሆን ብሎ ዶ/ር አብይን ብቻ እያጎላ ስለሚያቀርብ፣ ዶክተሩም በሁሉም ነገር ክሬዲት መውሰድ የሚፈልግ በመሆኑ፣ ሕዝብ የሚሰማው እርሱን ብቻ ስለሆነው ነው እንጂ ሌሎች ብዙ አመራሮች አሉ። የብልጽግና ፓርቲ የአንድን ሰው ተክለ ሰውነትን በመገንባት ላይ ያተኮረ ስለሆነ (ያው ደቡብ ኮሪያ እንደሚያደርጉት) ሌሎች አመራሮች የተሸፈኑበት ሁኔታ ነው ያለው። እንደው እንደምሳሌ ሁለት የብልጽግና አመራሮች ልጥቀስላችሁ።
አንደኛ ዶር አብይን መተካት የሚችለው አቶ ሙስጠፌ ኡመር ነው፡፡ አቶ ሙስጠፌ በቆዳ ስፋት ትልቅ የሆነ፣ ከኦሮሞና አማር ክልል ቀጥሎ ትልቅ ህዝብ ያለውን የሶማሌ ክልልኝ እያስተዳደረ ያለ ሰው ነው። ክልሉ በጣም ብዙ ችግሮች የነበሩት ክልል ነው። አቶ ሙስጠፌ ያንን ክልል አረጋግቶ አሁን አካባቢው በብዙ እጥፍ እየተሻሻለ የመጣ ክልል ሆኗል። ጂጂጋ ከተማ እጅግ በጣም ተወዳጅ ከተማ እየሆኑ ከመጡ ከተሞች መካከል በቀዳሚነት የምትጠቀስ ናት። እንግዲህ በስራ እንመዘን ከተባለ ሙስጠፌ በስራው ያሳየ ሰው ነው። በቅርቡ በጎዴ የአይሮፕላን ማረፊያ ተመርቋል፡፡ በርካታ መንገዶች በክልሉ ተሰርተዋል፡፡ በሸበሌ ወንዝ ዳር በመስኖ በርካታ የእርሻ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው፡፡ የኦጋዴን ነጻ አውጭዎች በሰላም እንዲቀንሳቀሱ በማሳመን፣ ይኸው ኦብነግም ያለ ምንም ችገ የሶማሌ ክልል ልማት ተሳታፊ ሆኗል፡፡ (ያው በኦብነግ ውስጥ እርስ በርሳቸው ያለው መከፋፈል እንደተጠበቀ)
እዚህ ጋር እነ ዶር አብይ ወደ ኦሮሞ ክልል እንዲገባ ካደረጉት ከኦነግ ጋር ያለውን ነገር ማነጻጸሩ ጠቃሚ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት እነ ዶር አብይ ከኦነጎች ጋር ጦርነት ላይ ነው ያሉት፡፡ እነ መስጠፌ ግን ኦብነነጎች አሳምነው የሶማሌ ክልል ሰላማዊ ክልል እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ እነ ዶር አብይ በሚመሩት የኦሮሞ ብልጽግና ስር ባለው በኦሮሞ ክልል ሌሎች ማህበረሰባት እንደ መጤ እየተቆጠሩ በሌሎች ላይ ከፍተኛ ሰቆቃ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችም እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ በኦሮሞ ክልል በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኦሮምኛ የማይናገሩ ሁለተኛ ዜጎች ተደርገው በአገራቸው አገር አልባ ሆነዋል፡፡ በሶማሌ ክልል 98% ሶማሌኛ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ ሆኖም የሶማሌ ክልል በአሁኑ ወቅት ሶማሌ ያልሆኑት በሰላምና በነጻነት የሚኖሩባት ክልል ሆናለች፡፡
ከአቶ ሚስጠፌ ሌላ ወ/ሮ ዳግማዊት ምገስም አለች፡፡ ሌላዋ የብልጽግና አመራር ናት። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ነበረች። በብቃቷ ከአዲስ አበባ ዩኒቨሪሲቲ በአዲስ አበባ መስተዳደር እንድትሰራ ተጠይቃ ፣ በመስተዳደሩ ብዙ ውጤቶች ያስመዘገበች እህት ናትነ። በስራዋም የአዲስ አባበ ምክትል ከንቲባ ሆና ትሰራም ነበር። አቶ ድሪባ ኩማ ከሃላፊነቱ ሲነሳ ለተወሰነ ጊዜም በምክትል ከንቲባ ማእረግ በከንቲባነት ሰርታ ነበር። ኢንጂነር ታከለ እስኪሾም ድረስ። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ መሆን የነበረባት እርሷ ነበረች። ብቃት ያላት፣ የተማረች ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነች። ሆኖም እነ ዶር አብይ በአዲስ አበባ የፊንፊኔ ፕሮጀክታቸውን የሚያሳካላቸው ስለፈለጉ ወ/ሮ ዳግማዊ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አልተፈለገችም። ከአዲስ አበባ መስተዳደር ተገፍታ ወጣች።
እነ አቶ ደመቀ መኮንን የዚች እህት ብቃትና ችሎታ ስላወቁ የአዴፓ ከፍተኛ አመራር አባል እንድትሆን መረጧት። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ድልድል የተደረገው በኮታ ነው። ዶር አብይ ለብአዴን ከተሰጡ ኮታዎች ውጭ ያሉን ሚኒስቴሮች የሾመው እርሱ ነው። ለብአዴን የተሰጡትን የሾሙት ግን እነ አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው። ለብአዴን ከተሰጡ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች መካከል አንዱ የትራስፖርት ሚኒስቴር ነው። ወ/ሮ ዳግማዊትም በአዴፓ አመራሮች የትራንስፖርት ሚኒስቴር እንድትሆን ተመደበች። እዚህ ጋር እንግዲህ ልብ እንድንል የሚያስፈልገው ወ/ሮ ዳግማዊትን የሾማት ዶር አብይ አህመድ አለመሆኑን ነው።
ወ/ሮ ዳግማዊት የትራስፖርት ሚኒስቴር ስትሆን ዶር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትራስፖርት ሚኒስቴር ቁጥጥር ስር ወጥቶ በጓደኛው በአህመድ ሺዴ (የገንዘብ ሚኒስቴር ስር) እንዲሆን አደረገ። ሆኖም ግን ወ/ሮ ዳግማዊት ቦይንግ ኩባኒያ የተከሰከሰውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን አስመልከቶ ሃላፊነቱን ላለመውሰድ በኢትዮጵያ ፓይለቶች ላይ ለማላከክ ፣ ከተጠያቂነት ለማምለጥ በሞከረበት ጊዜ በቀዳሚነት ወ/ሮ ዳግማዊት ቦይንግን በመጋፈጥ የሰራቸውን ስራ ሁላችንም የምናስታወሰው ነው። በብቃት ሃላፊነቷን በመወጣቷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመመከት የቻለች፣ የአገራችንን ጥቅም ያስጠበቀች የመንግስት ባለስልጣን ናት።
የአዲስ አበባ ኢኮኖሚ ከአማራ ክልል ወይንም ኦሮሞ ክልል ኢኮኖሚ የበለጠ ነው። ምን አልባትም የሁለቱም ተደርቦ። ያንን ያህል ኢኮኖሚ ትመራ የነበረች ናት። የአዲስ አበባ ህዝብ የሃረሬ፣ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የቤኔሻንጉል ክልሎች ተደምረው፣ እንደምክባለው ከትግራይና ከሶማሌ ክልሎች የበለጠ ህዝብ የሚኦርባትን አዲስ አበባ ከተማ ታስተዳድር የነበረች ናት።
በአሁኑ ወቅትም ቁልፍ የሆነ የመንግስት የሚኒስቴር መስሪያ ቤትን በብቃት እየመራች ነው። ወ/ሮ ዳግማዊት የአዲስ አበባ ልጅ ናት። ምን አልባት የአዲስ አበባ ልጅ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆን አይቻልም የሚል አሰራር ከሌለ በቀር ወ/ሮ ዳግማዊት በብዙ እጥፍ ከዶር አብይ በሁሉም መስፈርት ብትሻል እንጂ የምታንሳ አይደለችም።
