ሁሉም አብሮነቱንና የድርሻውን ሳይረሳ የምርጫ ውድድሩን እንዲጀምር የቦርድ ሰብሳቢዋ ጥሪ አቀረቡ
17 February 2021
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በመጪው አጠቃላይ ምርጫ ለሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተወዳዳሪዎች ባቀረቡት ጥሪ፣ ‹‹የሁላችንንም አብሮነትና የእያንዳንዳችንን ድርሻ ሳንረሳ በበጎ መንፈስ የምርጫ ውድድሩን እንጀምር ስል ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታወቁ፡፡
‹‹ዛሬ ለስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በዕጩነት ስትመዘገቡ ወይም እንደ ፓርቲ ዕጩዎቻችሁን ስታስመዘግቡ፣ ከፊታችን ያለው መንገድ ከፊል ተስፋ፣ ከፊል ሥጋትን አዝሎ እንደሚጠብቃችሁ፣ እንደሚጠብቀን ለሁሉም ግልጽ ነገር ይመስለኛል፡፡ ይሁንና ሥጋትን ለመቀነስ ብሎም ወደ መልካም ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችለን አቅምና ዕድል በየፈርጃችን ይዘን ይህን የጋራ ሙከራችንን በዝለት ሳይሆን በጥንካሬ ልንጀምረው ይገባል እላለሁ፤›› ብለዋል፡፡
በቀደሙ ምርጫዎች ባልነበረ ሁኔታ የሒደቱን ዋና ተዋናዮች ማለትም ተፎካካሪዎችን ግራ ወይም ቀኝ፣ ትንሽ ወይም ትልቅ፣ አገራዊ ወይም ክልላዊ ሳይል፣ በጥረታቸው ሊያግዝና ሳንካቸውን ሊፈታ የተዘጋጀ፣ አቅሙን የጨመረ፣ የገለልተኝነቱን መጠንና ስፋት ከተፅዕኖ ሁሉ የሚከላከል የምርጫ ቦርድ ሒደቱን እያስተዳደረ እንደሚገኝ ወ/ሪት ብርቱካን አስረድተዋል፡፡
በፍትሐዊነት በተቃኘ በጎ ሐሳብ ሳይሆን በሸፍጥ፣ ሌላውን በማክበር ሳይሆን ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ በእንፃሩ የቆመውን በማጥፋት ባለመ ሐሳብ፣ የሁሉንም ዜጐች ሐሳብን የመግለጽ ሰላማዊ ዕድል ሳይሆን ኋላቀር የሆነ ግጭታዊ መስተጋብርን ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫን ያሰበ ተወዳዳሪ ቢኖር፣ ይህን ከምርጫ ፖለቲካ ውጪ የሆነ ሥራውን ለአደባባይ አውጥተው ለሰው ዓይንና ጆሮ ሊያደርሱ የሚችሉ በቁጥር ትንሽ የማይባሉ የሚዲያ አውታሮች እንደ አገር ያሉ በመሆኑ፣ ለተሻለ ሽግግር ወደፊት ለመቀጠል የሚያስችል አንድ በጎ እውነታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማኅበራት አናቂ ይባል ከነበረ የሕግ ማዕቀፍ ወጥተው፣ ዜጐችን ስለእውነተኛ ምርጫ ሊያሳውቁ፣ እንዲሁም የምርጫ ሒደቱን ጉበኛ (Watchman or Watchwomen) ሆኖ በታዛቢነት ለማገልገል በጣት በሚቆጠሩ ሳይሆን፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ አደረጃጀቶቻቸው ላይ መሰናዷቸውን ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና እንደሚሉ ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል፡፡
‹‹የአውሮፓና የአሜሪካ ታዛቢዎችም ይህን ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያለውን ኩነት በእንግድነት ሊታዘቡ ከመንግሥት ግብዣው ደርሷቸው፣ ከእኛው ጋር የሒደቱ አካል ሊሆኑ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ነው፤›› ብለው፣ ‹‹ብዙ ሌሎች የምርጫ ማሻሻያዎቻችንና ብዙ ጎኖች መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም በዚህ እንደ ብርቱካን ሚደቅሳ በሚወጣው የመጀመርያ የፌስቡክ መልዕክቴ በዝርዝር ላሰለቻችቸሁ አልወደድኩም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹ዛሬ ፓርቲዎች በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ዕጩዎችን በማስመዝገብ፣ በዕጩነት በመመዝገብ የምርጫ ዘመቻውን ምዕራፍ ስትከፍቱ፣ ለሒደቱ የሚጠቅም በጎ እሴት ለመጨመር፣ በችግር ፈቺነት በጋራ ለመሥራት፣ የፖለቲካ ጥቃትን አሮጌ ባህል ዕለት ተዕለት ለመግደል (Old Habits Die Hard) ወይም ከክፉ አመል መላቀቅ በቀላሉ አይሆንም የሚለውን ያስቧል)፣ ለዘመናዊና ለሥልጡን ውድድር ራሳችንን ለማደስ፣ ከምንም በላይ የዜጎቻችንን ባለሥልጣንነት በማክበር እንዲሆን እያሳሰበኩ፣ በዚህ አስፈላጊና ትልቅ ትርጉም ባለው ሥራ የሁላችንንም አብሮነትና የእያንዳንዳችንን ድርሻ ሳንረሳ፣ በበጎ መንፈስ የምርጫ ውድድሩን እንጀምር ስል ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ በድጋሚ የኢፌዴሪ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያለበትን ሕጋዊ ኃላፊነትና ግዴታ እንደሚወጣና እየተወጣም እንደሚገኝ አረጋግጥላችኋለሁ፤›› ብለዋል።
ሪፖርተር