የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳዉድ ኢብሳ

የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳዉድ ኢብሳ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በዚህ ዓመት ይካሔዳል በተባለው ምርጫ ላይ አይሳተፍም የሚለው መረጃ የተሳሳተ ነው ሲል አስተባበለ።

የግንባሩ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኦነግ በምርጫው አይሳተፍም በሚል የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ግንቦት 28 እና ሰኔ 5/2013 .ም ለማካሄድ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ ተደርጎ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረገ ነው።

በዚህም መሠረት ፓርቲዎች በይፋ የምረጡኝ ዘመቻ የጀመሩ ሲሆን የዕጩዎች ምዝገባም ተጀምሯል።

በምርጫው ይሳተፋሉ ተብለው ከሚጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ድርጅታቸው እተደረሰበት ነው ባሉት ጫና ምክንያት ከምርጫው ለመውጣት ተገዷል ማለታቸው ተዘግቦ ነበር።

ነገር ግን ሊቀ መንበሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ድርጅታቸው የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች እየገጠሙት መሆኑን አመልክተው፤ ቢሆንም ግን በመጪው ምርጫ ላለመሳተፍ አለመወሰኑን ገልጸዋል።

የዕጩዎች ምዝገባ ቀነ ገደብ እየተጠናቀቀ ነው። መንግሥት ደግሞ ጫና እያደረግብን ነውያሉት አቶ ዳውድ፤ በምርጫው አንሳተፍም የሚል ውሳኔ ላይ ግን አልደረስንምሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከምርጫው እራሳችንን አግልለናል ብለን አላወጅንም። ከእንዲህ አይነት ውሳኔ ለመድረስ የራሱ አካሄድ አለው። መወያየት ያለብን ነገር አለብለዋል አቶ ዳውድ ጨምረው።

ኦነግ በአመራሩ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ጉዳዩ በምርጫ ቦርድ እየታየ የቆየ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራና በአመራሩ በኩል የተፈጠረውን አለመግባባት መቋጫ እንዲያበጅለት ተወስኖ የጉባኤው መካሄድ እተጠበቀ ነው።

በተጨማሪም ግንባሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉት የፓርቲው ጽህፈት ቤቶች መዘጋታቸውንና በርካታ አመራርና አባላቱ በእስር ላይ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር በተጨማሪ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችል አቋም ላይ አንገኝም ሲሉ ተሰምተዋል።

ፓርቲዎቹ መንግሥት አባላቶቻቸውን እና ከፍተኛ አመራሮቻቸውን ማሰሩን እንዲሁም ቢሮዎቻቸው እንደተዘጉባቸው ይገልጻሉ።

መንግሥት በበኩሉ በእስር ላይ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ለእስር የተዳረጉት በፖለቲካ ተሳትፏቸው አይደለም ሲል ይደመጣል።

ለአራት አስርት ዓመታት ያህል በፖለቲካዊና ወታራደራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የቆው ኦነግ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

ኦነግ ከደርግ ውድቀት በኋላ የተመሠረተው የሽግግር መንግሥት አካል የነበረ ሲሆን ከገዢው ኢሕአዴግ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት አመራሩ ከአገር ወጥተው መቀመጫቸውን አሥመራ በማድረግ የትጠቅ ትግል ለማድረግ ወደ ጫካ ገብቶ ነበር።

ለዓመታት በስደት የቆው ኦነግ ከሦስት ዓመታት በፊት የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ወደ አገር ቤት ተመልሷል።

ከበርካታ ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ለመወዳደር የተዘጋጀው ፓርቲው፤ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ነው።

ፓርቲው በመንግሥት ይደርስብኛል በሚለው ጫናና በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረው ቅራኔ በምርጫ ተሳትፎው ላይ ተጽዕኖ ካላደረገበት በቀር በኦሮሚያ ክልል ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችል ይጠበቃል።

በዚህ ዓመት በሚደረገው አገራዊ ምርጫ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ መራጮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።

ቢቢሲ