መነሻ ገጽ
በመጪው ምርጫ ክልሎች የሚኖራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውክልና መቀመጫ ይፋ ሆነ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳና ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ

21 February 2021

ዮሐንስ አንበርብር

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ምርጫ ክልሎች በፓርላማ የሚመራቸውን የውክልና መቀመጫ ይፋ ሲያደርግ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት አባል ሆኖ በ2012 ዓ.ም. የተመሠረተው የሲዳማ ክልል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚኖረው መቀመጫ 19 እንደሚሆን አስታወቀ፡፡

በ2012 ዓ.ም. በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ ከደቡብ ክልል ተለይቶ የራሱን ክልል ለመመሥረት የወሰነው የሲዳማ ዞን አሥረኛው የኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ሆኖ መቋቋሙ ይታወሳል። 

ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው መረጃ ከትግራይ ክልል በስተቀር የሁሉንም ክልሎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውክልና ድርሻ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የደቡብ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልናም 104 እንደሆነ አመልክቷል። 

የደቡብ ክልል ላለፉት ለ26 ዓመታት ገደማ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነበረው ውክልና ወይም መቀመጫ 123 እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፣ ሲዳማ ከደቡብ ክልል ወጥቶ ራሱን የቻለ የሲደማ ክልል ከመሠረተ በኋላ፣ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚካሄደው 6ኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚኖረው የመቀመጫ ብዛት 104 ይሆናል። 

ሲዳማ በዞን ደረጃ ራሱን ሲያስተዳድር በነበረበት ወቅት 19 ተወካዮች ከሲዳማ ዞን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወከሉ የነበረ ሲሆን፣ ለመጀመርያ ጊዜ በክልልነት በሚሳተፍበት አጠቃላይ ምርጫ የሚኖረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልናም ተመሳሳይ ነው።

የምርጫ ክልሎችን ስለማቋቋም የሚገልጸው የምርጫ አዋጅ 1162(13) (ሀ) ለምርጫ አፈጻጸም ሲባል የምርጫ ክልሎች የአገሪቱን የወረዳ አስተዳደር አደረጃጀት መሠረት በማድረግ እንደሚመሠረቱ፣ የሕዝብ ቆጠራን መሠረት በማድረግ ማስተካከያ ሊደረግባቸው እንደሚችል ይደነግጋል። 

በዚሁ አንቀጽ ቀጣይ ንዑስ አንቀጽ ሥር ደግሞ የምርጫ ክልሎቹ ተቀራራቢ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው እንደሚሆኑ፣ በመካከላቸውም ሊኖር የሚችለው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ልዩነት ከ15 በመቶ ሊበልጥ እንደማይችል ይደነግጋል።

ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መረጃ የደቡብ ክልል ቀደም ሲል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረው መቀመጫ ላይ ከተደረገው ማሻሻያና አዲስ ለተመሠረተው የሲዳማ ክልል፣ ከተደለደለው የውክልና ድርሻ ውጪ ሌሎቹ ክልሎችና ሁለቱ የፌዴራል ከተሞች የነበራቸው የውክልና ድርሻ በነበረበት እንደቀጠለ መረዳት ይቻላል።

በዚህም መሠረት ኦሮሚያ ክልል 178፣ አማራ ክልል 138፣ ሶማሌ ክልል 23፣ አዲስ አበባ ከተማ 23፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 9፣ አፋር ክልል 8፣ ጋምቤላ ክልል 3፣ ሐረር ክልል 2 እና ድሬዳዋ ከተማ 2 መሆኑን መረጃው ያመለክታል።

በግንቦት ወር መጨረሻ እንዲካሄድ ቀን በተቆረጠለት 6ኛው አጠቃላይ ምርጫ በትግራይ ክልል እንደማይከናወን ምርጫ ቦርድ ቀድሞ ያስታወቀ ሲሆን፣ ቦርዱ ይፋ ባደረገው የክልሎች የፓርላማ ውክልና ድርሻ ውስጥም የትግራይ ክልል አልተገለጸም። ይሁን እንጂ ላለፉት አሥርት ዓመታት የትግራይ ክልል የፓርላማ ውክልና 38 እንደሆነ ይታወቃል።

ይህንን ከግምት በማስገባት ሥሌት ሲደረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጠቃላይ መቀመጫ ብዛት ከነበረበት 547 አልተለወጠም።

በአጠቃላይ አሁን የጊዜ ሰሌዳ በወጣለት 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በ673 የምርጫ ክልሎች የሚደረግ ሲሆን ፣ ለዚህም ሲባል 49,407 የምርጫ ጣቢያዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ከምርጫ ቦርድ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እንዲህ እንዳለ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የምርጫ ክልልና የምርጫ ጣቢዎች አደረጃጀት ላይ የአፋር ክልል ቅሬታ ማቅረቡ ተገልጿል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በስምንት ቀበሌዎች የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች፣ ያላግባብ በሶማሌ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ሥር በሚገኙ ቀበሌዎች ስም ተካተው ይፋ ተደርገዋል የሚል አቤቱታ ማቅረቡን ቦርዱ አስታውቋል። 

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአፋር ክልል የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ በፊት ውሳኔ እንደሚሰጥበት፣ የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።