በትግራይ ክልል በሚገኘው ዋነኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈጸመው ጥቃት ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል መመለሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።
በከፍተኛ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ በደረሰ ጉዳት ከማክሰኞ የካቲት 09/2013 ዓ. ም ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በመላው ክልሉ ከአንድ ሳምንት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተቋርጦ ቆይቷል።
በወቅቱ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳለው አዲጉዶም ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከአላማጣ – መሆኒ – መቀለ በተዘረጋ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ የ“ህወሓት ርዝራዦች” በፈጸሙት ጥቃት ነበር በክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል የተቋረጠው።
ድርጅቱ እንዳመለከተው በክልሉ ኤሌክትሪክ ከተቋረጠ በኋላ ባሉት ቀናት ሲከናወን በነበረው ጉዳቱን የመጠገን ሥራ በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ ዛሬ ረቡዕ 17/2013 ዓ.ም ከቀኑ አስር ሰዓት ከ20 ጀምሮ በትግራይ ዳግም የአሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተጀመሯል።
በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በመላው ትግራይ ዳግም ኃይል ተቋረጠ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሕዝቡ የህወሓት ኃይሎችን እንዳያስጠጋ አሳሰበ
በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ እንዲሳተፉ እስካሁን የተለዩ ተቋማት አለመኖራቸው ተገለጽ
በመላው ትግራይ የመብራትና የስልክ አገልግሎት መቼ ይጀምራል?
በደረሰበት ጥቃት ለኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ምክንያት የሆነው ይህ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረ ሲሆን ለመጠገንም ረዘም ያለ ጊዜ እንደወሰደ ተቋሙ አመልክቷል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በደረሰ ጉዳት ለረዥም ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ የነበረ ሲሆን በክልሉ ያሉ የተለያዩ አካባቢዎች ኃይል መልሰው ለማግኘት ረዘም ላለ ጊዜ ለመጠበቅ ተገደው ቆይተው ነበር።
በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ ሕዝቡ ከኃይል አቅርቦት ውጪ ከመሆኑ ባሻገር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የወጣባቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች መውደማቸው መገለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በደረሰባቸው ጥቃት ከአገልግሎት ውጪ የሆኑትን ለትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀርብባቸውን መሠረተ ልማቶች በመጠገን የክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲመለስ እየሠራ መሆኑን ገልጾ ነበር።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ክልሉ እንዳይረጋጋ ለማድረግ የሚሞክሩ “የተበተኑ የህወሓት ኃይሎች” እንዳሉና ሕዝቡም ለእነዚህ ኃይሎች መጠጊያ እንዳይሰጥ ማሳሰቡ ይታወቃል።
ጊዜያዊው አስተዳደር በመግለጫው “የተበተኑ” ያላቸው የህወሓት ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ መሸሸጋቸውን አመልክቶ “የጥፋት ኃይሎች በመንደሮችና በከተሞች ውስጥ ተሰማርተው የሕዝቡን ሠላም በማናጋት ወደ ሌላ የከፋ ቀውስ እንዲገባ እየሠሩ ነው” ብሏል።
ጨምሮም በእነዚህ ኃይሎች ላይ ሊወሰድ በሚችለው እርምጃ ሕዝቡ እንዳይጎዳ “የጥፋት ኃይሎቹን አሳልፎ እንዲሰጥ ወይም ለደኅንነቱ ሲል ራሱን ከእነዚህ ኃይሎች እንዲያርቅ” አሳስቧል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የፌደራል መንግሥት በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ የክልሉ አስተዳዳሪ የነበረው የህወሓት አመራሮች ከስልጣን በማስወገድ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መደረጉ ይታወሳል።
ወታደራዊ ግጭቱን ተከትሎ በክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል በመቋረጡ ምክንያት የውሃ፣ የባንክ፣ የስልክ፣ የኢንተርኔትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ለረዥም ጊዜ ተቋርጠው ቆይተው አብዛኛው የክልሉ አካባቢ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘው በቅርቡ ነበር።
ቢቢሲ