የመተከል ዞን ተፈናቃዮች በቻግኒ። የመተከል ዞን ባለፉት ሶስት አመታት የተለያዩ ጥቃቶችን ያስተናገደ ሲሆን በተለይም ከመስከረም 2013 ጀምሮ ተደጋጋሚ ማንነነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በዞኑ ተፈጽመዋል።
በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ወደ 7 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተሰደው ወደ ሱዳን መግባታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳለው ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከምዕራባዊው የኢትዮጵያ ከፍል የመተከል ዞን ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት ሱዳን መሸሻቸውን ገልጿል።
የኤጀንሲው ቃል አቀባይ ብባር ባሌክ ትናንት በጄኔቫ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደገለፁት፤ ከኢትዮጵያ ወጥተው ወደ ሱዳኗ የብሉ ናይል ግዛት የገቡት ሰዎች ቁጥር 7 ሺህ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።
እስካሁን 3 ሺህ የሚሆኑትን መመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው፤ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቅለው የመጡ ሰዎችን መመዝገብ ሲቻል ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል የኤጀንሲው ቃል አባይ ተናግረዋል።
በደቡብ ሱዳን 15 የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ አባላት ወደ አገራቸው አንመለስም አሉ
በእነ አቶ ጃዋር የሕክምና ጉዳይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ይግባኝን ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ
ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ብቻ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ወደ 1 ሺህ ለሚጠጉ ተፈናቃዮች እርዳታ አቅርቧል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ድጋፉ ምግብ፣ ህክምና፣ ውሃ እና የንፅህና መጠበቂያዎችን እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶችን ያጠቃለለ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ቀሪዎቹን ጥገኝነት ጠያቂዎች የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሱዳናዊያን ተቀብለው እያስተናገዷቸው እንደሚገኙ ተገልጿል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ባለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ ጥቃቶች በነዋሪዎች ላይ ተፈጽሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በተለይም ከመስከረም 2013 ጀምሮ ተደጋጋሚ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ተከስተዋል።
በተለይ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውስጥ በሚገኘው የመተከል ዞን የአማራ፣ የኦሮሞ እንዲሁም የሺናሻ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች ላይ በተፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተከፍተኛ ቁጥር ያለው ሞትና መፈናቀል ማጋጠሙ ይታወቃል።
በዚህም ሳቢያ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት እንዲሁም የማፈናቀል ተግባራት ተደጋግመው እንደተፈጸሙ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ ገልፀዋል።
በአሁኑ ጊዜ የክልሉና የፌደራል መንግሥት በጋራ ያወቀሩት የዕዝ ማዕከል ተደጋጋሚ ችግር ባጋጠመባቸው አካባቢዎች ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን የእርዳታና የመልሶ ማቋቋም ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።
የክልሉ ፖሊስ ከፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ጥቃት ፈጽመዋል በተባሉ ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአገር ውስጥ መገናና ብዙሃን ከዚህ በፊት የዘገቡ ሲሆን፤ በመተከል ዞን ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም የተባሉ አመራሮችን በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው መገለጹ አይዘነጋም።
ቢቢሲ