ፖለቲካ

ኦነግ በእስር የሚገኙ አባላቱ በዕጩነት እንዲመዘገቡ ምርጫ ቦርድን ጠየቀ

24 February 2021

ነአምን አሸናፊ

በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብቱ ያልተገደበ ሰው በዕጩነት የመቅረብ መብት እንዳለው በመጥቀስ፣ በየፖሊስ ጣቢያው የታሰሩና በሕግ አግባብ እየተጠየቁ ያልሆኑ፣ እንዲሁም በፍርድ ቤት በነፃ የተሰናበቱ አባላቱ ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቀረበ፡፡

ጥያቄውን ለቦርዱ ያቀረቡት ደግሞ ፓርቲውን ወክለው ቦርዱ ባዘጋጀው የዕጩዎች ምዝገባና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ በተደረገ ውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉት አቶ በቴ ኡርጌሳ ናቸው፡፡

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ ሌሎች የቦርዱ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙበት የውይይት መድረክ ማክሰኞ የካቲት 16 ቀን 2013 .. በሳፋየር ሆቴል የተከናወነ ሲሆን፣ በውይይቱ የተሳተፉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም፣ ገጠሙን ያሉዋቸውን በርካታ ተግዳሮቶች አስመልክቶ ለቦርዱ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡

ኦነግ በእስር የሚገኙና መብታቸው በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ያልተገደበ አባላቱን ለዕጩነት ከማቅረብ ባለፈም፣ ጽሕፈት ቤቱ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኝ በመሆኑ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቱን እንዲለቅለት፣ እንዲሁም ፍርድ ቤት በነፃ ቢያሰናብታቸውም እስካሁን በእስር ላይ የሚገኙ አባላትና አመራሮቹን በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጠው ቦርዱን ጠይቋል፡፡

በዚህም መሠረት ‹‹በእስር ቤት ያሉ ሰዎች በዕጩነት መቅረብ ይችላሉ ወይ?›› ለሚለው ጥያቄ፣ ‹‹አጭሩ መልስ አይችሉም ነው፤›› ሲሉ ዋና ሰብሳቢዋ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የማይቻልበትን ምክንያት ሲያስረዱም፣ ‹‹እሱን በር ከከፍትነው የኦነግ አባላት ብቻ ሳይሆኑ፣ በነፍስ ግድያም የተከሰሱ ግን ያልተፈረደባቸው እንደ ዕጩ እንቅረብ ሊሉ ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች ያቀርባሉ፡፡ የእኛ ሕግ ግን ያንን የሚይዝ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር በእስር ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በዕጩነት ይቀርባሉ የሚባልበት የሕግ አግባብ የለም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በፍርድ ቤት ያልተያዙና ምንም ዓይነት የፍርድ ቤት ቀጠሮ የሌለባቸው ሰዎችን በተመለከተ፣ በተለይ ደግሞ የኦነግ አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ጉዳያቸው እንዲታይላቸው ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየተነጋጋሩ እንደሆነ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቀጠሮ እስከሌላቸው ድረስ በእስር የሚቆዩበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ቀጠሮ ያለበትም በራሱ አግባብ መታየት አለበት ብለን ነው እዚያ ውስጥ የማንገባው፤›› ሲሉ አክለው አብራርተዋል፡፡

የጽሕፈት ቤት ጉዳይን በተመለከተ ደግሞ በኦነግ አመራሮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳ አንደኛው ሌላኛውን ‹‹ሊያጠቃኝ ነው›› የሚል ስሞታ በመኖሩ ፖሊስ በሥፍራው መኖሩን በመጥቀስ፣ ‹‹እኛ ጣልቃ ገብተን ውሳኔ የምንሰጥበት ሁኔታ ስለመኖሩ እርግጠኛ ስላልሆንን፣ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት (Intervention) ማድረግ አልቻልንም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ገዥው ብልፅግና ፓርቲን ወክለው የተገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ተቋማት ኃላፊ ዓለሙ ስሜ (/) በበኩላቸው፣ ‹‹ያላግባብ የታሰረ ካለ አሳሪው የሚጠየቅበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ ያላግባብ ሰው መታሰር የለበትም፡፡ በአግባቡ ለሕግ የቀረበ ሰው ደግሞ በምርጫ ምክንያት፣ ምርጫ እናሰምራለን ወይም እናደምቃለን ተብሎ የሕግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነገር መምጣት የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

በዕለቱ ቦርዱ ከዕጩዎች ምዝገባ ጋር በተያያዘ ምዝገባው ከተጀመረበት የካቲት 8 ቀን 2013 .. ጀምሮ ያሉ አኃዛዊ መረጃዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ምንም እንኳን ዕጩዎች ምዝገባ ከተጀመረ ሳምንት ያለፈው ቢሆንም የተመዘገቡ ዕጩዎች ግን ጥቂት እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ለአብነት ያህልም ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በተደረገው ምዝገባና ቦርዱ እስከ ሰኞ የካቲት 15 ቀን 2013 .. ከሰዓት በኋላ ድረስ ባጠናቀረው መረጃ፣ በቦሌ 3፣ በአራዳ 8፣ በልደታ 0፣ በአዲስ ከተማ 12፣ በቂርቆስ 5፣ በኮልፌ 1፣ በየካ 15፣ በጉለሌ 8፣ እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ 10 ዕጩዎች ብቻ መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

ከዚህ ተጨማሪም በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ የምርጫ ክልሎች ተከፍተው ዕጩዎችን ለመመዝገብ የተዘጋጁ ቢሆንም፣ እስከ ሰኞ ከሰዓት ድረስ ቀርቦ የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የግል ዕጩ አለመኖሩን ቦርዱ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች የምርጫ ክልሎች ያልተከፈቱባቸው ክልሎች ማለትም በአማራ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በሲዳማና በደቡብ ክልሎች ደግሞ ከማክሰኞ የካቲት 16 ቀን 2013 .. ጀምሮ የዕጩዎቸ ምዝገባ መጀመሩን ቦርዱ ይፋ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር